Monday, January 12, 2015

የአርቲስት አስቴር በዳኔና ሳሞራ ፍጥጫ በደደቢት በረሃ


Aster Bedae
…አርቲስት አስቴር በዳኔ ከተቀመጠችበት ወደፊት ወጥታ ማይኩን ስትጨብጥ ፍርኃት ቢጤ እንደወረራት ከመጀመሪያው ያስታውቃል፡፡ ‹‹በጣም ነው የሚያስፈራው፤›› በማለት የጀመረችውን አስተያየቷን የያዘችውን ማስታወሻ እያነበበች አስተያየት መስጠት ቀጠለች፡፡
‹‹ይህንን ዕድል ተመቻችቶልን በቴሌቪዥን ስናየው የኖርነው ታሪክ ለማየት ስለቻለን እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በፊት የነበረኝ ያልተጨበጠ አመለካከት በመረጃ የተደገፈ ሆኗል፤›› በማለት ሐሳቧን ቀጠለች፡፡ ‹‹እውነትን መናገር እወዳለሁ፡፡ የሐሳብ ነፃነትም አለ፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ ያሰኘች ሲሆን፣ በሒደትም የፍርኃቷ መጠን እየቀነስ የመጣ ይመስላል፡፡
አርቲስት አስቴር በዳኔ
‹‹ዛሬ ባልናገረው የሚቆጨኝ የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ በጣም ከባድ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በጆሮ ስሰማው ደርግ ተደምስሶ ታጋይ እንዲህ ሆኖ ሲባል ከሁለቱም ወገን የተሰዉት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ የሞቱት፣ እግራቸው የተቆረጠ፣ ዓይናቸው የጠፋ ስላሉ ለሁለቱም ‹ጠላት› የሚለው ቃል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የወንድማማቾች ደም በመፍሰሱ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ሄደን ስናይ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የጦርነትና የትግል ታሪክ ዘመኑ የፈጠረው ነው፡፡ በወቅቱ መንግሥታዊ ለውጥ ለማምጣት የትጥቅ ትግሉ አማራጭ አልነበረውም፡፡ አሁንስ?›› አርቲስት አስቴር ትንፋሿን ዋጥ በማድረግ ቀጠለች፡፡
‹‹የትግሉ ዋና ሐሳብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ ለማምጣት ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የሥርዓት ለውጥ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ እንዲሆን ነበር ያ ሁሉ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለው፡፡ አሁን ላይ ሲታሰብ የሚመጣው ግንቦት ላይ 24 ዓመት የሚሆነው ሥልጣን ላይ ያለው አንድ ፓርቲ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ላይ ልባችሁ ምን ይላል? ያኔ ለሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ስትታገሉ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ ለውጥ እንዲደረግ ነበር፡፡ አይለደም?›› በማለት ጠየቀች፡፡
‹‹በእርግጥ የድሮን አስተሳሰብ መናፈቅ አዲስ አስተሳሰብ ለመቀበል ይከብዳል፡፡ አሁን ዝም ብዬ ሳስበው ራሱ ተቃዋሚ የሚለው ቃል ራሱ ጥሩ አይደለም፡፡ ተፎካካሪ ቢባል፡፡ አዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ያለው ተተኪ መሪ ሊፈጠር አይችልም የሚል አቋም ነው ያላችሁ?›› በማለት ሐሳቧን ያልቋጨችው አርቲስት አስቴር፣ ሐሳቧ በብዙዎች ተጠብቆ የነበረ አይመስልም፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› የሚለው የመጨረሻውን ቃል እስክትናገር ከአጠገቧ የተቀመጡ ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት አንጋፋ ታጋዮች ጥያቄው እስኪያልቅ የተጨነቁ ይመስላል፡፡ እርስ በርስ አየት ተደራርገው የተለዋወጡት ፈገግታ ጥያቄውን የጠበቁት እንዳልሆነ ያሳብቃል፡፡ በእርግጥም በምርጫ ዋዜማ ሆነው ለጥያቄው ምን ተብሎ ምላሽ እንደሚሰጥ ሳያስጨንቃቸው አልቀረም፡፡
‹‹እውነት መናገር እውዳለሁ›› በሚል የጀመረችው ፍርኃት እየፈጠረባትም ቢመስል የመጨረሻ ማጠናቀቂያ ሐሳቧ እንዲህ ነበር የሚለው፡፡ ‹‹ምክንያቱም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፡፡ ‘So, next time’ ምን ያህል አዲስ ታሪክ አዲስ አስተሳሰብ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተለውጦ እናያለን?›› የሚለው ፈራ ተባ እያለች የጨረሰችውን ጥያቄ ‹‹ውርድ ከራሴ›› ይመስል ድምጿ እየተቆራረጠ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብላ፣ ‹‹እናንተስ በምርጫ ትወርዱ ይሆን?›› ብላ ነበር ጥያቄዋን የቋጨችው፡፡
አቶ በረከት ስምኦን ሁለት እጆቻቸውን ወደፊት ወስደው እንደማፍተልተል ሲያደርጉ፣ ሌሎች ብዙዎቹ አንጋፋ አመራሮች በግርምት ጉንጫቸውን ደገፍ አድርገው ይዘው ቀታይተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment