Wednesday, December 25, 2013

በጥንቆላ ተግባር ተሰማርቶ የነበረው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ


አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 16 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህመም አድናለሁ፣ከደባል ሱስ እገላግላለሁ እና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን እፈፅማለሁ በማለት በጥንቆላ ተግባር ተሰማርቶ ከተለያዩ ሰዎች ጥሬ ገንዘብና ወርቅ ያጭበረበረው ግለሰብ በ 8 ዓመት እስራት ተቀጣ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ውንጀል ችሎት በተከሳሹ ተፈሪ ንጉሴ ላይ የ8 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም አስተላልፎበታል።
በቡራዩ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ39 ዓመቱ ንጉሴ ታህሳስ 14 ቀን 2005 ዓ.ም  ወይዘሮ መሰረት ታዬ የተባሉትን የግል ተበዳይ አሁን ካንቺ ጋር ያለው ሁለተኛ ባልሽ  ጥር 30 ቀን ይሞታል፥ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን 500 ሺህ ብር  ስጪኝና ከሞት ላድነው በማለት 300 ሺህ ብር የግል ተበዳይ ለመስጠት በመስማማት ብሩን እንደወሰደ የአቃቤ ህግ በክስ ያስረዳል።
በተጨማሪም ከተበዳይ ወይዘሮ መሰረት ላይ 130 ሺህ ብር የሚያወጣ የጆሮ እና የአንገት ወርቅም እንደወሰደ በክሱ ተካቷል።
በተመሳሳይ ወይዘሮ አፀደ ስንታየሁን ባልሽ ካለበት ደባል ሱስ አላቅቀዋለሁ በማለት ለማሳመኛ የተለያዩ የማሳሳቻ ድርጊቶችን በመጠቀም 50 ሺህ ብር እና 21 ካራት የሆነ 8 ግራም የወርቅ የአንገት ሃብል መውሰዱንም አቃቤ ህግ ለችሎቱ በክሱ አስረድቷል።
3ኛ ተበዳይ ከሆኑት ወይዘሮ አመናይ ከበደን ከህመምሽ እፈውስሻለሁ በማለት ካልተያዘ ግብረ አበሩ ጋር 100 ሺህ ብር እና 76 ግራም የተለያዩ  መጠን ያላቸው ወርቆችን ወስዷል ሲልም አቃቤ ህግ በክሱ አካቷል።
በአቃቤ ህግ በ3 የማታለል ክሶች የተመሰረተበት ተፈሪ ንጉሴ ያቀረበው የመከላከያ ማስረጃ የቀረበበትን ክስ ጥርጣሬ ውስጥ መክተት ባለመቻሉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ውንጀል ችሎት ጥፋተኛ  ሲል  በ8 ዓመት እስራት ቀጥቶታል።
በጥላሁን ካሳ

No comments:

Post a Comment