Tuesday, July 30, 2013

Freedom4Ethiopian

ሰበር ዜና == በጂንካ ነዋሪዎች ለእሁዱ የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀታቸውን ገለፁ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሚልዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መሪ ቃል እያከናወነ በሚገኘው የህዝባዊ ንቅናቄ መርሃ ግብር መሰረት ሐምሌ 28 ቀን 2005 በጂንካ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማከናወን በበራሪ ወረቀትና ፖስተሮችን በመለጠፍ ህዝቡን ሲያነቃቃ ቆይቷል፡፡ የጂንካና የአካባቢው ነዋሪዎችም በዕለቱ አደባባይ በመውጣት የታፈነ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ለአንድነት የጂንካ አመራሮችና አባላት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የጂንካ ከተማ ከንቲባ ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ከአንድነት የጂንካ ጽ/ቤት ለሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ ክፍል ገቢ የተደረገው ደብዳቤ ማሳወቅ ሳይሆን ሊፈቀድልን ይገባል በሚል መልኩ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም የአንድነት ተወካዮች ህገ መንግስቱ አሳውቁ እንጂ አስፈቅዱ የማይል በመሆኑ የደብዳቤውን ይዘት አንለውጥም በሚለው አቋማቸው ፀንተው በመግለጽ ወደ ቅስቀሳ ስራቸው ገብተዋል፡፡ የክልሉ የፖሊስ ሃይል በበኩሉ ሰላማዊ ሰልፉን ፓርቲው ማድረግ እንደሚችል በቃል በመግለፅ ነገር ግን ‹‹በዕለቱ ለሚፈጠረው ማናቸውም ነገር ሃላፊነት እንወስዳለን በማለት ፈርሙ ›› በማለት ተገቢ ያልሆነ ቅድመ ሁኔታ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ህዝብ ለሚያደርገው የአደባባይ ሰልፍ ፖሊስ ተገቢውን ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት የሚገነዘቡት የአንድነት የጂንካ አባላት ቅድመ ሁኔታው እነርሱን እንደማይመለከት በመግለጽ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ አስረድተዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደር በ22/07/2005 በደብዳቤ ቁጥር 417/05 ለአንድነት የጂንካ አመራሮች በጻፈው ደብዳቤ ‹‹ነገ ጠዋት ቢሮ ድረስ በመምጣት ልታደርጉት ባሰባችሁት ሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ መነጋገር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ተወካዮችን እንድትልኩ ይሁን›› በማለት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ የአንድነት የጂንካ አመራሮች በዞኑ አስተዳደር ቢሮ በመገኘትም ስለሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ አላማዎች ለማስረዳትና ሰላማዊ ትግሉ የሚጠይቀውን ማናቸውም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ለአካባቢው ባለስልጣነት ለማስገንዘብ የነገዋን ጸሀይ መጠባበቅ ጀምረዋል፡፡ source: freedom4ethiopian.wordpress.com

No comments:

Post a Comment