Monday, December 30, 2013

በተቀነባበረ የመብራት ሀይል ሙስና ኢትዮጵያ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንድታጣ ተደረገ


December 30/2013

ታህሳስ ፳፩ ( ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ኤለክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ውስጥ በታየው ከፍተኛ የሙስና ወንጀል አገሪቱ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ አጥታለች። ይህንን የሙስና አሰራር የተቃወሙት ስራ አስኪአጁ አቶ ምህረት ደበበ በመጨረሻ ከስልጣናቸው ተነስተዋል።
የህወሃቱ ነባር ታጋይ፣ የደህንነት ምክትል ሃላፊ ፣ በአሁኑ ጊዜ በም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመብራት ሃይል የቦርድ ሰብሰባ የሆኑት  ዶ/ር ደብረ ጸዮን ገብረሚካኤል ስለአቶ ደበበ ምህረት ከሃላፊነት መነሳት  ” እሱም የሚመሰገነውን ያክል ጉድለትም እንደነበረበት ይረዳል። ከሃላፊነቱ ሲነሳም አልደነገጠም።” በማለት መናገራቸው ይታወቃል።  ምንም እንኳ ዶ/ር ደብረጺዮን አቶ ደበበ በብቃት ችግር እንደተነሱ አድርገው ለመገናኛ ብዙሀን ቢገልጹም፣ አቶ ምህረት ደበበ ግን በህወሃት ባለስልጣናት ስውር እጅ ሲቀነባበር የነበረውንና ኢትዮጵያን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንድታጣ ያደረገውን ከፍተኛ ሙስና ሲቃወሙ እንደነበር ለጠቅላይ ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ የቀረበው እና ለኢሳት የደረሰው የጸረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት ያስረዳል።
በ1999 እና በ2000 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ የሚረዱ ትራንስፎርመሮችን ለመግዛት ካወጣቸው አለም አቀፍ ጨረታዎች ጋር ተያይዞ በጨረታዎቹ ሂደት ላይ ግልጽነትና ኃላፊነት የጎደለው አሰራር መከሰቱንና ይህም የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን  ምርመራ በማድረግ የምርመራ ውጤቱን በወቅቱ በስልጣን ላይ ለነበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትት መለስ ዜናዊ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን  አገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮግራምን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛሉ በማለት የሥርጭት (Distribution) ትራንስፎርመሮችን ለመግዛት ሁለት ዓለም አቀፍ ጨረታዎችን ለማውጣት ዝግጅት ጀመረ። ጨረታዎቹ በኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎችና በጨረታ ገምጋሚ የኮሚቴ አባላት ይሁንታ አግኝተው አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በሁዋላ  የመጀመሪያው ጨረታ በ1999 ዓ.ም፣ ሁለተኛው ጨረታ ደግሞ በ2000 ዓ.ም እንዲወጡ ተደረገ፡፡የጨረታዎቹን መውጣት ተከትሎም መረጃው የደረሳቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጨረታው ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  በተለያየ ጊዜ ተደረጉትን ጨረታዎችም  “ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ ሊሚትድ” የተሰኘ  የሕንድ ኩባንያ አሸናፊ መሆኑ በወቅቱ በይፋ ተነገረ።
ኩባንያው የጨረታው አሸናፊ ተብሎ ይለይ እንጅ ባቀረበው ሰነድ ላይ የገለጸው የትራንስፎርመር ዓይነት ኮርፖሬሽኑ በጨረታው ሰነድ ላይ ሊገዛው ካሰበው ዓይነት ጋር የሚመሳሰል ሆኖ ሳይገኝ ቀረ፡፡ ይህ አልተጠበቀ ክስተት ደግሞ በግዥ ሂደቱ ውስጥ ገና ከጅምሩ የሙስና ወንጀል ድርጊት የተጠነሰሰ መሆኑን አመላከተ፡፡ ኮርፖሬሽኑ  በጨረታ ሰነዱ ላይ በግልጽ ያስቀመጠው የትራንስፎርመር ዓይነት “ሄርማቲካሊ ሲልድ” የሚል ሲሆን  የጨረታው አሸናፊ ኩባንያ  ባቀረበው የውል ማቅረብያ ሰነድ (ኦፈር) ላይ “ትራንስፎርመር ዊዝ ኮንሰርቫቶር ዩኒት” የተባለ ነው።
“ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ ሊሚትድ” ያቀረባቸው ሰነዶች ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ያወጣውን መስፈረት እንደማያሟሉ ሲታወቅ ፣ የነበረው የመፍትሄ አማራጭ ጨረታዎቹን አሸንፏል ተብሎ የተለየው ኩባንያ ያቀረበው ትራንስፎርመር በኮርፖሬሽኑ የጨረታ ሰነዱ ላይ የተቀመጠው መስፈርት (ሰፔስፊኬሽን) አያሟላም በሚል በአሰራሩ መሰረት በቴክኒክ ግምገማ ውድቅ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ላይ አቶ ምሀረት ደበበ ተቃውሞ ያሰማሉ፤ ይሁን እንጅ የኮሚቴ አባላቱ ተቃውሞውን ወደ ጎን በመተውና አዲስ ቃለ ጉበኤ በመያዝ ኩባንያው ትክክለኛ የትራንስፎርመ ዓይነት ይዘው ለውድድር ከቀረቡ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እንዲወዳደር በማድረግ በህገወጥ መንገድ ቀጣዩን የ ፋይናንስ ግምገማ ሥርዓት እንዲያልፍ አድረጉ፡፡ በዚህ አግባብ ኮርፖሬሽኑን ወክለው በጨረታው የተሳተፉ አካላትም ሆነ ጨረታውን አሸነፈ የተባለው ኩባንያ ባለቤት በኪራይ ሰብሳቢነት ስሌት ያልተገባ ጥቅም ለመቀራመት እየተንደረደሩ መሆኑን የሚያሳይ ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀረበላቸው።
የጨረታው ሂደት ቀጥሎ ኮርፖሬሽኑ እና የጨረታው አሸናፊ ኩባንያ በሚቀርቡ የትራንስፎርመሮች መጠንና በገንዘብ ጉዳይ ላይ ውል የሚዋዋሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ።  ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸውን ሁለቱን ጨረታዎች የተመለከተ የውል ሰነድ ተዘጋጅቶም በሁለቱም ወገኖች ተፈረመ።  የጨረታዎቹ አሸናፊ ነው የተባለው “ጉድላክ
እስቲል ቲዩብስ ሊምትድ” ኩባንያም ትራንስፎርመሮቹን በሰፕላየርስ ክሬዲት (supplier credit) እንደሚያቀርብ ተስማማ፡፡ በውሉ መሰረት ኩባንያው በአንደኛው ጨረታ ብዛታቸው 1950 የሆኑ የስርጭት ትራንስፎርመሮችን ወለዱን ጨምሮ በ8 411,946 የአሜሪካ ዶላር፤ በሌላኛው ጨረታ ደግሞ ብዛታቸው 3520 የሆኑ ትራንሰስፎርመሮችን ከነወለዱ በ17,695,686 የአሜሪካ ዶላር፤ በድምሩ ብዛታቸው 5470 የሆኑ ትራንስፎርመሮችን ወለዱን ጨምሮ በ 26 107 632 የአሜርካ ዶላር ለማቅረብ ስምምነቱ ተፈረመ።፡
የሁለቱ ጨረታዎች የመጀመሪያ ውሎች በዚህ መልክ በኮርፖሬሽኑና በጨረታው አሸናፊ ኩባንያ መካከል ይፈረሙ እንጅ በኩባንያው በኩል ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው መዘግየት የሚጠበቁ ውጤቶች ሊታዩ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ኩባንያው ገንዘቡን በራሱ ማቅረብ እንዳማይችልም ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡  ይህን የተረዱ የጨረታው ኮሚቴ አባላትና የኩባንያው ባለቤት መፍትሄ ይሆናል ብለው ያሰቡትን አማራጭ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ አውጥተው ካወረዱ በኋላም ሌላ አዲስ ውል ቢኖር የፋይናንስ ችግሩን ይቀርፋል በሚል ሀሳብ ተስማሙ፡፡  በአዲሱ ሀሳብ ላይ ተቃውሞአቸውን የገለጹት አቶ ምህረት ደበበ እራሳቸውን ለማግለል ጥያቄ ቢያቀርቡም በቀጥታ በውሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በጠ/ሚሩ ጽ/ቤት በኩል ትዕዛዝ ደረሳቸው።  