Thursday, January 1, 2015

አንድነትና መኢአድ በምርጫ ዋዜማ ከምርጫ ቦርድ ጋር የጀመሩት ውዝግብ

-- ምርጫ ቦርድ ምን ይላል? 
 ልጅ  ግሩም (ከ ሪፖርተር ጋዜጣ)  
ከእነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ጋር የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
‹‹እነኚህ ሁለት ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን ለጊዜው በሆደ ሰፊነት እንዲያስገቡ የተደረገ ቢሆንም፣ በየፓርቲዎቹ የውስጥ ጉዳይ ምክንያት በአመራሮች መካከል መከፋፈል በመፈጠሩ የፓርቲዎቹ ሕጋዊና ትክክለኛ አመራሮች ያለመታወቅ ችግር ነበር፤›› በማለት ይገልጻል፡፡
በመኢአድ በኩል በቦርዱ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ የውስጥ ዴሞክራሲ እጦት ምክንያት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ አዋጁንና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ባላከበረ መንገድ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ ለቦርዱ ሪፖርት በማድረግ ማፅደቅ ያለመቻል፣ በየጊዜው ደንብ በማሻሻል አመራር በመቀየር ተመርጠናል የሚሉ አካላት መከሰታቸው ይጠቀሳል፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ችግር ከመቅረቡም በላይ፣ ቦርዱ ትክክለኛው የመኢአድ አመራር ማን መሆኑን ለመለየት ግራ ተጋብቻለሁ ይላል፡፡
‹‹የመኢአድ ፕሬዚዳንት ማን ነው? አቶ አበባው መሀሪ? ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል? ወይስ አቶ ማሙሸት አማረ?›› በማለት ምርጫ ቦርድ ይጠይቃል፡፡ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ቦርዱ በማያውቀውና ዕውቅና ባልሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻሉን፣ አሻሻልኩ የሚለውን ደንብም ለሰባት ወራት ለቦርዱ ሪፖርት ሳያደርግ ሚስጥር አድርጎ አስቀምጧል፤›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ይኼንኑ ደንብ በመጠቀም ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን (የፓርቲውን ፕሬዚዳንት) ከሥልጣን አሰናብተዋል፡፡ በምትካቸውም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብም ሆነ በምርጫ አዋጁ በጠቅላላ ጉባዔ መመረጥ ያለበትን ወደጎን በመተው በብሔራዊ ምክር ቤት እንዲመረጥ አድርገዋል፤›› ይላል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ አሥራት ጣሴ:-
‹‹ምርጫ ቦርድ ያወጣው መግለጫ በጣም የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ታኅሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደን በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፕሬዚዳንት ምርጫና የብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫ ተከናውኗል፤›› ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ መሠረትም እርግጥ ነው ሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው ለምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባዔ የቃለ ጉባዔ ሰነድ ያስገነባው፤›› በማለት ለሰባት ወራት ያህል መዘግየቱን አምነዋል፡፡
መኢአድ :-
የመኢአድ አመራር ማን እንደሆነ መለየት መቸገሩን ለሚገልጸው የቦርዱ ጥያቄ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ያውቀናል፡፡ እንደሚያውቀንም ማረጋገጫው ጠቅላላ ጉባዔአችንን በሁለት ታዛቢዎቹ አማካይነት መታዘቡንና ከዚህም በላይ የምርጫ ምልክታችሁን በአስቸኳይ እንድታስገቡ የሚል ደብዳቤ መላኩ ነው፤›› በማለት ቦርዱ ያወጣው መግለጫ እውነታን መሠረት ያላደረገና መራጩን ኅብረተሰብ ውዥንብር ውስጥ የሚከት ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment