ሙሉጌታ አሻግሬ
mulugetaashagre@yahoo.com
mulugetaashagre@yahoo.com
‘ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ’ ነበር ነገሩ። ዓመቱ የሆነ አግራሞት ሳይፈጥር አያልፍም ለማለት የተባለ ነው። የፈረንጆቹ 2013 ዓመት ከመገባደዱ በፊት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ጉድ እየሰማን ነው።
አጤ ምኒሊክ በነገሱበት ዘመን ኢትዮጵያን ለማነፅና ህልውናዋን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመጣል ዘመኑ በፈቀደላቸው የእውቀት ደረጃ የበኩላቸውን ሰርተዋል። በዚህ ኢትዮጵያን የማነፅ ሂደት ውስጥ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ነበር ብሎ የሚደመድም ጤናማ ግለሰብ አይኖርም። ግዜውና ስርዓቱ የአፄ ከመሆኑም አንፃር ‘የአገር ማቅናት’ ሂደቱ በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በድምፅ ብልጫ፣ በውይይት ነበር ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቆም የነበረው ሂደት አብዛኛው የዓለም አገር በተመሰረተበት መንገድ የኃይል አጠቃቀም እንደነበረበት ግልፅ ነው።
ለዘመናት በዓለማችን በርካታ ጦርነቶች ተደርገዋል። ከጦርነት መለስም በህዝቦች መካከል የተለያዩ አንባጓሮዎች በየአካባቢው ይከሰቱ ነበር። ከዚህም ሌላ ከባህልና እምነት ጋር ተያይዞ በግለሰቦች መካከል በደል ይደርሳል። በእነዚህ ሽኩቻዎች ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የተለያዩ ግፍ እና እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈፀማሉ። ይህን ተከትሎ በርካታ ግለሰቦችም ሆኑ ህዝቦች ሰለባ ሆነዋል።
ስለዚህም በአጤው የጦር እንስቃሴ ውስጥ ችግር እንደነበር እሙን ነው። ምን ያህል ጦር ዘመተ? ፤ የደረሰው ጥፋት ምን ይመስላል? መቼ እና እንዴት ተከናወነ? የሚሉትን መረጃዎች ከታሪክ ድርሳናት ለማጣቀስ የሚቻልበት መንገድ አለ። ነገር ግን ከሳሽ ወገኖች ደርሶብናል (አፄ ምኒሊክ አድርሰውብናል) ብለው ያቀረቡትን ድርጊት በሙሉ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተመዝግቦ ለማግኘት ያለመቻሉ ምስጢር ሁኔታውን አጠራጣሪ ያደርገዋል። በርካታ ወገኖች የሚከራከሩበት ነጥብ በደሉ አልደረሰም ሳይሆን፤ ችግሩን የተወሰኑ ቡድኖች ለራሳቸው ፍላጎት ለመጠቀም በመፈለግ አጋነውና ጠምዝዘው ያቀርቡታል የሚል ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያገባኛል ያለው ዲያስፖራ እሰጥ እገባ ውስጥ ይገኛል። የችግሩ መነሻም ተበዳይ ነኝ ባዮቹ ‘ እኛ የምንናገረውን አፈታሪክ እውነት ነው በሎ ያልተቀበለ የድርጊቱ ፈፃሚ ተከታይ ነው ’የሚል ፍፁም ኢዲሞክራሲያዊ አቋም ነው።
