ታህሳስ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጌዲዮ ዞን በሚገኙ 9 ወረዳዎች ውስጥ በዚህ ወር ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ረሀብ በመከሰቱ የዞኑ የአገር ሽማግሌዎች ህዝቡ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመግለጽ የተፈራረሙበትን ደብዳቤ ዛሬ ለዞኑ መስተዳድር አስገብተዋል። በከፍተኛ ደረጃ ተደናገጡት የዞኑ ባለስልጣናት መረጃው ይፋ እንዳይወጣ ለማድረግ ዛሬ ቀኑን ሙሉ በስብሰባ ተወጥረው መዋላቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአገር ሽማግሌዎቹ የገጠሩ ህብረተሰብ በከፍተኛ ሁኔታ በመራቡ መንግስት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ ” የገጠሩ ህዝብ በረሀብ የተነሳ እየፈለሰ ወደ ከተማ እየተሰደደ ነው፣ እናንተ ምን እየሰራችሁ ነው ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በዚህ ወር የጌዲዮ ዞን ነዋሪዎች ከፍተኛ ቡና በማምረት የእህል ሸመታ የሚያካሂዱበት ነበር የሚሉት ምንጮች፣ አሁን ግን ሁኔታው ተቀይሮ የህዝቡን ህይወት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የጣለ ረሀብ ተከስቷል ብለዋል።
በጌዲዮ ዞን ከ900 ሺ በላይ ህዝብ የሚኖር ሲሆን አብዛኛው ህዝብ ገቢውን የሚያገኘው ከቡና ነው።
በመላ አገሪቱ በሚታየው የኑሮ ውድነት ህዝቡ ምሬቱን እየገለጸ ነው። የዞኑን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በሌላ ዜና ደግሞ በሸዋ ሮቢት በርካታ መምህራን ስራቸውን እየለቀቁ ነው። መምህራኑ ስራቸውን የሚለቁት ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ መሆኑን መምህራን ተናግረዋል። መምህራኑ ወደ ዋና ከተሞችና ወደ ውጭ አገር እየሄዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
No comments:
Post a Comment