Sunday, December 22, 2013

የማንታገለው “ከእባብ እንቁላል ጫጩት ሲፈለፈል” ለማየት ነውን?!..


መንግሥት ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን ከሕገ መንግሥቱ የመነጩ የሃይማኖት ነፃነትና የእምነት መብትን የማስከበር ጥያቄዎች ላለመመለስ በየጁሙአው በመስጂዶች የሚደረጉ የተቃውሞ ትዕይንቶችን ሰበብ እንዳያደርግ፣ ‘እስኪ ጥያቄያችንን በሰከነ ልብ አጢኖ ሕጋዊና ተገቢ ምላሽ የሚሰጥበት ዕድል እንስጠው’ በሚል ቀና መንፈስ የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በዚህ የእፎይታ ጊዜ ውስጥ የህዝበ ሙስሊሙን የልብ ትርታ ያገናዘበ አንድም ቀና እርምጃ ሲወስድ አልታየም፡፡ እንዲያውም በሃይማኖትና በእምንት ነፃነታችን ላይ የሚቃጡ ጥሰቶች ተጠናክረው ነው የቀጠሉት፡፡ …
አሚራችን ድምፃችን ይሰማ የሕዳር 23ቱ የኮሚቴዎቻችን የፍርድ ቤት የብይን ቀጠሮ ወደ ታሕሣሥ 3 እንደተዘዋወረ፣ “የእፎይታ ጊዜው በታሕሣሥ 3ቱ ብይን ላይ ተመሥርቶ ያበቃል” የሚል ውሳኔ በይፋ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ እናም ሁላችንም ታሕሣሥ 3ን በጉጉት ጠበቅናት፡፡ ገዢው ኢሕአዴግ ከሚያሾረው ፍርድ ቤት ፍትኅ ይገኛል ብለን ታሕሣሥ 3ን በተስፋና በጉጉት ጠበቅናት፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ! … እውነት እውነት እላችኋለሁ ተሞኘን! … ‹‹ከእባብ እንቁላል ጫጩት ይፈለፈላል›› ብለን ጠበቅን፡፡ … ከዚህ ወዲያ መሞኘት አለን?! …
ታሕሣሥ 3 ቀን ምን ተፈጠረ?
ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ … ታሕሣሥ 3 የሆነው ምን መሰላችሁ? … መቼቱን 4ኛ ወንጀል ችሎት ያደረገውና፣ እስከ ሕዳር 23 ተጽፎ ያልተጠናቀቀው የኢሕአዴግ የፍርድ ቤት ድራማ ስክሪፕት ተጽፎ ለመድረክ ቀረበ፡፡ በቃ! በታሕሣሥ 3፣ 2006 የሆነው ይኸው ነው፡፡ … በስክሪፕቱ መሠረትም፣ የተወሰኑት ፍርደኞች እስካሁን የታሹት ይብቃቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ጥቂት ተጨማሪ ጊዜያት ፍርዳቸውን ይቀጥሉ … ተባለ፡፡ በአጭሩ ታሕሣሥ 3 ቀን ለመድረክ የበቃው ድራማ ስክሪፕት ጭብጡ ይህ ነው፡፡
ኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በእሥር ላይ የሚገኙ ሙስሊም ወንድምና እህቶች በሙሉ ከፍርደኛ አይለዩም፡፡ ኢሕአዴግ ምንም ጥፋት እንዳልሠራህ እያወቀ የተጋነነ ክስ ይመሰርትብህና የዋስትና መብትህን ይነፍግሃል፡፡ ከዚያ በተራዘሙ ቀጠሮዎች ከወህኒ ቤት ፍርድ ቤት እያመላለሰ በእስረኝነት ይቀጣሃል፡፡ ለዚህም ነው በመላ አገሪቱ በእሥር ላይ የሚገኙ ሙስሊም ወንድምና እህቶች በሙሉ ከፍርደኛ አይለዩም የምለው፡፡…
