Sunday, December 22, 2013

ቤተ ክርስቲያን የካሽ ሬጅስተር ተጠቃሚ ልትኾን ነው


  • የአ/አ ሀ/ስብከት፣ የክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች፣ የልማትና በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ደረጃ አንድና ሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የቅድሚያ ተጠቃሚ ይኾናሉ
  • ለመንበረ ፓትርያርክ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር መሠረት የሚጥል ነው
  • ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመጠየቅ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል
  • ድብቅ ሙዳየ ምጽዋት ማስቀመጥ፣ በዣንጥላና በምንጣፍ ገንዘብ መለመን ይከለከላል
(አዲስ አድማስ፤ ታኅሣሥ ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. )
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽንን ለገቢ መሰብሰቢያነት ለመጠቀም የሚያስችላቸው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑ ተገለጸ፡፡
ዘመኑን ያልዋጀውንና ጥራት የጎደለውን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አሠራርና ቁጥጥር ችግር ግልጽነት፣ ወጥነት፣ ተቀባይነትና ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አያያዝ ሥርዐት ለመቅረፍና ለማድረቅ ያስችላል፤ በሚል በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ እንደተጠቀሰው÷ በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ገንዘብ ሕጋዊ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት የሚገባ ሲኾን ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስትር ማሽን እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡
የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽን ተጠቃሚ መኾናቸው በገቢ ሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል፡፡ በጥናቱ ላይ በመነሻነት ከተዘረዘሩት ችግሮች ለመረዳት እንደሚቻለው በዕለት ገቢዎችና ደረሰኝ አጠቃቀም ረገድ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ገቢ ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ አሳትሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለግል ገንዘብ ይሰበሰባል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተከለከለ ደረሰኝ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ታይቷል፤ ከደረሰኙ በበራሪው/ለከፋዩ ከሚሰጠው/ የተለየ መጠን በቀሪው ላይ መጻፍና የግል ጥቅምን ማካበት ይዘወተራል፤ በዘወትርና በክብረ በዓላት በርካታ ገንዘብ ገቢ ቢኾንም በዕለቱ ወደ ባንክ ያለማስገባት ኹኔታ አለ፤ ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ከመተማመን አንጻር ደረሰኝ የመቀበል ልማድ የለሌላቸው መኾኑን እንደክፍተት በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን የመጣው ገንዘብ ‹‹በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛል፤›› በሥራ ላይ ያልዋሉ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች ሴሪ ንምራ ቁጥር) መሠረታዊ ችግር ተጠንቶ መፍትሔ አልተሰጠም፡፡
በንግሥ፣ በወርኃዊ በዓላትና በዕለተ ሰንበት በሙዳየ ምጽዋት ሳይኾን በተዘረጋ ጨርቅ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ መኖሩን የሚጠቅሰው ጥናቱ÷ በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ ሀ/ስብከቱ በታኅሣሥ፣ 2003 ዓ.ም. ባስተላለፈው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ የሥራ መመሪያ መሠረት የምእመናንና ካህናት ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በሙሉ በተገኙበት ቆጠራ የማይካሄድበትና በተወሰነ መልኩም ሙሉ ገንዘቡ ገቢ የማይደረግበት ኹኔታ በመኖሩ አሠራሩ ለብኩንነት፣ ሐሜትና አሉባልታ መጋለጡን ገልጧል፡፡ በንግሥ በዓላት ወቅት ጥላ ዘቅዝቀው የሚለምኑ ሰዎች ኹሉም ስለማይታወቁ የተኣማኒነት ችግር አለ፡፡ በስእለትና በሙዳየ ምጽዋት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦች በመመሪያው መሠረት በዕለቱ የባንክ ምንዛሬ ወደ ብር እየተቀየሩ በተገቢው መንገድ ገቢ አለመኾናቸው፣ በምትኩ ቅያሬው ወጥነት ያለውና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደኾነም ተዘግቧል፡፡
በቃለ ዐዋዲ ድንጋጌው የተመለከተውንና በዝርዝር የሥራ መመሪያ የተላለፈውን የገቢ አሰባሰብ በተሻለ አሠራር ያጠናክራል የተባለው በፖሊሲና መመሪያ ረቂቁ የሒሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ ምዝገባና አወጋገድ መሠረት÷ ለሒሳብ ሥራ የሚያገለግሉ ደረሰኞችና ቫውቸሮች የዋና ተጠቃሚውን ተቋም ስም ይዘው በሀገረ ስብከቱ ምስጢራዊ ኮድ ይዘው ይታተማሉ፤ የማሳተም ሓላፊነቱም የሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል ሲኾን ይህም በዋና ሥራ አስኪያጁ ፈቃጅነት የሚከናወን ይኾናል፡፡
