Thursday, January 1, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ከገንዘብ ክፍፍል ቀመሩ በፊት ምርጫው ፍትሓዊ እንዲሆን መወያየት እንደሚያስፈልግ አሳሰበ

• ተወካዩ ስብሰባውን ረግጦ ወጥቷል
(ነገረ ኢትዮጵያ)
ምርጫ ቦርድ ዛሬ ታህሳስ 22/2007 ዓ.ም ለመጭው 2007 ዓ.ም ምርጫ የገንዘብ ክፍፍል ቀመር ላይ ለመወያየት በጠራው ስብሰባ ሰማያዊ ፓርቲ ከገንዘብ ክፍፍል ቀመሩ በፊት ምርጫው ፍትሓዊና ነጻ ለማድረግ መወያየት እንደሚቀድም ማሳሰቡን ፓርቲውን ወክሎ በስብሰባው የተገኘው አቶ ጌታነህ ባልቻ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ትብብሩን የመሰረቱት ፓርቲዎች ምርጫው ፍትሓዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ትግል እያደረጉ እንደሆነ ያስታወሰው አቶ ጌታነህ፤ ታህሳስ 12/2007 ዓ.ም የህዝብ ታዛቢዎችን ለመምረጥ በተደገው ሂደት የተመረጡት የኢህአዴግ አባላት መሆናቸው፣ ከተመረጡት መካከል የሞቱ ሰዎች ስምም መካተቱ፤ እንዲሁም በህመምና በተለያዩ ምክንያቶች ለመታዘብ የማይችሉ የሚገኙበት መሆኑ፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመታዘብ ልምድ ያላቸው ተቋማት ራሳቸውን ማግለላቸው ምርጫው ከአሁኑ ፍትሓዊ እንዳልሆነ እንደሚያሳይና ከገንዘብ ክፍፍሉ በፊት ምርጫውን ፍትሓዊ ለማድረግ መወያየት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የገንዘብ ክፍፍል ቀመር መሰረት 10 በመቶ ለሴቶች፣ 10 በመቶ ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል፣ 25 በመቶ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት እጩ፣ 55 በፓርላማና በክልል ምክርት ቤት ባላቸው መቀመጫ እንደሚያከፋፍል የተቀመጠ ሲሆን ይህም 99.6 በመቶ ፓርላማ እንዲሁም የክልል ምክርቤትን የተቆጣጠረው፣ ከዚህም በተጨማሪ 547 ተወዳዳሪዎችን ለሚያቀርበው ኢህአዴግ የሚጠቅም ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን ወክሎ በምርጫ ቦርድ ስብሰባ የተገኘው የፓርቲው እቅድና ስትራቴጅ ኃላፊ የሆነው አቶ ጌታነህ ባልቻ ‹‹ከገንዘብ ክፍፍሉ በፊት ምርጫው ፍትሓዊ እንዲሆን መወያየት አለብን›› በሚል ያቀረበው ሀሳብ በምርጫ ቦርድ ተወካዮች ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

No comments:

Post a Comment