Saturday, December 28, 2013

ይድረስለኢትዮጵያመለዮለባሾች (ለፖሊስሠራዊት፤ለፌድራልፖሊስና ለጦርኃይልሠራዊትዓባላት)


December 28/2013


በገብረክርስቶስ ዓባይ ታህሣሥ 2006 ዓ/ም

ከታሪክ እንድምንገነዘበው የአንድ ሀገር ደኅንነት ወይም ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው፤ ዳር ድንበሯ ተከብሮ ፤በውስጧ የሚኖሩ ሕዝቦች በሰላም ላይ የተመሠረተ፤  ቀልጣፋ ዕድገትና ብልጽግና ያለምንም ሥጋትና መሸማቀቅ ማከናወን ሲችሉ፤ የዜጎች ኅልውና ተጠብቆ፤ የሕግ የበላይነት ነግሦ፤ ያለማንም ጣልቃገብነትና ያልተንዛዛ የፍትሕ ሥርዓት ማስፈን ሲቻል ነው።

ለዚህ ዓይነተኛና ቁልፍ የሆነ ተግባር የመለዮ ለባሹ ተሳትፎ ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ይሁን እንጅ መለዮ ለባሹ የተማረም ይሁን ያልተማረ የንቃተ ኅሊናው ደረጃ ግን ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ውጤት ወሳኝ ሚና መጫወት እንዲችል ያደርገዋል።

በመሠረቱ መለዮ ለባሹ የማን ወገን ነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ እጅግ በማያሻማ ሁኔታ የሕዝብ የሚል መልስ እናገኛለን። ምክንያቱም በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ሁሉም መለዮ ለባሽ  የገባው ቃል ኪዳን ለአገሩና ለወገኑ  ደኅንነት በሙሉ ኃይሉና ዕውቀቱ መሥራት ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ  ደግሞ እስከ ሞት የሚደርስ የሕይወት መስዋዕትነት እከፍላለሁ በማለት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ቅጥሩ በውክልና ማለትም በወቅቱ በሥልጣን ላይ ባሉ ኃላፊዎች ቢፈጸምም ወርኃዊ ደመወዝና ተጓዳኝ ጥቅማጥቅሞችን የሚከፍለው ወገኑ (ሕዝቡ) መሆኑን መለዮ ለባሹ ጠንቅቆ መረዳት ይገባዋል።

በሦስተኛ ደረጃ መጠቀስ ያለበት ሹመኛ ጥፋት ሠርቶ ይሻራል፤ ዕድገት አግኝቶ ይዛወራል፤ በሞትም ሊለይ ይችላል ወይም ደግሞ በመንግስት ለውጥ የተነሣ የኃላፊነት ቦታውን ሊያጣ ይችላል። ሕዝብ ግን ትውልዱን እያደሰ እንደሚቀጥል እንገነዘባለን።
ስለሆነም መለዮ ለባሹ ምንጊዜም ከሕዝብ አብራክ የተገኘ እንደመሆኑ መጠን የሕዝብ አካል ነውና ለሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት ጥብቅና የመቆም ግዴታ አለበት። ሕዝብ በተለያዬ ምክንያት ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ያንንም ተከትሎ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ትኩረት ለማግኘት ሲል ሰብሰብ ብሎ ጥያቄዎቹንና አቤቱታዎቹን በሰላማዊ ሰልፍ በኅብረት ሆኖ ለመንግሥት እንዲያቀርብ የሚያስገድድ ሁኔታ ይገጥመው ይሆናል። ነገር ግን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ግለሰቦች(ኃላፊዎች) የሕዝቡን ጥያቄ አዳምጠው መፍትሔ መፈለግ ሲገባቸው  በተለያዬ ስንካላ ምክንያት የሕዝቡን ጥያቄና ድምፅ ለማፈን፤ አልፎ ተርፎም በድንገት ተነስተው መለዮ ለባሹን በወገኑ ላይ አስከፊና አጸያፊ እርምጃ እንዲወስድ መመሪያ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ መለዮ ለባሹ የቃል ብቻ ሳይሆን የጽሑፍ ማስረጃ መያዝ ይጠበቅበታል።

ያንንም ካደረገ በኋላ የደረሰውን ትዕዛዝና የሕዝቡን ጥያቄ አግባብነት ከሕገመንግሥቱ ጋር ማገናዘብ ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱ የሕዝቡን ጥያቄ አግባብነት የሚፈቅድ ከሆነ ጉዳዩ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ራሱን መለዮ ለባሹንም ጭምር የሚጠቅምና የሚያቅፍ ስለሚሆን ሰላማዊ ሰልፉ በሥርዓት እንዲመራና እንዲጠናቀቅ ድጋፍ መስጠት ይኖርበታል እንጅ ያንን የሚያደናቀፍ እርምጃ መውሰድ የለበትም።
ለምሳሌም ያህል በቅርቡ የተፈጸመውን እንጥቀስ፡ አገራችን ኢትዮጵያ በሦስት ሺህ ዘመን ታሪኳ እንዳሁኑ መንግሥት ጊዜ እጅግ ተዋርዳና ተደፍራ አታውቅም።

የሳዑዲ አረብያ ሕዝቦች ቀደም ሲል ከ604-607 ዓ/ም የመጀመሪያዎቹ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከነብዩ መሐመድ በተነገራቸው መመሪያ መሠረት ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ተሰደው በመምጣት በሰላም የመኖራቸውን ሁኔታ ታሪክ መዝግቦት ይገኛል። የሳዑዲ ሕዝቦች እጅግ በጣም ድሀዎች ነበሩ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሰደው በአገራችን ይኖሩ ነበር። በተለይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ 1967 ዓ/ም ድረስ አዲስ አበባን ጨምሮ  በተለያዩ የኢትዮጵያ ጥቃቅን ከተሞች ሳይቀር የንግድ ሡቅና ሻይ ቤት ከፍተው፤እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እየሠሩ በሰላም ሲኖሩ ቆይተው እንደ ዕድል ሆኖ በአገራቸው በሳዑዲ አረብያ የነዳጅ ዘይት በገፍ መውጣት ሲጀምርና፤ በአንድ ተራራ የወርቅ ማዕድን ክምችት መገኘትን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። በዚህ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ጊዜ የደረሰባቸው ወከባም ሆነ እንግልት አልነበረም።
መቼም ዓለም ተለዋዋጭና ተገለባባጭ ናትና ሁኔታው ተቀይሮ፤ አሁን ባለው ዘረኛ የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን፤ ወንዱ ለአሽከርነት፤ ሴቷ ለግርድና ወደ ሳዑዲ አረብያ ተሰደዱ። የኢትዮጵያ መንግሥትም በእነዚህ ወገኖቻችን አማካኝነት ወደ አገራችን የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ስለጣመው በረጅሙ ታሪካችን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ፤ እኛን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ባነጋገረ መልኩ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፤ ለዘመናዊ ባርነት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርሞ በቀን 1500 በወር 45000 ወገኖቹን በይፋ ሲልክ መቆየቱ ይታወቃል።

ሆኖም መንግሥት ለውጭ ምንዛሬ ማግኛ ብሎ የሸጣቸውን ወገኖች የሰብአዊ መብታቸውንና ደኅንነታቸውን ተከታትሎ ለማስከበር ጥረት ለማድረግ ባለመሞከሩ በዘመናችን ሊታሰብ የማይችል እጅግ በጣም የሚዘገንንና ስሜትን የሚሰቀጥጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ዓለም አቀፍ የሆነው የሰብአዊ መብታቸው አልተከበረላቸውም።

ከዚህም የተነሳ በሳዑዲ አረብያ ያሉ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ድምፅ ሲያሰሙ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የወያኔው መንግሥት ዓይኔን ግምባር ያድርገው፤ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ጸጥ አለ። በዚህ ጊዜ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና የወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ በሆነው የኢሳት ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ዜናው ተላለፈ።

ወዲያውኑ፤ በዚሁ ለመንግሥትነት ብቃት በሌለው ዘረኛ የወያኔ አስተዳደር፤ በተለያየ ምክንያት እየተገፉ በዓለም ዙሪያ ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ የወገኖቻቸውን እሮሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር፤ የስደተኞች ድርጅትና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንዲያውቁት በሰላማዊ ሠልፍ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በቅብብሎሽ ተስታጋባ።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ የሳዑዲ ዓረብያ መንግሥት በስደትኞች ወገኖቻችን እያደረሰባቸው ያለውን መከራና ሥቃይ በዩ ቲዩብ፤ በምስል በታገዘ የድረ ገጽ ዘገባዎችና በተዕይንተ ሕዝብ በመላው ዓለም አካሂደዋል። ጥቂቶችን ለመጥቀስ በአሜሪካ በብዙ እስቴቶች፤ በካናዳም እንዲሁ፤ በእንግሊዝ ለንድን፤ ከአውሮፓ በስዊድን ስቶክሆልም፤ በኖርዌይ ኦስሎ፤ በፊንላንድ፤ በአምስተርዳም፤ በኮፐንሀገን፤ በፓሪስ፤በጀርመን፤ በስዊዘርላንድ፤ በብራሰልስ፤ በሮም፤በእሥራኤል፤በደቡብ አፍሪካ፤ በአውስትራሊያ፤በደቡብ ኮሪያ፤በቶክዮ ጃፓን ባጭሩ ኢትዮጵያውያን በተሰደዱበት የዓለማችን ክፍል በሙሉ ሰላማዊ ሠልፍ ተካሄዷል።

በአገር ውስጥም በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ቢሞከርም በመንግሥት ታጣቂዎች ድብደባና ወከባ እንዲበተን ተደርጓል። እዚህ ላይ የመንግሥት ታጣቂዎች የተበሉት እነማን ናቸው?
ከልዩ ዓለም የመጡ? ወይስ ከብረትና ከመሳሰሉት የተገጣጠሙ፤ በራሳቸው አእምሮ የሌላቸውና ሰው ሠራሽ አእምሮ (artificial intelligence)የተገጠመላቸው ሮቦቶች? ይህንን መመለስ ያለባቸው፤ በወቅቱ ግዳጅ ተሰጥቶአቸው ትዕዛዛቸውን ተቀብለው እንደወረደ የተገበሩት መሆን ይገባቸዋል።

በመሠረቱ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ይህንን መሰል ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ትዕዛዝ ተቀባዩን ክፍል እንዴት ቢንቀው እንደሆን በትክክል መግለጽ ይከብዳል። ምክንያቱም ጉዳዩ የሕዝባችንን ክብርና የአገራችንን ሉዓላዊነት የሚመለከት እንደመሆኑ መጠን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውንና የሁኔታው ተካፋይ በመሆን ጥብቅና መቆም የሚገባውን አካል ተቃዋሚ እንዲሆን ለማድረግ መሞከር እጅግ በጣም ከባድ ነውና።