የተከበራችሁ ወንድም እና እህቶቼ፣ እባካችሁ ታሕሣሥ 3 ቀን “እነ እከሌ በነፃ ተለቀቁ” አትበሉ፡፡ እንዴት እንዲህ እንላለን?! ማነው በነፃ የተለቀቀው?! … አንድ ዓመት ከአራት ወር ታስሮ የተፈታ ሰው “ፍርዱን ጨርሶ ወጣ” ይባላል እንጂ “በነፃ ተለቀቀ” ይባላል እንዴ?! … እነዚህ ወንድሞቻችን እና አባቶቻችን የመጀመርያዎቹን ድፍን አራት ወራት የታሠሩት’ኮ አቃቤ ሕግ ተብዬው ተዋናይ “መረጃ ሰብስቤ አልጨረስኩም” እያለ እንዲራዘምለት በጠየቃቸው አራት የ28 ቀናት ቀጠሮዎች ምክንያት ነው፡፡ ከዚያች አራት በኋላ እንኳን ይኸው ድፍን አንድ ዓመት ያለ ምንም ማስረጃ ዋስትና አስከልክሎ ለድፍን ተጨማሪ አንድ ዓመት በወህኒ አማቀቃቸው፡፡ የማን ያለህ ይባላል?! እባብን ጫጩት እንዲፈለፍል ለምን እንማፀነዋለን?! … ለምን አንታገለውም?! … ለምንድነው እንቅልፍ እስኪነሳው እስኪያደነቁረው ድረስ ድምፃችንን የማናሰማው!! … ለምንድን ነው ስለ እምነት ነፃነታችን፣ ስለ ዜግነት መብታችን … የማንጮኸው?! …
ኢሕአዴግ በ1987 በአንዋር መስጂድ ራሱ የቀሰቀሰውንና መስጂድ ውስጥ ገብቶ በመተኮስ የ11 ንፁሃን ሙስሊሞችን ደም ያፈሰሰበትን ሁከት መነሻ አድርጎ ሐጅ ሙሐመድ ወሌ አህመድን ጨምሮ በርካታ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንጋፋ መሪዎችና ምሁራንን “የሰው ነፍስ በማጥፋት” ከሷቸው ነበር፡፡ አቃቤ ሕጉ መሥፍን የሚባል ሆዳም ነበር፡፡ አሁን ሞቷል አላህ ይፍረድበት!! “የተከሰሱበት አንቀጽ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ነው” በሚል ስክሪፕት ላይ ተመሥርቶ እነ ሐጅ ሙሐመድ ወሌን የዋስትና መብት አስከልክሎ አምስት ዓመት ከወህኒ ቤት ፍርድ ቤት ካመላለሳቸው በኋላ፣ በመጨረሻ የዳኛ ገፀ ባህሪ የሚጫወተው ተዋናይ “ነፃ ናችሁii” ብሏቸው ከእስር ተፈቱ፡፡… የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የፍርድ ቤት ድራማ አንድን ሰው አምስት ዓመት ሙሉ ከቤተሰቦቹ ነጥሎ በወህኒ እያማቀቀ አኑሮ “ነፃ ነህi” በሚል የሚጠናቀቅ “የከረፋ የሸፍጥ ድራማ” ነው፡፡ …
ታሕሣሥ 3 የተወሰኑ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ፍርዳቸውን ጨርሰው ወጥተዋል፡፡ አልሃምዱሊላህ! ሌሎቹ ወንድሞቻችን ደግሞ ያልተፈረደባቸው ፍርደኞች በመሆን እንዲቀጥሉ ተፈርዶባቸው አሁንም ፍዳቸውን እየተቀበሉ ነው፡፡ ታዲያ እኛ በፍትኅ ላይ ይህንን መሰል ሸፍጥ ከሚሠራ ኢሕአዴግን መሰል እባብ መንግሥት ፍትኅ ይገኛል ብለን ትግላችንን ማቀዛቀዛችን ከምን የመጣ ነው?! … በእኔ እምነት ይሄ በምንም መሥፈርት ትክክል አይደለም፡፡ ለመንግሥት “ለምን የእፎይታ ጊዜ መስጠት አስፈለገን” እያልሁ በ‹ነዳማ› እየተንገበገብኩ አይደለሁም፡፡… ኢሕአዴግ “የሰዎች ስብስብ ነው” ብለን በማሰብ፣ ሰዎች ደግሞ ነገሮችን መለስ ብለው በጥሞና ለማሰብ የሚችሉ ፍጡሮች ናቸው ብለን በማመን ለመንግሥት “የእፎይታ ጊዜ” ሰጥተነዋል፡፡ ተሞኘን ወንድሞቼ! ተሞኘን!… ኢሕአዴግ የእባቦች ስብስብ ነው! … “ከእባብ እንቁላል ጫጩት አይፈለፈልም!!” …
ፍትኅ፣ መብት፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ወዘ.ተርፈ. … የትግልና የመስዋዕትነት እንጂ የልመና ውጤቶች አይደሉም፡፡
Nasrudin Ousman

No comments:

Post a Comment