Saturday, August 3, 2013

Saturday, August 3, 2013 ጥያቄው ዛሬም የሕዝብ ጥያቄ ነው! ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ ሐምሌ 27 ቀን 2005 ዓ. ም. የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የፀረ-ኢትዮጵያው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አገዛዝ ለሱዳን መንግሥት በድብቅ አሳልፎ የሰጠውን የእርሻና ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ያለውን ለም የድንበር መሬት አስመልክቶ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም-አቀፍ ሕብረተሰብ እንዲያውቀውና ሴራውንም እንዲያወግዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ይታወቃል።Ethiopian Territorial Integrity and Ethiopiawinet Sudan annexing Ethiopian Territory በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት የወያኔ ገዥ ቡድን ለሱዳን በገፀ-በረከትነት የሰጠውን እርዝመቱ 1600 ኪ/ሜትር የጎን ስፋቱ ከ30 እስከ 60 ኪ/ሜትር የሆነውን የዳር-ድንበር መሬት ጉዳይ እንደ አንዱ ሕዝባዊ ጥያቄአቸው አድርገው እንዲይዙትና ይህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ የተፈፀመው ውልና ስምምነት ሕገወጥና ተቀባይነት እንደማይኖረው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ማስገንዘባችን የሚታወስ ነው። ከዚህ መነሻነት፤ ለሱዳን ፕሬዚዳንት ዑመር አል-በሽር፣ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ-ሙን፣ለአፍሪካ ሕብረትና ለሌሎች በርካታ ዓለም-አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት በተመለከተ የተለያዩ ደብዳቤዎች በመላክ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገውን የድንበር ስምምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀው በድብቅ የተደረገ ስለሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው በጥብቅ አሳስበናል። ይህ ጥያቄ ዛሬም ሕዝባዊ ባህሪነቱን በመያዝ በተለይ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በቅርቡ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በጐንደር ከተማ ባካሄደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ነዋሪው ሕዝብ ጥያቄውን በይፋ በማቅረብ ይህን የመሰለ የአገር ክህደት የፈጸሙ የወያኔ አመራር አባላት ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሕግም ተጠያቂ እንደሆኑ በወቅቱ ባሰማው መፈክር ግልጽ አድርጓል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገራችን የሕግ የበላይነት፤ ዴሞክራሲና እኩልነት እንዲሰፍን ያለውን ፍላጎትና የትግል ስሜት በቅርቡ በወጣት ኢትዮጵያውያን የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲና ከዛም ወዲህ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በጠሩት ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በተጨባጭ አስመስክሯል። በተለያዩ ከተሞች ነዋሪው ሕዝብ የወያኔ ከፍተኛ አሻጥርና አፈና ተቋቁሞ በነቂስ ወጥቶ ያሳየው ሕዝባዊ ቁጣና አልበገርነት፤ ለቀጣይው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችና ሕዝባዊ ትግል ያለው አነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ ነው ብለን እንገምታለን። በተለይ በጐንደር ከተማ በተደረገው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የከተማው ሕዝብ አንግቦት ከወጣውና በይፋ ካቀረበው ጥያቄዎች መካከል “የአገራችንን ለም መሬት ለሱዳን አሳልፈው የሰጡና ይህንን አሳፋሪ ተግባር ያስፈጸሙ የወያኔ ባለሥልጣናት በአገር ክህደት ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል” ሲል ያነሳው ጥያቄ በአገር ውስጥ በአደባባይ ሲጠየቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። ሟቹ አቶ መለሰ ዜናዊ ቀደም ብሎ በወያኔ የተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በሰጡት ገለፃ ለም መሬታችን ከአራሹ ኢትዮጵያውያን እጅ ተነጥቆ ለሱዳን መሰጠቱንና በተለይም በጐንደር ክፍለ ሃገር በመተማ አካባቢ በእርሻ ይተዳደሩ የነበሩ ወገኖቻችን በሱዳን ጦር ተወርረው መንደሮቻቸውና የእርሻ ተቋማቶቻቸው ተቃጥለው፤ እነርሱም በሱዳን ታጣቂዎች እጃቸው በካቴና እየታሠረ ከተወሰዱ በኋላ በሱዳን እሥር ቤት ይሰቃዩ እንደነበረ እያወቁ “አንድም ሰው አልተፈናቀለም፣ ወደ ፊትም አንድም ሰው አይፈናቀልም” በማለት የሰጡት ቃል የወያኔ ሥርዓት ምን ያህል ለአገራችን ሉዓላዊነት ደንታ እንደሌለው ያረጋገጠበት ሌላው አጋጣሚ ነበር። ዛሬ የክልሉ ሕዝብ አገር የሸጡና ኅብረተሰቡን ቁም ስቅሉን እንዲያይ ያደረጉ አጥፊዎች የፍርድ መዝገብ ይያቸው ሲል ያቀረበው ጥያቄና ያሰማው አቤቱታ ከታሪክም ሆነ ከሕግ አንፃር ሲታይ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ ነው። የሱዳን መንግሥት ተበዳይ ሆኖ የመሬት ሥጦታ ሲደረግለት፤ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ግን እንደ በዳይና ወራሪ ኃይል ተቆጥሮ በባዕዳን ሰዎች ሲሰቃይና ለመከራ መዳረጉ መቼም ቢሆን የማይሻር የታሪክ ጠባሳ ነው። በዚህ ረገድ የአገር ክህደት ወንጀል የፈጸሙት ጥቂት የወያኔ ባለሥልጣናት ቢሆኑም፤ የሥርዓቱ ተጠሪዎች በሙሉ ተጠያቂ ናችው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ እነዚሀ አገር-ከሃዲዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህንን ከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸም ቁንጮ ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ደመቀ መኮንን ሲሆን፤ እሱም ለሥርዓቱ ባሳየው ታማኝነት ዛሬ በሹመት ላይ ሹመት ተጨምሮለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኗል። ትላንት ““ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ተብሎ ለወራሪው ፋሽስት ጣሊያን በባንዳነት ላደሩ አገር-ከሃዲ ኢትዮጵያውያን የተገጠመው ግጥም ባለመታደል ሆኖ ዛሬ እኛ በዓይናችን ለማየት ችለናል። የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሊያስገነዝብ የሚወደው፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ጉዳይም ሆነ የድንበር ለም መሬቶቿን ለሱዳን አሳልፎ የሰጠውን ስምምነት የማውገዙና አስፈጻሚዎቹን ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ በአንድ ክልል ሕዝብና በአንድ ቦታ ብቻ ቀርቦ የሚያበቃ ሳይሆን በሁሉም የአገራችን ክፍል ሥርዓቱ የፈጸመውን ግፍ ለማውገዝና ለመታገል በሚጠራው ሕዝባዊ የተቃውሞ ስብሰባ ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ሊነሳና ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚገባ ነው። አዲሱ ትውልድ ከሚችለው በላይ ዕዳ ውስጥ ተነክሯል፣የዛሬው ትውልድ ኃላፊነትም ይህ መጠነ ሰፊ የሆነው የአገር ዕዳ የሚገታበት፣ አልፎ ተርፎም የተፈጸመው ውልና ሠነድ የሚሻርበትን መንገድ ከወዲሁ ከታሪክም ከሕግም አኳያ ተገቢውን ጥናት ማጥናት ነው ብለን እናምናለን። ለዚህ ነው፣ ለሱዳን የተሰጠው ከሰሜን ጐንደር እስከ ጋሞ-ጎፋ ድረስ ያለው የአገራችን ለም የድንበር መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንግቦ ከሚይዛቸው መሪ መፈክሮች መካከል አንዱ መሆን አለበት የምንለው። ለመብላት የሚኖሩ እንጂ ለመኖር የማይበሉት የወያኔ ባለሥልጣናት እነዚህን የመሰሉ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ሲነሱ ሰዎችን ማሠር ተግባራቸው ነው። ሕዝባዊ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የገቡበት የማይታወቁ አያሌ ስማዕታት አሉና። ሕዝባዊ ጥያቄ ይዞ በአደባባይ ለመብት መቆም ለወያኔ የሽብርተኝነት ተግባር ነው። በሽብርተኝነት ጥላ ሥር ደግሞ ወያኔ የሚፈጽመው የሰብአዊ መብት እረገጣና ዘግናኝ ድርጊት በዚህ ጽሑፍ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የዚህ የዛሬው ትውልድ ኃላፊነትም ኢትዮጵያ ለደሙላት፣ ለቆሰሉላትና ለተሰውላት እንጂ ላደሟት፣ ላቆሰሏትና ለገደሏት አትመችም ብሎ በጋራ መነሳትና ሕዝባችንና አገራችን ከገጠሟቸው የጥፋት ማዕበል ማዳን ነው። ይህን ታላቅ ግዴታና ኃላፊነት ካልተወጣ ደግሞ፤ በታሪክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በቆራጥ ልጆቿ ይከበራል! ድል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ! ኢትዮጵያ ለዘላለም በነፃነትና በክብር ትኑር!

No comments:

Post a Comment