Sunday, November 24, 2013

ሳኡዲ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ሰቆቃ


ሰሞኑን በህገወጥ መንገድ ሳኡዲ አረቢያ ከገቡ ብዙ ሺ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል ዓለም አቀፍ የስደተኞ ተቋም ከ350 በላይ የሚሆኑትን ወደ አገራቸው መልሷቸዋል፡፡ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በተቋሙ መጠለያ ጣቢያ ያገኘቻቸውን ሦስት ተመላሾች አነጋግራለች፡፡
“ሳኡዲ ወርቅ እየዘነበ ነው ቢሉኝ አልሰማም” አብዱ እንድሪስ
“ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት እየተሰቃዩ ናቸው” እንድሪስ መሃመድ
“አበሻ ለእነሱ ርካሽ እቃ ማለት ነው” እንድሪስ የሱፍ አብዱ እንድሪስ እባላለሁ፣ ከኮምቦልቻ ተነስቼ ከጓደኞቼ ጋር ነው የሄድኩት—መንገዳችን ጥሩ ነበር፡፡ የመን ከዛም ሳኡዲ ደረስን። ከስምንተኛ ክፍል ነው የሄድኩት..ቤተሰቦቼ ድሆች ነበሩ — የእነሱን ችግር እያየሁ መቀመጥ አላስቻለኝም፡፡
ስንት ጊዜ ቆየህ ሳኡዲ?
አስር ወር ቆይቼ ነው የመጣሁት፡፡ አምስቱን ወር በእስር ቤት፣ አራት ወር ጎዳና ተዳዳሪ ሆኜ ስንከራተት—አንድ ወር ብቻ ነው ተቀጥሬ የሰራሁ፡፡
ምን ነበር የምትሰራው?
በግ እጠብቅ ነበር፡፡ ደሞዜ ስምንት መቶ ሪያድ ነበረ፡፡ ደሞዜ እንደነገ ሆኖ እንደዛሬ ፍተሻ ሲያደርጉ አገኙኝና ወሰዱኝ፣ አምልጫቸው ጎዳና ለጎዳና ስንከራተት—መንገድ ለመንገድ ስተኛ– በመጨረሻ ምግብ እየለመንኩ መኖር ጀመርኩ፡፡ ለማኝ ነበርኩ፡፡
አራት ወር ጎዳና ተዳዳሪ ሆነህ ምግብ የሚሰጥህ ማን ነበር?
በህጋዊ መንገድ የመጡ የእኛ ሴቶች አሉ፣ ሥራ የሚሰሩ፡፡ አልፎ አልፎ ምግብ ደብቀው ይሰጡኛል፡፡ ሴቶችም ወንዶችም ብዙ ጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ፣ ብዙ እብዶችም አሉ፡፡ ቆም ብለሽ ዞር ስትይ ኢትዮጵያዊ ለማኝ፣ ጎዳና ተዳዳሪ፣ እብድ—አለ በየመንገዱ፡፡ አንዳንዴ ፖሊሶች ከመንገድ አንስተው ያስራሉ፡፡
አንተም ጎዳና ላይ ተገኝተህ ነው የታሰርከው?
አምስት ወር ሙሉ በእስር ቤት ነበርኩ፡፡ እስርቤቱ እንዴት ነበር ብለሽ እንዳትጠይቂኝ–ማስታወስ አልፈልግም፣ ያመኛል፡፡ ዱላውንና ድብደባውን..ማንጓጠጡንና ማንቋሸሹን…አልነግርሽም፡፡ ግን የሰው ዘር ናቸው? እኔ አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያኖች እኮ እስር ቤት ሁሉ ይሞታሉ፡፡ ረሃብማ ተይው፡፡ እንኳን ብቻ ለአገራችን አበቃን፡፡
ቤተሰብህ ያለህበትን ሁኔታ ያውቅ ነበር?
እንደገባሁ ደውዬ ነበር፡፡ ከዛ ግን አስር ወር ሙሉ የት እንዳለሁ — ልሙት ልዳን የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ አሁንም ዝም ብዬ ነው ተሳፍሬ የምሄደው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሳኡዲ ውስጥ ኢትዮጵያኖች እየተንገላቱ ነው ይባላል..
ድብደባ ቢሉሹ ድብደማ መሰለሽ፡፡ ዝግንን በሚል ሁኔታ ነው የሚደበድቡበት፡፡ ዱላ እኮ መፈንከት ብቻ ሳይሆን የደምስርሽ እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡ ሽባ ነው የሚያደርጉት—.በጣም ይጠሉናል፡፡
ከዚህ በኋላ ተመልሰህ አትሄድም?
እንኳንም መጣሁ፡፡ አላህ ለአገሬ ምድር አበቃኝ፡፡ አሁን አገሬ ስገባ የምሰራውን ስራ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ ለእኔ ብቻ ሳሆን ለጓደኞቼም ትምህርት ነው የምሆነው፡፡ ይጠቅመኛል ያለ ይከተለኛል፣ ያለዚያ የራሱ ጉዳይ፡፡
ምን ልትሰራ አሰብክ?
በንግድም ሆነ በሚያዋጣኝ ወጥሬ ነው የምሰራው፡፡ ሳኡዲ አረቢያ ወርቅ እየዘነበ ነው ቢሉኝ — ከአሁን በኋላ ስሙን እንኳን መስማት አልፈልግም፡፡ የቅጣታቸው አከፋፍ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ… አውራ ጣትና አውራ ጣትን በገመድ ያስሩና ርቆ ከተሰቀለ ባላ ላይ ያቆማሉ፡፡ ከስር የተቆመበትን ወንበር ጎትተው ሲጥሉት ..ስቃዩና ሰቆቃው አይጣል ነው፡፡ ስንቱ የጀርባ ህመምተኛ፣ ስንቱ መሽናት አቅቶት እየተንፏቀቀ እንዳለ ብታይ …አየሽው /ክብዱን እያሳኝ ለምጥ/ ይሄ ለብዙ ጊዜ ያሰቃየኝ ቁስል ነው ደብድበውኝ፡፡ የእኔ ጓደኛ ተደብድቦ ተደብድቦ በሽተኛ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መለሱት—በተመለሰ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሞተ። መቼም ብዙ መከራ አሳለፍን፡፡

No comments:

Post a Comment