አንደኛ በስደት ላይ ሆነው ሥቃይና መከራ እየተቀበሉ ያሉት ወገኖቹ፤ በሁለተኛ ደረጃ በወገኖቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው ይህ አስከፊ መከራና ሰቆቃ እንዲቆምላቸው በሠላማዊ ሠልፍ የሚገኙትም እህቶቹና ወንድሞቹ ሆነው እያለ፤ እርሱም እብሮ መሳተፍ ሲገባው፤ ሂዱና ሠላማዊ ሰልፉን አስቁሙ ተብሎ ሲታዘዝ አሜን ብሎ ሄዶ ለራሱ ክብር ጭምር የተሰለፉ ወገኖቹን በዱላ የሚቀጠቅጥ፤ ይሄ ከሰባዊነት በእጅጉ የወረደ ሮቦት አልያም ደግሞ ውሻ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ለዚህ ተግባር ለመታዘዝ መታሰቡ ከፍተኛ ንቀት ሲሆን ከዚህ የበለጠ ውርደት የለም። በሁለተኛ ደረጃ በራስህ ላይ ዝመት ሲባል እሺ ብሎ የሚቀበል ይሄ በቁሙ የሞተ ጎፍላ፤ አልያም ሰሎግ ውሻ ነው። ወያኔዎች ከናዚ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ መንግሥት የቀዱትን ወንድምህን ግደል ብትባል እንኳ  ትዕዛዝክን ከፈጸምክ በኋላለምን ብለህ ጠይቅ በማለት መለዮ ለባሹን እንደሚያሠለጥኑ ይታወቃል፡፡ ሙያ በልብ ነው እንዲሉ በሥልጠናው ወቅት ዝም ቢባልም በተግባር ጊዜ ግን ማን በቅድሚያ እርምጃ እንደሚወሰድበት ግልጽ ነው። እንደኔ ያን መሰል ትዕዛዝ በንቀት ያዘዘኝን ባለሥልጣን በፍጹም አልምረውም፤ ደረቱን እሰነጥቀዋለሁ እንጂ ወንድሜን ግን በክፉ ዓይን እንኳ አላየውም። መከጀሉ ራሡ ትልቅ ውርደት ነው። ከዚህ የበለጠ ሞት ከየት ይመጣል? ተዋርዶና ተንቆ ከመሞት  ግን በክብር መሞት ሺህ ጊዜ እንደሚበልጥ ማስተዋል ያስፈልጋል።

ይኼ ምን ይላል የጎበዝ ገራም፤
ሲያኩት ይቆማል እንደ ጎፍላ ላም።
የሚሉት አበው እንዲህ ያለውን ነፈዝ ነው።   እንዲህ ያለው መለዮ ለባሽ ሚስትህን ለዛሬ አውሰኝ ቢለው አለቃው እሺ ብሎ ሌላ ሰው ሳይቀድመው ባለቤቱን ወስዶ የሚያስረክብ ነው። ወያኔ የሕዝብን አእምሮ እንዴት እንደሚጫወትበት ከዚህ መረዳት ይቻላል። ራሱ ያወጣውን ሕግ እንኳ የማያከብር አምባ ገነን ሥርዓት ነው።

እንደሠይጣን ከፋፍሎ ካልሆነ አስማምቶና አፋቅሮ ማስተዳደር አይሆንለትም። የአገርን ሉዓላዊነት ማዋረድና ሰባዊ ክብርን ማርከስ ያስደስተዋል።
ለመሆኑ እንዲህ ያለው መለዮ ለባሽ የአገርን  ዳር ድንበር ያስከብራል ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ በፍጹም አይታሰብም ነው። ለነገሩ ይህ አባባል እውነት ለመሆኑ እሩቅ አያስኬድም፤ መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። በጀግኖች አባቶቻችን ደም ለዘመናት ታፍራና ተከብራ የቆየችው ሀገራችን በዘረኛው የወያኔ  የአስተዳደር ዘመን ጊዜ በአሁኑ ሰዓት  በምዕራብ ጎንደር፤ ጎጃም፤ ወለጋና ኢሉባቦር ድንበር ከአንድ ሺህ ኪሎሜትር በላይ ለም መሬት፤ ኃላፊነትን ባላስጠበቀ መልኩና ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ  በተለይም ድንበሩን በግልጽ የሚያውቁት የአካባቢው ነዋሪዎች ሳይመክሩበት፤ በጓዳ በኩል ለሱዳን ለመስጠት ላይ ታች ሲባል እያየና እየሰማ ዝም ብሎ የሚመለከተውን መለዮ ለባሽ፤ ለማን እንደቆመ እንኳ የማያውቅ፤ ከእንስሳ በታች አድርገው ቆጥረውታል። ይሄም ሌላው ሞት ነው።