ይህ ማለት ግን ሁሉንም በኢትዮጵያ ዙሪያ የተፃፉ መረጃዎችና ታሪኮች በጠቅላላ ጠንቅቄ አንብቢያለሁ የሚል ድምዳሜ ለመውሰድ አይደለም። ስለዚህ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ትክክለኛው መረጃ እና ማስረጃ አለኝ የሚል ማንኛውም ሃላፊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ መረጃውን ለሌሎች በማካፈል ሁኔታውን በሚዛናዊነት መርምሮ በመረዳት የጠራ አቋም ለመያዝ እንዲቻል የመነሻ ፅሁፍ ማቅረብ ነው።
(በዚህ ፅሁፍ ተፈፅሟል የተባለውን ድርጊት መጥቀሱ ባልተረጋገጠ ጉዳይ ላይ እውቅና መስጠት ስለሆነ ቃላቱን መግለፅ አስፈላጊ አይደለም። ይህን አቋም መውሰድ ያስፈለገበት ምክንያት የዚህ አስተያየት ፀሃፊ ይህን ሁኔታ በተመለከተ የተፃፈ መረጃ ለማግኘት ባለመቻሉ ነው።)
በተቃራኒ የቆመው ኃይል ደግሞ ይህ አካሄድ ማስረጃ ያለቀረበበት ከመሆኑም አንጻር ጥያቄውን የሚያራግቡት ግለሰቦች በፖለቲካ መድረክ ላይ ሪከርድ ያላቸው ስለሆነ ጥያቄውን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ነው የሚል ውዝግብ ነው።
የሚቀርበውን በደል የጥፋት ልክ በሚዛናዊነትና ያለወገንተኝነት ለመመርመር እንዲቻል የተወሰኑ ተበድለናል ባይ ግለሰቦችን በግል ለማግባባት ተሞክሯል። ነገር ግን እነዚህ ከሳሾች ችግሩን ለመተንተን የሚያስችል ማስረጃ አያቀርቡም። እንደምክንያት ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል ፣
- ይህን ጥፋት ለመመዝገብ ግዜው አይፈቅድም የሚል ‘ የሞኝ ብልጠት ’ ነው። ከዚህም ባለፈ ድርጊቱ በአፈ ታሪክ የተነገረን ነው በማለት መረጃውን የማይዳሰስና የማይጨበጥ አፈተረት ያደርጉታል። ነገር ግን የኢትዮጵያን ታሪክ ፅፈዋል የተባሉ አውሮፓውያንና ኢትዮጵያውያን ከአፄ ምኒሊክ ዘመን በፊት የነበረውን የአገሪቱ ታሪክ በስፋት ጽፈውታል። ምንም እንኳን እነዚህ ወገኖች የአገራችንን ታሪክ ፀሃፍያን ‘ደብተሮች ’ ብለው የተለየ ትርጉም ለመስጠት በመሞከር ታሪካችንን ቢያጣጥሉትም፤ እነርሱ የሚቀበሏቸው አውሮፓውያንም ቢሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የጠቀሱት ነገር አለመኖሩ ድርጊቱን ኢተዓማኒ ያደርገዋል።
- ከአፄ ምኒሊክ ዘመነመንግስት ሦስት ክፍለ ዘመን (ሦስት መቶ ዓመታት) በፊት ተነስቶ ስለነበረው በተለምዶ አጠራር ግራኝ አህመድ በመባል የሚታወቀውን የኣዳሉን አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ ታሪክ በማመላከት የቆዩ የህዝቦች መካከል የተፈጠረ ችግር በታሪክ ተቀምጧል ለሚለውም የመከራከርያ ነጥብ፤ ሁኔታውን ከሃይማኖት ጋር በማጋጨት ወደማይፈለግ መንገድ ይከቱታል። ስለዚህ በዚያ በኩል የሚደረገው አካሄድ ሁኔታው የሃይማኖት ቅርፅ እንዲይዝ ስለሚያደርጉት በፖለቲካ መስመር አሊያም ከሃይማኖት በራቀ መልኩ ለመነጋገር አዳጋች ይሆናል።