ኩባንያው መጀመሪያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተፈራረመው ውል በአዲሱ ውል እንዲተካም ተደረገ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የተፈረመው የዚህ የአዲሱ ውል ዋና ፍሬ ሀሳብም የመጀመሪያው ውል ተቀይሮ ግዥውን ፋይናንስ የሚያደርግ ሌላ ሶስተኛ ወገን በውሉ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ የሚል ነው፡፡ በዚህ መሰረት ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር ከፍተኛ ቢዝነስ እንደሚሰራ የሚነገርለት “ኮብራ ኢንስታሌሽንስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር”  ግዥውን በገንዘብ አቅርቦት የሚደግፍ ተባባሪ (ፋይናንሲንግ አሶሺዬት)፣ “ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ” የትራንስፎርመሮቹ አቅራቢ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ደግሞ የትራንስፎርመሮቹ ገዢ በመሆን የሶስትዮሽ ውል እንደገና እንዲፈረም ተደረገ፡፡
ይሁን እንጅ ሌላ አዲስ ውል በሕንድ ኩባንያዎች መካከል መፈረሙም ታወቀ፡፡ ዉሉ በ“ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ”፤በ“ኮብራ ኢንስታሌሽንስ” እና ሌላ በሕንድ አገር ከሚገኘ የትራንስፎርመር አምራች የሆነ “ናሽናል ኤሌክትሪክ ኢክዩፕመንት ኮርፖሬሽን” በተሰኘው ኩባንያ መካከል የተፈረመ የሦስትዮሽ ውል ነበር፡፡ ኩባንያዎቹ ይህን ውል ሲፈራረሙ በኮርፖሬሽኑ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም እና የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ሥ/አስፈፃሚዎች የነበሩ ግለሰቦች በሚገባ የሚያውቁት ጉዳይ ቢሆንም ከኮርፖሬሽኑ እውቅና ውጭ መሆኑ ግን በምርመራው ተደርሶበታል፡፡ ከምርመራው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው ይህ ሁሉ አካሄድና ቀና ደፋ ደግሞ “ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ” የተባለውን ኩባንያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በሦስትዮሽ ከተፈራረመው ውል ማውጣት ነውና ይህም ተሳካለቸው፡፡ ስለሆነም “ኮብራ ኢንስታሌሽንስ” የተባለው ኩባንያ ከፋይናንሲንግ አሶሺዬት ወደ አቅራቢነት የውል ተቀባይ ወገን ተቀየረ፡፡
የኮርፖሽኑ የቀድሞው የስራ ሃላፊ አቶ ምህረት ደበበ  ከኮርፖሬሸኑ እውቅና ውጭ የተደረገው ውል ያለአግባብ መሆኑን በመገንዘብ “ጉድላክ እስቲል ቲዩብስ” የተባለ ኩባንያ ከውሉ መውጣት እንደማይገባውና ቀደም ሲል ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተፈረመው የሦስትዮሽ ውሉ ጽንቶ መቆየት አለበት በሚል ማሳሰቢያም ጭምር ለመስጠት ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁን እንጅ በአቶ ምህረት ደበበ የተሰጠውን ማሳሰቢያ የሚሰማ ጆሮ አልተገኘም፡፡ ይልቁንም ምርመራው እንዳረጋገጠው
ተጠርጣሪ የኮርፖሬሽ የሥራ ኃላፊዎች “ኮብራ” የተሰኘው ኩባንያ ትራንስፎርመሮቹን የማቅረብ የሕግ መሰረትና አቅሙ ሳይገመገም እንዲሁም የኮርፖሬሽኑን ይሁንታ ሳያገኝ በሚያዚያ ወር ም ለ“ሪዘርቭ ባንክ ኦፍ ኢንዲያ” በጻፉት ደብዳቤ ኩባንያዎቹ ከኮርፖሬሽኑ እውቅና ውጭ ለተፈራረሙት ውል ማረጋገጫ በመስጠት ኩባንያው ሕግን ባልተከተለ መንገድ የትራንስፎርመሮቹ አቅራቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ትራንስፎርመሮቹን የሚያቀርብ ኩባንያ ለመለየት የተጀመረው ድራማ በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩ የሚሆነው ደግሞ የግዥ አፈጻጸም ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡ በዚህ የግዥ አፈጻጸም ተግባር ውስጥ በኮርፖሬሽኑ የሲስተምና የደንበኞች አገልግሎት ድጋፍ ክፍል ኃላፊ እና የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ፕሮግራም ኢንጂነሪነግ ፕሮሰስ የስራ ሂደት ተወካይ የነበሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊ በዋናነት ተሳታፊዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የትራንስፎርመሮቹን ግዥ አፈጻጸም በተመለከተ “ኮብራ” የተሰኘው ኩባንያ ባለቤት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት ለኮርፖሬሽኑ ያቀረበውን የአፈፃፀም ዋስትና ተከትሎ ዋስትናው ውሉ በሚያዘው ፎርማት (ቅፅ) መሰረት ያልተዘጋጀ መሆኑን እያወቁ ሕጉ ከሚያዘው አሰራር ውጭ ኩባንያው እንዲያልፍ ረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሁለቱም ጨረታዎች በቀረቡ የአፈፃፀም ዋስትናዎች ላይ “… በግዥው አፈጻጸም ውስጥ የባንክ ዋስትና ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በዋስትና ሰጪው ባንክ የገንዘብ መጠየቂያ ደብዳቤ በሕንድ መንግስት ባንክ የሚሰጥ ሆኖ ፓሪስ በሚገኘው የናቲክሲስ የማድሪድ ቅርንጫፍ ባንክ ተቀባይነት ካገኘበት ቀን በኋላ ብቻ ነው” የሚል ይዘት ያለው ቅድመ ሁኔታ የሰፈረ መሆኑን እያወቁ እንዲሁም የኩባንያው ባለቤት ግዴታውን በውሉ መሰረት ሳይፈፅም ቢቀር ኮርፖሬሽኑ ወዲያውኑ የአፈፃፀም ዋስትናውን መውረስ የሚያስችለው መሆኑን እየተረዱ ይህን ሁኔታ ለሚመለከተው የኮርፖሬሽኑ አካል ሳያሳውቁ እንደ ዋዛ አልፈውታል፡፡
“ኮብራ” የተባለው ኩባንያ በበኩሉ ትራንስፎርመሮቹን ለማቅረብ “ጉድላክ” ከተባለው ኩባንያ ላይ የተረከበውን ኃላፊነት ሳይወጣ ጊዜ ነጎደ፡፡ ኮርፖሬሽኑም ትራንስፎርመሮቹ በወቅቱ መቅረብ እንዳልቻሉና ኩባንያው በውሉ መሰረት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳልሆነ መገንዘብ ችሏል፡፡ መገንዘብ ብቻም ሳይሆን ኩባንያው በዉሉ መሰረት ግዴታውን ሳይፈጽም ቢቀር የአፈፃፀም ዋስትናውን ለመውረስ የሚያስችለውን መብትም ለመጠቀም ሲባል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብዳቤ አቅርቧል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ያቀረበው የአፈፃፀም ዋስትና ውርስ ጥያቄ በባንኩ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ ለዚህ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ የአፈጻጸም ዋስትናው በቅድመ ሁኔታ የተገደበ መሆኑ ነው፡፡
በዚህ አግባብ ኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም ዋስትናውን መውረስ የማይችልበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ለኪሳራ ከሚዳረግ ይልቅ የሚቀርብለትን የትራንስርፎርመር ዓይነት ለመቀበል አጣብቅኝ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በእርግጥ ኮርፖሬሽኑ
ሊገዛ ያቀዳው የትራንስፎርመር ዓይነት ቀርቦለት፣ የአፈጻጸም ዋስትናውን መውረሱ ቀርቶ ትራንስፎርመሩን በተገኘ ጊዜ ለመቀበል ቢችል እንኳ ባልከፋ ነበር፡፡ አሁን ኮርፖሬሽኑ ከሁለት ያጣ እንደሚባለው ሆኗል፡፡ ወይ ገንዘቡን አሊያም በጨረታ ሰነዱ የገለጸውን የትራንስፎርመሮች ዓይነት ለማግኘት አልቻለም። የምርመራው ውጤት እንዳመለከተው በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊዎች የነበሩ በቁጥር ሰባት የሚደርሱ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች የጨረታው ገምጋሚ ኮሚቴ አባልትን ጨምሮ የ“ጉድላክ” እና የ“ኮብራ” ኩባንያዎች ባለቤቶች በአንጻሩ የማይገባቸውን ጥቅም ለመቀራመት የወጠኑትን ውጥን ከዳር ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
