Thursday, January 1, 2015

“በሐውዜን ድብደባ፤ የእሥራኤል እጅ አለበት” አቦይ ስብሃት ነጋ

 "Israel played role in Hawzen bombing in Ethiopia" Sebhat Nega

በ  

ከ26 ዓመታት በፊት የደርግ መንግሥት በትግራይ ክልል በሐውዜን ሕዝብ ላይ ያካሄደው የአውሮፕላን ድብደባ በስተጀርባ የእሥራኤል መንግሥት እጅ እንዳለበት የቀድሞ የህወሓት ሊቀመንበር አቶ ስብሃት ነጋ ይፋ አደረጉ። 
አቶ ስብሃት ይህን የገለፁት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የደርግ 604 ኮር የተደመሰሰበትን የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ አስመልክቶ ሰሞኑን በሽሬ ከተማ በተሰናዳ የውይይት መድረክ ላይ ነው።
     አቦይ ስብሃት ሲያስረዱ፣ “የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምን ተከትሎ ታላቋ ሶቪየት ሕብረት መፈራረስ ጀመረች። ይህን ክስተት ተከትሎ ሶቪየት ሕብረት ከኢትዮጵያ እየወጣች መጣች። በእሷ እግር የተተካውም የሩሲያ ፌዴሬሽን ለደርግ አገዛዝ ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረውን ወታደራዊ እርዳታ አቋረጠ። ይህን ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ዳይናሚዝም ተከትሎ አሜሪካ መራሹ የምዕራብ ዓለም እና የእሥራኤል መንግስት ከደርግ ጋር ወዳጅ ሆኑ። የደርግ አገዛዝን መውደቅን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የጂኦ-ፖለቲካል ኃይል አሰላለፍ በመፍራት የምዕራቡ ዓለምና እሥራኤል  ደርግን ወዳጅ አድርገው በእኛ የትግል እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ እርምጃዎች መውሰድ ጀመሩ” ብለዋል።
     አያይዘውም፣ “በወቅቱ ሕወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅሙ እየጠነከረ እየመጣ በመሆኑ አሜሪካና እሥራኤል ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ገብተዋል። የአዲስ አበባው መንግስት ወዳጅ ስለሆኑ እንዴት ከተጀመረው የትጥቅ ትግል ሊያድኑት እንደሚችሉ ብዙ መንገዶችን ሞክረዋል። በጊዜው ደርግን ለማትረፍ ያልሞከረ የምዕራብ ሀገር አልነበረም። ሁሉም የሚችለውን አድርጓል። አሜሪካ ለማደራደር ስትሞክር እሥራኤል ግን የተለየ ሚና ወሰደች” ሲሉ ወንጅለዋል።
     “አሜሪካ አንዴ ወደ ሮማ ሌላ ጊዜ ወደ ለንደን እንድንመጣ ጠራችን።  ሮማ ላይ ጂሚ ካርተር አስጠርቶን የነበረ ቢሆንም፣ የደርግ ልዑካን ቡድን እናንተ ስለኢትዮጵያ ምን ያገባችኋል አሉን። ወደ ለንደን ተጠርተን ስንሄድ ግን ሁሉን ነገር ስለጨረስን ደርግን ጥለን ነበር” ብለዋል።
     እስራኤል ግን ወደ ሮማ ከመሄዳችን በፊት፣ ደርግን በጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ጀምራለች። ደርግ የታጠቀውን የክላስተር ቦምብ እ.ኤ.አ ጁን 22 ቀን 1988 ሐውዜን በገበያ ቀን ህዝቡ ላይ አዘነበው። በጥቃቱም ከ2ሺ 500 በላይ ህዝብ ማለቁን ተናግረዋል። አያይዘውም፤ “ይህ ሁሉ የህዝብ ዕልቂት በእሥራኤል አስታጣቂነት የተፈጸመ ነበር” ሲሉ አቦይ ስብሃት ለተሰብሳቢው በሃዘን ተውጠው አስረድተዋል።
     የቀድሞ የደርግ መንግሥት ርዕሰ ብሔር የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ወደ ዙምባቡዌ የሸሹት በምዕራብ ሀገሮች ድጋፍ መሆኑ ሲነገር ነበር። ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሞት ፍርድ ቢተላለፍባቸውም አንዳቸውም የምዕራቡ ሀገራት የዙምባቡዌ መንግስት አሳልፎ እንዲሰጥ ግፊት አድርገው አያውቁም።

No comments:

Post a Comment