ባለፈው ሳምንት የሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ በግል ጉዳዬ ተገኝቼ ነበር፡፡ በቢሮው ውስጥ ጉዳዬን እያስፈጸምኩ ሳለሁ የጋዜጣው አዘጋጆች
በቢሮው የእንግዳ መቀበያ ሶፋ ላይ ከተሰየሙ ሦስት ሰዎች ጋር በጋዜጣው ዕትም ላይ አንድ ታዛቢ ስላስነበቡት ጽሑፍ በመወያየት ላይ ነበሩ፡፡ በጋዜጣው አዘጋጆችና በእንግዶቹ መካከል ሲካሄድ የነበረው ውይይት በሒደት ኃይለ ቃል የታከለበት ጭቅጭቅና ዛቻ እንደነበረበት አስተውያለሁ፡፡
በእንግድነት የተገኙት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ሰዎች፣ አዲስ አበባ ቦሌ ብራስ አካባቢ በሚገኘው የሪፖርተር ቢሮ ድረስ ገስግሶ ያስመጣቸው ጉዳይ ደግሞ፣ በጋዜጣው ላይ አንድ ታዛቢ፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው አስተዳደራዊና አካዴሚያዊ ችግሮች ላይ ጋዜጣው ያስነበበው ጽሑፍ መሆኑን ተግንዝቤያለሁ፡፡ ለመሆኑ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጋዜጣው በወጣ ማግሥት ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ድረስ ገስግሶ ያስመጣቸው በእውነት የተጻፈው ነገር ሚዛናዊ አለመሆኑ አስቆጭቷቸው ለእውነት ለመሟገት ነው? ወይስ ከበስተጀርባው ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን?
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም አንድ ጸሐፊ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስላሉት አስተዳዳራዊና አካዳሚያዊ ችግሮች የታዘቡትን፣ ቁጭት በታከለበት መንፈስ ሐሳባቸውን ለአንባቢያን፣ ለመንግሥትና ለዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ይደርስ ዘንድ ጽፈው ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ባለፈው ሰኞ በሪፖርተር ቢሮ የተገኙት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች፣ እሳት ለብሰው እሳት ጐርሰው የመጡበት ሁኔታቸውን የታዘብኩበት ያልገመትኩት ገጠመኜ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ወደ የት እየሄድን ነው ብዬ እንድጠይቅም አስገድዶኛል፡፡
በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በአገራችን እንግዳና አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ድክመታቸውን፣ ጥፋታቸውንና ስህተታቸውን የሚገልጹባቸውን ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች ሥልጣናቸውን፣ ገንዘባቸውንና የሚያውቋቸውንም ሆነ የማያውቋቸውን ባለሥልጣናትን ተገን በማድረግና ስማቸውን እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ለመበቀል የሚፈልጉ፣ በቁጣና ዛቻ ቆይ ባላሳይህ በሚል የሚያስፈራሩ ሰዎችንና ተቋማትን በተደጋጋሚ አይተናል፤ ታዝበናል፡፡ ግን የነገው ትውልድ ተስፋ በሆኑ የትምህርት ተቋሞቻችን ውስጥም እንዲህ ዓይነት ሰዎች መኖራቸው አሳሳቢ ነው፡፡ የሰኞው ዕለት የሪፖርተር ቢሮ ገጠመኜም ይህንኑ እውነታ ያጠናከረልኝ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ለተወሰኑ ደቂቃዎች በሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ ውስጥ ኃይለ ቃል በታከለበት ሁኔታ ከጋዜጣው አዘጋጆች ጋር አተካራ የገጠሙት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት ከሆኑ ሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በወጣው ጽሑፍ በእጅጉ መናደዳቸውንና መብገናቸውን ከሁኔታቸው በግልጽ ያሳይ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን የዩኒቨርሲቲውን ስምና ዝና የሚያጐድፍ ወይም ሚዛናዊ ያልሆነ ጽሑፍ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መውጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ ሲያስረዱና ሲወተውቱ ነበር፡፡
ይህ ጽሑፍ በጋዜጣው ላይ መስተናገድ እንዳልነበረበት፣ የተጻፈው ነገር ከእውነት የራቀና የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሆነ ለማስረዳት ያልቦዘኑት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች፣ ከጋዜጣው አዘጋጆች ጋር የገጠሙት አተካራና ጭቅጭቅ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካሉ ሰዎች የሚጠበቅ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ለመሆኑ ምሁራኖቻችን የፈረንሳዊው ፈላስፋና ጸሐፊ ቮልቴርን ‹‹በምትናገረው ወይም በምትጽፈው ነገር ባልስማማም ስለመናገር ወይም ስለ መጻፍ መብትህ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ እታገልልሃለሁ፤›› ያለውን አባባል ዘንግተውታል ማለት ነው እንዴ?! በእርግጥም ዩኒቨርሲቲዎቻችን በእንዴት ተነካን ባዮች፣ ስለድካማቸውና ስህተታቸው በተነገራቸውና በተጻፈባቸው ቁጥር ቁጣ፣ ዛቻና ማስጠንቀቂያ በሚቀናቸው በእንዲህ ዓይነት ሰዎች የተሞሉ ከሆነ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡
በዕውቀት፣ በመነጋገርና በሰከነ ውይይት የሚያምን ትውልድ ማፍሪያ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን እንዴትና ምን ተደርጐ እንነካለን በሚሉ ሰዎች የተሞሉ ከሆነ በእውነትም አስፈሪ ነው፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነም ቆም ብለን ልንጠይቅ የሚገባን ይመስለኛል፡፡
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሰዎች ሐሳባቸውን የመግለጽ ሙሉ ነፃነት እንዳላቸው በግልጽ አስቀምጦ ሳለ (ምንም እንኳን ተግባራዊነቱ በጥያቄ ውስጥ መውደቁን እየታዘብን ቢሆንም) ለምን እንዲህና እንዲያ ተጻፈብን በሚል ሰበብ ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ድረስ ገስግሶ መምጣት ምን ማለት ነው? ለመሆኑ እነዚህ የዩኒቨርሲቲው አባላት አቤቱታ ቢኖራቸው በዚህ በሠለጠነ ዘመን ሐሳባቸውንም ሆነ አቤቱታቸውን የሚያቀርቡባቸው ስንት መንገዶች እያሉ፣ ሦስት ሰዎች ሥራ ፈትተው ያውም በሥራ ቀን ጊዜያቸውን ማባከን ነበረባቸውን? ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ሲመጡ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የመኝታና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ማን ይሆን የሚሸፍንላቸው? መቼም ወጪያቸውን ከራሳቸው ኪስ ነው የሚሸፍኑት ብሎ የሚል የዋህ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
ስለዩኒቨርሲቲው የተጻፈው ነገር ሚዛናዊ ያልሆነና ከእውነት የራቀ ነው ቢባል እንኳ ቅሬታውን ለማቅረብ አንድ ሰው በቂ አልነበረም? የሆነስ ሆነና በጋዜጣ ላይ ለወጣ ትችት በዚያው ጋዜጣ ላይ ዩኒቨርሲቲው ሕዝቡ እውነታውን እንዲያውቅ የአፀፋ ምላሽ መስጠት የሚችልበት ዕድል እያለ በምን ምክንያት ነው ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ድረስ ሦስት ሰዎች ጊዜና ገንዘብ አባክነው ለአቤቱታ የሚመጡት? ስለመናገርና መጻፍ መብት፣ ስለዲሞክራሲና ስለሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት እናስተምራለን ብለው የሚለፍፉ ዩኒቨርሲቲዎቻችንና ምሁራኖቻችን ሌላ ሌላውን እንጂ በእኛ ላይ እንዴት ተደርጐ ይጻፍብናል የሚሉ ከሆነ ወዴት እያመሩ እንዳሉ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በስንት ልመናና ልምምጥ ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ዘንድ ፈቃድ አግኝታ ለሕትመት ብርሃን የበቃች ‹‹ሕሊና›› የምትባል ጋዜጣ ነበረች፡፡ ጋዜጣዋ ከጥቂት ወራት ያለፈ ዕድሜ ግን አላገኘችም ነበር፡፡ ዕጣ ፈንታዋ፣ ፅዋ ተርታዋ መዘጋት ነበር፡፡ ‹‹ሕሊና›› ጋዜጣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ስላለው አስተዳዳራዊና አካዳሜያዊ ችግሮች፣ ስለአንዳንድ ምሁራን ነን ባዮች መምህራን የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የጐጠኝነትና ኢሞራላዊ ድርጊቶቻቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ዙሪያ የድርሻቸውን ማበርክት ስለተሳናቸው፣ ‹‹እኔ ምን አገባኝ›› በሚል ስሜት የፍርኃት ቆፈን ስለያዛቸው ምሁራኖቻችን በማንሳት መጻፍ ስትጀምር፣ ‹‹ይህች ባቄላ ያደረች እንደሆነ አትቆረጠምም›› በሚል በአስቸኳይ እንድትዘጋ ተደረገች፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የሕዝብ አንደበት መሆን ከተሳናቸው፣ ፍትሕ ሲዛባ፣ የሰው ልጆች/የዜጎች መብት ሲጣስ፣ የጭቆናና የአፈና ቀምበር በሕዝቦች ላይ ሲከብድ አላየንም አልሰማንም በሚል ፈሊጥ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚሉ ከሆነ ፍፃሜያችን ምን ሊሆን ነው? በሪፖርተር ጋዜጣ የታዘብኩት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ሁኔታም በአገራችን ባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመናገርና የመጻፍ መብቶች ያለ ምንም ገድብ ዕውን ሆነው በሁለት እግራቸው መቆም እንዲቻላቸው ገና ብዙ ሥራ፣ ብዙ ልፋትና ረጅም ጉዞ እንደሚጠበቅብን ያሳየ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
(ብዙአየሁ ማቴዎስ፣ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን)
* * *
No comments:
Post a Comment