በግልጽና በስውር በሕዝብ ላይ ሲፈጽሙት በቆዩት ሠይጣናዊ ተንኮል የተነሳ በደም የተበከለ እጃቸውን ሳያጸዱ፤ ለንስሐ ሞት እንኳ ሳይበቁ እስከ ሐጢያታቸው በሰማያዊ ፍርድ በድንገት የተቀሠፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ለመሆኑ የተቀበሩት የት ነው?ቅድስት ሥላሴ እንዳልሆነ ሹክሹክታዎች በሠፊው ይወራሉ ቀብርማ ዓየን እኮ! በደቡብ አፍሪካ የተከናወነውን የሰላም አባት የሆነውን የኔልሰን ማንዴላን በግልጽና በይፋ የተተገበረውን፤ እንዲያው ነገርን ነገር ያነሳዋል ነው እንጂ የመለስ ቀብር የኢትዮጵያ ሕዝብ አጀንዳ ሳይሆን የወያኔ አጀንዳ ነው ለዚህም ነው ከእውነት የራቀ ድራማ የተሠራብን) የሚጠሉትን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ በክትባት ስም  እንዳይራቡ የሚያደረግ ማምከኛ መርፌ  እስከ ማስወጋት እርምጃ መውሰዳቸው በገሐድ እየወጣ ነው፤ በተባባሪነትና በአስፈጻሚነት የተገበሩት ደግሞ አሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ መሆናቸው ይታወቃል።

እኒሁ እኩይ ሰው በሥልጣን ወዳድነታቸውና፤ ኢትዮጵያን ከመጥላታቸው የተነሣ ገና በትረ መንግሥቱን እንደጨበጡ የወሰዱትን እርምጃ ማጤን አስፈላጊ ይሆናል። ከሌላው ታጋይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመደራደርና በመመካከር ሕዝቡ ሳይለያይ ማስተዳደር ሲገባ፤ ለብዙ ሺህ ዓመታት በመልክአ ምድር አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን በደምና በአጥንት ተዋህዶ በአንድ ዘውዳዊ አስተዳደር ጥላ ሥር የኖረውን የኤርትራና የኢትዮጵያ ወንድማማች ሕዝብን ጉዳይ ወደጎን ትተው ለሥልጣናቸው ብቻ በማድላት በቅድሚያ ያደረጉት ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራ ነፃ ሀገር ሆናለች፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ዕውቅና ትሰጣለችና እንደ መንግሥትእንድትመዘገብ ድጋፋችንን እናረጋግጣለን” የሚል ደብዳቤ በመጻፍ ነበር ቀልባቸውን ለመሰብሰብና ሥልጣናቸውን ለማደላደል የሞከሩት።

እንዳጋጣሚ ሆኖ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት የኢትዮጵያ ዋነኛዋ ጠላት የሆነችው ሀገር ሰው ግብጻዊው ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ ነበሩና ሐሳባቻው እውን ሆነላቸው። ለዚህም ተግባራዊነትና ፈጣን የሆነ ምላሽ እንዲገኝ ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በተደረገበት ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ በማቅረባቸው ድብደባና ከእስር እስከ ግድያ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ይህንንም አሠቃቂ ድርጊት የፈጸሙት መለዮ ለበሾች ናቸው። በዚህም ወቅት ያገለገሉት ሕዝብን ሳይሆን፤ የገዛ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በመግደል የፈጸሙት ተግባር ከውሻነት ደረጃ ከፍ ሊያደርጋቸው አይችልም። መለዮ ለባሹ እንደዚህ ያልውን ደረቅ የጭፍጨፋ ተግባር የሚፈጽመው የሀገራችንን  ሉዓላዊነት ረግጦ፤ ድንብር ጥሶ በሚመጣ የውጭ ጠላት ላይ ያውም እስኪማረክ ድረስ ከተማረከ ግን ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቱ የተከበረ ነው፤ እንጂ በወገን ላይማ ከቶ የሚታሰብ እንኳ መሆን አልነበረበትም።

በሥልጣን ወንበር ያለው ዘራፊ መንግሥት በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል ስለሚያውቅ፤ ምናልባት ከእስክሪቢቶና ከወረቀት በስተቀር ሌላ ነገር በእጁ ምንም ያልያዘውን ሰላማዊ ሠልፈኛ፤ መንግሥት ለመገልበጥ በማሴር ላይ ናቸውና ሄዳችሁ አስፈላጊውን  እርምጃ በመውሰድ ሠልፉን በትኑ በማለት ቀጭን ትዕዛዝ የሚሰጥ ባለሥልጣን አንደኛ ወንጀለኛ ነው፤ ሁለተኛ ሕገመንግሥቱን አያከብርም፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መለዮ ለባሹን በመናቅ እንደግቢው ውሻ ያዘዋል ማለት ነው።