Cash register machineበማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ሕጋዊ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት ይገባል፤ ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስተር ማሽን ተፈጻሚ ይኾናል፤ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከገንዘብ ሰብሳቢ ውጭ መያዝና መጠቀም አይቻልም፡፡ ማንኛውም የገንዘብ ስጦታ በገንዘብ ያዡ በኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ስጦታው እንደተበረከተም ወዲያውኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሊቆረጥለት ይገባል፡፡ በዐይነት የሚሰጥ ስጦታ በግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይመዘገባል፡፡
ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውጭ በሙዳየ ምጽዋት ሣጥን ገንዘብ መሰብሰብ አይቻልም፤ ቋሚ ሙዳየ ምጽዋት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚቀመጥበት ቦታ ተጠንቶ በሰበካ ጉባኤው መጽድቅ አለበት፤ ለቆጠራ ካልኾነ በቀር ከተቀመጠበት ማንቀሳቀስ አይቻልም፤ በትከሻና ተይዘው የሚዞሩ ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ሙሉ መረጃ ተመዝግቦ ይያዛል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ሣጥኖቹ ከመከፈታቸው በፊት ሁሉም ቆጣሪዎች የቁልፍ ካዝናውና የቁልፍ ሣጥኖች፣ የሣጥኖቹን ብዛትና እሽጋቸው አለመከፈቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ የተቆጠረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ካልተቻለ ከሌላ ገንዘብ ጋራ ሳይቀላቀል በበነጋው ወደ ባንክ አካውንት መግባት አለበት፤ ዣንጥላን፣ ምንጣፍንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ገንዘብ መሰብሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ይኾናል፡፡
[የሀገረ ስብከቱ የመዋቅርና አደረጃጀት ሰነድ አካል የኾነው የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ጥናት ረቂቅ እንደሚያትተው÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት፣ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች፣ የልማትና በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ደረጃ አንድ እና ሁለት የኾኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በኮምፒዩተር የታገዘ የሒሳብ አያያዝ ዘዴን/ሥርዐት እንዲከተሉ ይደረጋል፡፡ የሒሳብ አያያዝ ዘዴውምየሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ዘዴ(Double entry system) ሲኾን በአክሩዋል ቤዝስ ከሚጠቀሙት ከልማት ተቋማት በስተቀር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሥሩ ያሉ ሌሎች ተቋማት በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ፣ ገቢንና ተከፋይን በታሳቢነት በሚያስላው የሒሳብ አያያዝ ዘዴ(Modified cash bases) እንዲከተሉ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጦአል፡፡ በኮምፒዩተር የሚታገዘው የሒሳብ አያያዝ ሶፍትዌርም በሀገረ ስብከቱ ተመርጦ የተዘጋጀው እንደሚኾን ታውቋል፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ዘመናዊው የፋይናንስ ሞያ በጥምረት ሥራ ላይ ለሚውልበት ለዚህ አሠራር ተፈጻሚነት÷ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶችና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተመርጠው ለተውጣጡና ለሚመለከታቸው የሒሳብና የቁጥጥር ሓላፊዎችና ሠራተኞች ሥልጠና እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲኾን የሀገረ ስብከቱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ዶኩመንቴሽን ዋና ክፍል በማእከል ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የመሠረተ - ቴክኖሎጂው ዝርጋታ በሚተገበርባቸው ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናትም በግልጽ የፕሮጀክት አሠራር እንደሚፈጸም ተገልጧል፡፡]
ዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲኾንም በተጭበረበሩ ደረሰኞችና በማይታወቁ የገንዘብ አሰባሰቦች የግል ጥቅምን ማካበት በመከላከል ለክትትልና ቁጥጥር አመች ለማድረግ እንደሚያበቃ ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በልማትና በጎ አድራጎት ተቋማቱ እንዲሁም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘጋጁ የፋይናንስ ሪፖርቶች ግልጽነት፣ ወቅታዊነትና ተኣማኒነት/ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ሀገረ ስብከቱ በሚሰበሰበው የኻያ በመቶ ፈሰስና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በቅጽ ተሞልቶ በሚላከው ሒሳብ መካከል በየዓመቱ የሚያጋጥመውን ልዩነት ለማስወገድ እንደሚያስችል ተገልጧል፡፡
ይህም በሒደት ከፍተኛ የሀብት ክምችት የሚገኝበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አሠራሩና መልካም አስተዳደሩ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል በመኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ይኖራት ዘንድ መሠረት ለመጣል፣ የካህናቷን ኑሮ በማሳደግና በማሻሻል ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም የምትፈጥርበት መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡

No comments:

Post a Comment