- ግለሰቦቹ ተፈፅሟል የተባለው ክፉ ተግባር ላይ መረጃ ያለመገኘቱን ምስጢር ለማስረዳት የሚሞክሩበት መንገድ የተለየ ነው። እነርሱ እንደሚሉት በምኒሊክ ዙሪያ የተፃፉት ታሪኮች በሙሉ ቅዱስ የሆኑት የአፄው ተግባራት ብቻ ናቸው፤ የአፄዎች ክፉ ድርጊት አይፃፍም የሚል ነው። ነገር ግን ታሪክ እንደሚነግረን ከምኒሊክ በፊት የነበሩት የአፄ ቴዎድሮስ ከልጅነት እስከ እውቀት ብሎም ሞት ድረስ ያለው የሽፍትነት፣ የጦርነት፣ የወረራ ፣ ብሎም በንግስና ዘመን አገርን ለመከላከል ከእንግሊዞች ጋር የተደረገው ጦርነት በግልፅ ተፅፏል። በተረጋጋ መንፈስ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ስንመለከት አሉታዊ ጎኑ የሚያመዝን ሆኖ እናገኘዋለን። ከመሳፍንት አና የሃይማኖት አባቶች ጭምር የነበረው ውዝግብ በግልፅ ተቀምጧል። ስለዚሀ ‘ የአፄዎች ክፉ ነገር አይፃፍም ‘ የሚለውን ነጥብ ውድቅ ስለሚያደርገው እንደምክንያት ለመቀበል አስቸጋሪ ነው።
ከእነዚህ ወገኖች ጋር የተደረገው ውይይት መቋጫ በሁለት አማራጥ የታጠረ ነው። አንድ ድርጊቱን በእርስዎ መጀን ስልት በድፍኑ መቀበል ካልሆነ ደግሞ የአጤ ምኒሊክ ባለሟል ተደርጎ መቆጠር ነው።
ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ባልተረጋገጠ ነገር ላይ ያለማስረጃ መነጋገር ምን ይጠቅማል?
ግለሰቦቹ እንደሚሉት የአፄ ምኒሊክን ጥፋት ለማስታወስ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አንድ ሙዚየም እየተሰራ ይገኛል። በጦርነት ለሚደርሱ ጉዳቶች በርካታ ሙዚየሞች በዓለማችን ቆመዋል። የእነዚህ ሙዚየሞች ተቀዳሚ ዓላማ ያለፈውን የጥፋት ድርጊት በመረጃ ለመጪው ትውልድ በማሳየት ችግሩ እንዳይደገም ማስተማር ነው። ወደ እኛው ሁኔታ ስንመጣ በሙዚየሙ አቅራቢያ እንዲቆም ያደረጉት ሃውልት አለ። የሃውልቱ ይዘት የሚያሳየው ግለሰቦቹ ደረሰብን የሚሉትን በደል ነው፤ …እንደእነርሱ አባባል። ነገር ግን ሁኔታው በዝርዝር ሳይነገረው ሃውልቱን የማየት አጋጣሚ ያገኘ ማንኛውም ሰው በራሱ አእምሮ የሚሰጠው ትርጓሜ ይኖረዋል እንጂ እነሱ እንዳሰቡትና እንደሚዘረዝሩት ተፈፅሞብናል የሚሉትን መልዕክት ሃውልቱ በራሱ አያስተላልፍም።
ቁምነገሩ ግን የሃውልት መቆምና አለመቆም፣ ቅርጽና ውበት አይደለም። ችግሩ የሚመጣው እነዚህ ወገኖች በደሉን ለሶሰተኛ ወገን የሚገልፁበት መንገድ ነው። ሃውልት የቆመለትና ተፈፀመ የሚሉት በደል ፖለቲካቸውን ለማጦዝና ለማስፈፀሚያነት በእነዚህ ግለሰቦች ጭንቅላት ውስጥ አስርተ ዓመታትን አስቆጥሯል። የሃውልቱ አጠያያቂነት የሚጀምረው እነዚህ ግለሰቦች በደሉ የተፈፀመው (የተፈፀመ እንኳን ቢሆን) በምኒሊክ እና በአማራው ነው የሚል ሃላፊነት የጎደለው ጭፍን ፍረጃ መሆኑ ነው። ስለዚህ አጤ ምኒሊክ በሌሉበት ዘመን ሁሉ አማራው በጉዳዩ ተጠያቂ እንደሆነ ይቀጥላል ማለት ነው። በመሆኑም ይህን ቂም በመያዝ በ1980ዎቹ በበደኖ ፣ አርባ ጉጉ ፣ አሶሳ እና ሌሎችም አካባቢዎች ዘግናኝ ጥፋት አድርሰዋል። ይህ የሆነው እነርሱ በደለኛ ብለው በመደቡት አንድ ህዝብ ላይ ነው። ይህ የአማራው ህዝብ ነው። እነዚህ ሰዎች የአጤ ምኒሊክን ጥፋት መካስ ያለበት አማራው ነው ብለው የጨለማ ጉዞ ከተያያዙ በርካታ ዓመታት አስቆጥረዋል። ስለዚህ አጤ ምኒሊክ ሰው ይሁን መልአክ፤ አለቃ ይሁን ምንዝር ፤ ነጭ ይሁን ጥቁር ለይተው የማያውቁ እድሜያቸው አስር እንኳን የማይደርስ ህፃናት የአጤው በደል ብድር ከፋይ ተደርገው በመቆጠር በህይወታቸው እንዳሉ ወደገደል እንዲወረወሩ ፤ በርካቶች ደግሞ ቤት ተቆልፎባቸው በእሳት እንዲቃጠሉ ተደርጓል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ መንግስት ተብዬው አካል የሃውልቱን ስራና ተያያዥ ጉዳዮች ችላ በማለት ህዝቦች እርስ በእርስ በዘላቂነት እንዲቃቃሩና ለመጠፋፋት የሚያስችል የመጨካከን ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በግዴለሽነት በመመልከት ምን ያህል ሃላፊነት የጎደለው ተቋም እየሆነ እንደመጣ እያሳየን ነው።
ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሳይበር ንትርክ እንዲጀመር የመንግስት እጅ ከጀርባ እንዳለበት ነው። አንደኛው ምክንያት የሃውልቱ መሰራት በህዝቦች መካከል ሊያስከትል የሚችለውን ችግር የተረዱ ‘ቅን’ የስርዓቱ ግለሰቦች ያነሱትን ጥያቄ ወደ ዲያስፖራው በመወርወር፤ በዲያስፖራው መካከል በሚደረገው ንትርክ የማሳመን ስራ ለመስራትና በውስጥም በውጭም የሃውልቱን አስፈላጊነት ማሳየት ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ኢትዮጵያውያን በአረቡ ዓለም በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ዲያስፖራው ባልተጠበቀ ሁኔታና ሌሎች ህዝቦች ባልፈፀሙት መንገድ በመላው ዓለም አንድ ሆኖ መውጣቱ ነው። በዚህ የኢትዮጵያውያኖች ሞገድ ገዥው ወያኔ ለአርባ ዓመታት የሰራው የመከፋፈል ስራ መፈረካከሱና ለስርዓቱም አደጋ መሆኑ ነው። ይህን ኃይል ወደ ነበረበት የእርስ በእርስ መጠራጠር ደረጃ መመለስና ልዩነቱን የማስፋት ስራ መሰራት ነበረበት። ስለዚህ ከአጤ ምኒሊክ ጋር ተያይዞ የመጣውን አጋጣሚ ወያኔ በሰፊው ተጠቀመበት።
ዋናው ቁም ነገር ግን በሁለቱም ምክንያቶች ውስጥ በምዕራቡ አገራት የሚኖሩ የወያኔ አጫፋሪዎች ተበድለናል ባዮቹን ሲካድሙና እሳቱ እንዲፋፋም ሲያራግቡ የመገኘታቸው ምስጢር ነው። ስለዚህ ወያኔ ከችግሩ ጀርባ አርጩሜውን ይዞ እነዚህን ጥቂት ግለሰቦች ወደፈለገው አቅጠጫ እየጋለባቸው ይገኛል።
ከላይ ከተቀመጠው ሁለተኛ ምክንያት ጋር ተያይዞ በቋንቋ የተደራጁ ግለሰቦች ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በቋንቋ የተደራጁት ቡድኖች ወደአንድነት የመጣውን ኢትዮጵያዊ በመበታተን በሚፈልጉት መልኩ ወደ ጉያቸው በመሰብሰብ ወደተለመደው ጎሬ መጥበብ ነበረባቸው። በመሆኑም አንድ ሃይማኖት አንድ ህዝብ ልትሆን ነው፤ የቀደመው በደል ሊደርስብህ ነው፤ ይህን መንገድ ካልተከተልክ ይህን ትሆናለህ፣ ያኛው ይወሰድብሃል፣ ይህ ስም ይሰጥሃል፣ እንዲህ ተደርገህ ነበር የሚለውን የጎጥ መርዝ በመርጨት የሚፈልጉትን አባል መልሶ በማሰባሰብ መጠናከርና ህልውናቸውን ማረጋገጥ ነው።
ማጠቃለያ
በዲያስፖራው የተነሳውን እንኪያ ሰላንቲያ ከተለመደው እኔ እሻል ፖለቲካ በዘለለ፤ እንመራዋለን የሚሉት ድርጅት ግብዓተ መሬቱ ያስፈራቸው ተስፋ የቆረጡ ግለሰቦች ፤ በአልሞት ባይ ተጋዳይ መንፈስ ለጥፋት በሰፊው እየሰሩበት ነው። በህዝቦችና በሃይማኖት ላይ እየሰነዘሩት ያለው የጥፋት አማራጮች እውነትም እነዚህ ግለሰቦች የተሳፈሩበት ባቡር ሃዲዱን እንደሳተ ያሳየናል። በዚህ ፅሁፍ ዘርዝሮ ማቅረብ ባይገባም ከተቀረፁ የድምፅ ክምችቶች ለመረዳት እንደተቻለው አገሪቱ ዳግመኛ አገር ሆና እንዳትቆም ለማድረግ አእምሯቸው የፈቀደውን ጥፋት ሁሉ እንደአማራጭ ይደረድራሉ።
ስለዚህ በፖለቲካው መስመር ይህን አካሄድ ስንቃኘው ማንኛውንም ምክንያት ተደግፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ጥረት እንዳለ ያሳያል። ስለዚህ ይህች ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ሆና እንድትቆም መሰረት የሆነውን ምኒሊክ ማንነት በማፍረስ አገሪቱን በመበታተን ስራ የተጠመዱ ግለሰቦች ማስቆም ተገቢ ይሆናል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዚህን ጥያቄ መንስኤ በሰከነ አእምሮ ለመረዳት በመሞከር ተበድለናል የሚሉትን ወገኖች ለማዳመጥ ፍቃደኛ መሆን ያስፈልጋል። የተባለውንም ችግር በመረጃ አስደግፎ በማጤን የችግሩን ስሜት መጋራት የሚያስፈልግ ነው። ይህም በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመገንባት የምንመኛትን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ የመቻቻልን ፖለቲካ የምንለማመድበት አንዱ መንገድ ነው። ከዚህ በተለየ የሚቀርበው በግርድፉ ‘አይንህን አውጥተህ ጣል እኔ አይልሃለው’ የሚል እኔ ያልኩህን ብቻ ተቀበል ኋላቀር አካሄድ ተቀባይነት የሚያገኝ አይሆንም። ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ለማሳመን የሚደረገውን ጥረት ድብቅ ዓላማ በመረዳት ሊከተል የሚችለውን ጥፋት መከላከል ያስፈልገናል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመላው ዓለም የተስገመገመው ኢትዮጵያዊነት ወዳጅን በግርምት እጁን በአፉ እንዲጭን፤ ጠላትም ኢትዮጵያ ለካንስ አሁንም አለች ብሎ በፍርሃት እንዲጠነቀቅ አድርጎታል። ይህን ኢትዮያዊነት የሚሸረሽር ማንኛውንም እንቅስቃሴ በእንጭጩ እንከላከል። አዎ ሳይቃጠል … በቅጠል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
No comments:
Post a Comment