መለዮ ለባሹ ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆኑን ካመነ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ለሠፊው ሕዝብ ጥቅም መስዋዕት ቢሆን ስሙ ለዘለዓለም በክብር ሲነሳ ይኖራል። ነገር ግን ራሡን አዋርዶ ለጊዜያዊ ጥቅም የሚኖር ከሆነ ግን በግዳጅ ላይ እያለ ድንገት እንኳ ቀኑ ደርሳ ሕይወቱ ብታልፍ የውሻ ሞት እንደሞተ ይቆጠራል እንጂ ምንም ከብር አይሰጠውም።

በተለይ ፌድራል ፖሊስ የሆናችሁ መለዮ ለባሾች የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ታሪካችሁን ጠንቅቃችሁ ማወቅ ይገባችኋል። የአብርሃ ደቦጭና የሞገስ አስገዶምን ለወገን ክብርና ለአገር ሉዓላዊነት ሲሉ በጠላት ላይ የወሰዱት ቆራጥ የሆነ የጀግንነት ወኔ ከልባችሁ ሠሌዳ ላይ ለአፍታም ቢሆን መጥፋት ቀርቶ መደብዘዝ የለበትም። ጣሊያን የባዕድ አገር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዋራጅ ገዥ ሲሆን ወያኔ ደግሞ ከወገን የወጣ ቢሆንም ታሪክን እያጠፋ ቅስም የሚሰብር ከሃዲ ቡድን ነው።  ስለሆነም የወያኔው ዘረኛ መንግሥት ከሰብዓዊ ክብራችሁ አዋርዶ እንደ ሮቦት ወይም እንደውሻ ሊገለገልባችሁ ስለሚፈልግ ኃላፊነታችሁን በብቃትና በጥራት ለመወጣት እንድትችሉና ከኅሊና ወቀሳም ነፃ እንድትሆኑ ሕገመንግሥቱን በማወቅ፤ በዚያ መሠረት የወገናችሁን ሰብዓዊ ክብር በማይጋፋ መልኩ ግዳጃችሁን እንድታከናውኑ ይረዳችኋል።

እዚህ ላይ ማጤን ያለባችሁ እናንት ወዶ ዘማቾች(mercenaries) አይደላችሁም:: የተከበራችሁ የወገን አለኝታና መከታ ናችሁ። ወዶ ዘማች ማለት በሌላ ሰው አገር በገንዘብ ተገዝቶ የሚዘምት ሆድ አደር ማለት ነው እናንተ ግን ለአገራችሁና ለወገናችሁ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ቃለመሃላ የፈጸማችሁ እንደመሆኑ መጠን ወገናዊ ሆናችሁ መቆም ያለባችሁ ከሠፊው ሕዝብ ጎን እንጂ፤ የወገናችሁን ሰብዓዊ መብትና ክብር በመደፍጠጥ ከድሀው ሕዝብ አላግባብ እየዘረፉ እራሳቸውን ለሚያደልቡ አምባገነን አሳማዎች መሆን የለበትም። የፈለገው ነገር ጥንቅር ብሎ ይቅር እንጂ በወገን ላይ ያላግባብ እየተዘመተ በሚገኝ እንጀራ እንደ ውሻ ተዋርዶ ከመኖር ይልቅ የክብር ሞት ይሻላችኋል። ለነገሩ በየዋሃን ወገን ላይ ከመዝመት የበለጠ ሞት አለን?

አገራችን ኢትዮጵያ እንደቀድሞ አባቶቻችን ሁሉ ዛሬም  በሐቀኛና ጀግኖች ልጆቿ  ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !

ይህን ጽሑፍ ያነበባችሁ ላላነበቡ ወገኖች በማስተላለፍ ተባበሩ!

No comments:

Post a Comment