እነዚህ በሁለቱም ጎራ በጨረታው ላይ የተካፈሉ አካላት የጨረታውን ሂደት ፍትሃዊነት በማሳጣትና ግባቸውን ያልተገባ ጥቅም መቀራመት አደርገው በመንቀሳቀስ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ውሎች ውስጥ ኮርፖሬሽኑ ሊገዛ ካሰባቸው የትራንስፎርመር ዓይነቶች ውጭ እንዲቀርብ ሁኔታዎችን የማድበስበስ ተግባራትን መፈፀም ቀጠሉ፤ ቀደም ሲል በሁለቱም የጨረታ ሰነዶች ላይ የሰፈረውና ኮርፖሬሽኑ ሊገዛ ያሰበው የትራንስፎርመሮች ዓይነት “ሄርማቲካሊ ሲልድ” የሚለው ሲሆን ከዚህ መስፈርት ውጭ ከአቅራቢዎች ጎራ ሌላ ዓይነት መስፈርት ከመቅረቡም በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ አዲስ፣ ያላገለገሉ እና የቅርብ ስሪት የሆኑ የትራንስፎርመሮች ዓይነት እንዲቀርብለት ያስቀመጠውን መስፈርት ወይም ስፔስፊኬሽን ኩባንያዎቹ ባቀረቡት ሰነድ ላይ ሳይካተት ታልፏል፡፡
እነዚህ ተግባራት ተደማምረው ሕገ-ወጥ የግዥ አሰራር የበላይነትን ይዞ የጨረታ ኮሚቴ አባላትና የኩባንያዎቹ ባለቤቶች የማይገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማሳለጫ መንገድ እንደሆናቸው የምርመራው ውጤት ያስረዳል፡፡ የኩባንያዎቹ ባለቤቶችም ከጨረታው ገምጋሚ ኮሚቴ አባላትና በጨረታው ተሳታፊ ከነበሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ያመቻቹትን ይህን ሕገ-ወጥ አካሄድ በመጠቀም ኮርፖሬሽኑ የማይፈልጋቸው የትራንስፎርመሮች ዓይነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማደረጋቸውንም ምርመራው ያሳየናል፡፡
በጨረታው ተሳታፊ የነበሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ከትራንስፎርመሮቹ ጥራት ጋር በተያያዘ ጎልተው የታዩ ችግሮችን ለመሸፋፈን የተለያዩ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ ከዚህ አኳያም ትራንስፎርመሮቹ በሙያተኞች እንዲፈተሽ አድርገዋል፡፡ በውጤቱም የዛጉና የዘይት መንጠባጠብ የሚታይባቸው፣ የሲሊካ ጄል እና ከፍተኛ የመብረቅ መከላከያ የሌላቸው፣ የታፕ ቼንጀር ማስሪያ ብሎኖች የሌሏቸውና የተሰበሩ ትራንስፎርመሮች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትራንስፎርመሮቹ ኮርፖሬሽኑ ከሚፈልጋቸው ዓይነት ውጭ ከመሆናቸው በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው በተደረገው ምርመራ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከዚህም በመነሳት በጨረታው ሂደት ውስጥ በዋናነት ተሳታፊ የነበሩ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ስራ አስፈፃሚ፣ የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ሥ/አስፈፃሚ እንዲሁም የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም የቴክኒክ ክፍል ቡድን መሪ የነበሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ለ“ጉድላክ” እና “ኮብራ” ኩባንያ ባለቤቶች ደብዳቤዎችን ፅፈው ነበር፡፡ ውስጥ ለኩባንያዎቹ የጻፉዋቸው ደብዳቤዎች ይዘት ትራንስፎርመሮቹ በውሉ መሰረት ያልቀረቡ መሆናቸውን የሚገልጽ ሲሆን በነዚህ ደብዳቤዎች መሰረት የሥራ ኃላፊዎቹ ለኮርፖሬሽኑ ጥቅም ውግንና ያሳዩ ይመስላል፡፡
