ኢንጂነር ግዛቸው የዉህደት ጥሪ ለሰማያዊ/መኢአድ/መድረክ/አረና/ኢዴፓ አቀረቡየአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ «በመድረክ ዙሪያም ሰፊ ዉይይት ያደረገ ሲሆን፣ አዲሱ ብሄራዊ ምክር ቤት፣ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ፓርቲው ከመድረክና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የጀመረውን ውህደት እልባት እንዲያበጅለት መመሪያ ሰጥቷል» ስንል መዘገባችን ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ አስተያየት ያደረጉት አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ድርጅታቸው ከአሁን በኋላ በግንባርነት እንደማይሰራ ገልጸዋል።
ድርጅቶች ልዩነቶቻቸዉን አጣበው ወደ ዉህደት በመምጣት፣ በጋራ ትግሉን ወደፊት ማራምድ እንዳለባቸው የገለጹት ኢንጂነር ግዛቸው የዉህደትን ጥቅም አጠንክረው አስምረዉበታል። ለመኢአድ፣ ለመድረክ፣ ለሰማያዊ ፓርቲ፣ ለአረና እንዲሁም በአቶ ልደቱ አያሌዉ ይመራ ለነበረዉ ለኢዴፓም ጥሪ አቅርበዋል።
ዉህደት ማድረግ ካልተቻለ ግን፣ አንድነት ለድርጅቶች እዉቅና ሰጥቶ መተባበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ (እንደ በጋራ ሰልፍ መጠራት የመሳሰሉ) ትብብር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል የሚገልጽ እድምታ ያለው ንግግር ነበር ኢንጂነር ግዛቸው ያቀረቡት።
መኢአድና አረና ከአንድነት ፓርቲ ጋር የመዋሃድ ፍላጎት እንዳላቸው ከዚህ በፊት ማሳወቃቸው፣ በዚህም ረገድ አንዳንድ ንግግሮች እየተደረጉ እንደነበረ ይታወቃል።
የመድረክ አባል ድርጅቶች ከአንድነት ጋር ለበርካታ አመታት አብረው የሰሩ እንደመሆናቸው የጠነከረ መቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል ቢታወቅም፣ በዉህደቱ አንጻር ግን ምን ያህል ከአንድነት ጋር ለመዋሃድ እንደሚፈልጉ፣ ምን ያህል ያላቸውን መሰረታዊ የፖለቲካ ልዩነቶች ለማጥበብ እንደሚችሉ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም።
ሰማያዊ ፓርቲ ለጊዜዉ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ የመስራት አዝማሚያ ያለው አይመስልም። ነገር ግን በአንድነት ዉስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ተጨባጭ ለዉጦችን በመመልከት የአቋም ለዉጥ ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም።
የዉህደቱ ጥሪ ለኢዴፓ መቅረቡ ብዙዎችን ሊያነጋገር የሚችል አዲስ ዜና ነው። በአንድነት አካባቢ ከኢዴፓ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት መታየቱ፣ በቅርቡ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አቶ ልደቱ አያሌው ላቀረቡት በጋራ የመስራት ጥሪ፣ ምላሽ ተደረጎ ሊወስድ የሚችልበት ሁኔታም ሳይሆን እንደማይቀር ነዉ።
ኢንጂነር ግዛቸው ለተቃዋሚ ድርጅቶች የዉህደት ጥሪ በማቅረብ ብቻ አልተወሰኑም። ገዢዊ ፓርቲ ኢሕአዴግ የከረረ አቋሙን ቀይሮ ለእርቅና ሰላም እንዲዘጋጅም አሳስበዋል።
No comments:
Post a Comment