ይሁን እንጅ የምርመራ ውጤቱ እንደሚጠቁመው እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች ለኮርፖሬሽኑ ያሳዩ የሚመስለው ውግንና ዘለቄታ አልነበረውም፡፡ ከ2001 ዓ.ም በኋላ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከኩባንያዎች ጋር በተጻጻፉት ደብዳቤዎች መሰረት ትራንስፎርመሮቹ እንዲቀየሩ ከማድረግ ይልቅ በኩባንያዎቹ የቀረበላቸውን የጥገና መርሃ ግብር ተቀብለውና አፅድቀውት በመላክ ትራንስፎርመሮቹ ያለአግባብ እንዲጠገኑ አድርገዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በኮርፖሬሽኑ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የኢንጂነሪንግ ክፍል እና የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የሳፕላይ ቼይን የሥራ ኃላፊዎች ትራንስፎርመሮቹ ብልሽት ያለባቸው ሆነው እያሉ ሙሉ በሙሉ እንደተጠገኑና ስራ ላይ እንደዋሉ በመግለፅ፣ አንድ ጊዜ እንዲጠገኑ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲተኩ በሚል ያለ በቂ ሙያዊ ፍተሻ ተገቢ ያልሆነ የውሳኔ ሃሳብ በመስጠትና የውስጥ ማስታወሻዎችን በመጻጻፍ ትራንስፎርመሮቹ በአዲስ እንዳይተኩ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በግዥው ሂደት ውስጥ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘትና ለኩባንያዎቹ ባለቤቶች ለማስገኘት በማሰብ በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ተካፋይነት በሚፈፀም ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በድርጊቱ ውስጥም በስልጣን ያለአግባብ መገልገል፣ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት እና ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ድርጊቶች የተፈጸሙ መሆናቸው ታይቷል፡፡ በዚህ አግባብ በተፈጸሙ ብልሹ አሰራሮች ሳቢያ በአገር ጥቅም ላይ ከ26 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱም ተጠቅሷል፡፡  ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰባት የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ በአራት የጨረታ ኮሚቴ አባላትና የ“ጉድላክ” እና የ“ኮብራ” ኩባንያ ባለቤቶች ላይ ተገቢውን ማስረጃዎች አሰባስቦ በሁለት የክስ መዝገቦችና በስድስት ክሶች በማጠናቀር ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ቀርቧል፡፡ የአቶ ምህረት ደበበ የስልጣን ዝውውር የጀርባ ፍጥጫ ሌላው የግምገማ ታሪክ ይህን ሲመስል፣ በተፈጠረው አለመግባባት ስራውን በአግባቡ እንድመራው በወጣው ህግ እና ደንብ መመራት አልቻልኩም ሲሉ ያቀረቡት መልቀቂያ ጥያቄ በዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ተቀባይነት አግኝቶ ምንም በቂ ሃላፊነት ወደ ሌላው የጠቅላይ ሚ/ሩ አማካሪነት እንዲዛወሩ ተደርጓል።
አቶ ምህረት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እና የሙስናውን ድራማ ከጀርባ ሆነው ሲመሩት የነበሩት ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆኑት የህወሀት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ሳይውሉ፣ በመካከለና የአመራር ቦታ ላይ ያሉ የተወሰኑ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። በቅርቡ  አንድ የህንድ ኩባንያ የኤልክትሪክ ኮርፖሬሽንን ማኔጅመንት ለመምራት ውል መዋዋሉ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment