Sunday, December 29, 2013

ጃዋርና ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ክፍል 3)

December 29, 2013

ከዓለማየሁ መሀመድ (ክፍል 3)
Jawar Mohamed Muslim fundamentalistአቧራው ጬሷል። ግለቱ ጨምሯል። ሙቀቱ አይሏል። የሳይበሩ ጦርነት ተጋግሏል። በሁሉም ወገኖች ትርፍና ኪሳራው ገና አልተሰላም። ከመነሻው ትርፋማ መሆኑ የተረጋገጠለት ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ዘና ፡ ከወንበሩ ለጠጥ ብሎ በትዝብት ፈገግታ ሁለቱን ወገኖች ይመለከታል። ቢቻለው ካራ አቀብሎ የፌስ ቡኩ ጦርነት ደም ወደ ሚያፋስስ ዕልቂት ቢቀየርለት ምንኛ በመረጠ?!
በእርግጥ እያሰበበት ነው። የመረጃ ምንጮቼ ሹክ እንዳሉኝ ከሆነ የህወሀት ስሌት እስከ እልቂቱ የሚሻገር ነው። ሰሞንኛዋ ግርግርም አራት ኪሎ ቤተመንግስ ተቀምራ፡ ዋሽንግተን ዲሲ በህወሀት ኤምባሲ ተከሽና በእነ ጃዋር መሀመድ ታውጃ፡ ሺዎች በደመነፍስና በስሜታዊነት የተቀላቀሉት ስለመሆኑ ከበቂም በላይ መረጃው አለኝ።
ለዛሬ መረጃዎቹን ላካፍላችሁ። ማስረጃዎቹን እየጠበኩኝ ነው። የድምጽና የፎቶግራፍ ማስረጃዎቹ ከእጄ እንደገቡ ጀባ እንደምላችሁ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ። በእርግጥ አንድ ላይ ላወጣቸው ነበር እቅዴ። ሆኖም የጬሰው አቧራን እየቃሙ ላሉት ወገኖች በተወሰነ ደረጃ ሰከን እንዲሉ፡ ሰማይ ምድሩን የበጠበጠው ንትርክ የኦሮሞ ህዝብን ብሶት ለመግለጽ ታስቦ  ሳይሆን በህወሀት መንደር ተዘጋጅቶ የቀረበ መርዛማ አጀንዳ መሆኑን በቶሎ እንዲያውቁት በሚል መረጃዎቹን ብቻ ላፈነዳቸው ፈለኩ። ሁለት ናቸው
መረጃ አንድ
ፋይሳል አልዬ ዓመታት የዘለቀ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ አባል ነው። እሳት የላሰ ካድሬ ይሉታል። ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ሰዎች ምቾት የሚሰጣቸው፡ በኦሮሚያ ክልል  ወጣቱ ለህወሀት ቀጥ ለጥ ብሎ  እንዲገዛ የቤት ስራቸውን በሚገባ የሚሰራላቸው በመሆኑ ፋይሳል በህወሀት መንደር ስሙ ወፍራም ነው። ወጣት ነው። ምላሱ ጤፍ ይቆላል የሚባልለት ዓይነት ነገር።
ጃዋርን ለመመልመል ጊዜ አልወሰደበትም። ጎረምሳው ጃዋር ከአከባቢው የነቃ፡ ነገር በቶሎ የሚገባው ስለነበረ የፋይሳል ቀልብ ውስጥ የገባው በጠዋቱ ነው። በእድሜም እኩያሞች የሚባሉ ናቸው። እናም ጎረምሳው ጃዋር፡ ሰተት ብሎ ኦህዴድን ተቀላቀለ። ኦህዴድ የበኩር ልጆቿን መልምላ ከጨረሰች በኋላ ለተለያዩ ተልዕኮዎች ማሰማራት ጀመረች። ጃዋር በአዲስ አበባ ቆይታው ውሎው ዶሮ ማነቂያ አከባቢ ካሉ ጫት ቤቶች ነበር። ጃዋርና ምልምል የኦህዴድ ካድሬዎች ብዙውን ጊዜ የስለላ ስራዎችን የሚያከናውኑት በዶሮ ማነቂያ አከባቢ በተሰገሰጉ ጫት ቤቶች ነበር። ጫቱን እያመነዥጉ ወሬ ሲለቃቅሙ መዋል የእነ ጃዋር መደበኛ ስራቸው ነበር።
በዚህን ጊዜ ወጣቱ ፋይሰል ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የህወሀት ኤምባሲ ይዛወራል። ምሳዩን፡ እኩያውን፡ በግብርም በምግባርም የሚመስለውን ወዳጁን ጃዋርን ተስፋ ሰጥቶት ወደ ዲሲ ይበራል። ጃዋር እዚያው ጨፌ ኦሮሚያ ውስጥ ድርጅታዊ ተልዕኮዎችን እየተወጣ እያለ በመሃል ከወዳጁ ፋይሳል ጥሪ ይደርሰዋል። በትምህርት እድል ሰበብ ጃዋር ወደ አሜሪካ የሚመጣበት አጋጣሚ ይፈጠርለታል።
ለጃዋር የምስራች የነበረው ዜና እንደመጣች በኦህዴድ አማካኝነት ህወሀት ተልዕኮ ማዘጋጀት ጀመረ። የዲያስፖራውን ፖለቲካ ለመበጥበጥ፡ ጊዜ እየጠበቀ እንዲያተራምሰው የሚያስችል የቤት ስራ ተዘጋጀና በዋሽንግተኑ ፋይሳል መሪነት እንዲከናወን ህወሀት አዘዘ። ጃዋርን ይሄን ተልእኮ ሰንቆ ዋሽንግተን ዲስ ከተፍ አለ።
የህወሀት ኤምባሲ የጃዋር መሸሸጊያ ሆነ። ጠዋት ነግቶ ኤምባሲ ይገባል። ከፋይሳል ጋር ሲሰራ ይውልና ማታ ጸሀይ ስትጠልቅ ኤምባሲው አከባቢ ወደተከራዩለት መኖሪያው ይሄዳል። ለአንድ ዓመት ያህል በዚህ ሁኔታ ዘለቀ። አሁን ከወያኔ መንደር የተሰናበተው ብርሃኑ ዳምጤ አባመላ የቅርብ ግንኙነት ነበረው። ሻይ ቡና የሚባባሉት እነዚሁ የኤምባሲው ሰራተኞችና ባለልዩ ተልእኮ አስፈጻሚዎች ነበሩ።
ሁኔታዎች በዚሁ እየቀጠሉ እያለ ጃዋር ከሚኒሶታ የኦሮሞ አንድ ማህበር ጥሪ ይደረግለታል። ወንበር እያሞቁ መዋልና ማደር የሰለቸው ጃዋር ለሚኒሶታው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት አልዘገየም። ጓዙን ጠቅልሎ ሚኒሶታ ገባ። ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች ተቀባበሉት። ህወሀት ያዘጋጀው፡ ኦህዴድ ያስጠናው ተልኦኮ ለጊዜው አደጋ ገጠመው። የኦነግን የ40 ዓመት ሙዚቃ በቅርበት ለመኮምኮም ዕድል ያገኘው ጃዋር በሚኒሶታ ውርስ ነበር የጠበቀው። ያረጀውን፡ የሻገተውን የኦነግን ፍልስፍና አፈሩን አራግፎ ለማንሳት ቃል የገባው ጃዋር በዋና ጊዜው ትምህርት እየተከታተለ፡ በትርፉ ደግሞ የኦነግን ዜማ እያቀነቀነ የሚኒሶታውን ህይወት ጀመረው።
እነፋይሳል የጃዋር መክዳት ብዙም ያሳሰባቸው አይመስሉም። የተሸከመውን አደራ ሳይወጣ፡ ኮትኩታ ያሳደገችውን፡ ለወግ ማዕረግ ያበቃችውን ኦህዴድን(ህወሀት) ለጊዜው ተለይቷታል።
ፋይሳል በመሃሉ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል። በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትልቅ የሃላፊነት ቦታ ተሰጥቶት መስራት ይጀምራል። ጃዋር ደግሞ በዲያስፖራው ውስጥ እንዴት መሰስ ብሎ  መግባት እንዳለበት ሂሳብ ማስላት ጀመረ። በልቡ ውስጥ የኦነግን ነፍስ ተሸክሞ ወደ ተቀሩት ኢትዮጵያውያን መጠጋት ያዘ። እንደ ቪኦኤ፡ ዶቸቬሌ፡ ኢሳት የመሳሰሉ ሚዲያዎች ላይ ቀርቦ ሲናገር በእርግጥ እኔን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጃዋር አልጎረበጣቸውም ነበር።
ጃዋር እዚህም እዚያም ይናገራል። ይጽፋል። ህወሀትን ያወግዛል። ኦህዴድን ይረግማል። በቃ! እውነተኛ ተቃዋሚ የሚል ታርጋ ተለጠፈለት። ወጣቱ የፖለቲካ ምሁር እየተባለ ይጠራም ጀመር።
ነገሮች ጃዋር ባሰባቸው መልኩ እየሄዱ ናቸው። እናት ድርጅቱን ኦህዴድን ለጊዜው ከድቷል። በልቡ የቀበረው የኦነግ ፍልስፍናም እዚያው ተዳፍኖ ይቀመጣል። ቀን ሲመጣ ሁለቱ ተስማምተው ይወጣሉ። የጃዋር ህልም እናት ድርጅቱን ኦህዴድንና የነፍሱ ማረፊያ የሆነውን ኦነግን ማጋባት ነው። ለዚህ ደግሞ ስሙን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መተከል አለበት። እያደረገው ዘለቀ።
እነፋይሳል ጸጥ ብለዋል። ጃዋር መጨረሻው ከየት እንደሆነ ያውቁታል። አስረዝመው አሰሩት እንጂ ፈተው አለቀቁትም። ጃዋርም ይህቺን ልቅም አድርጎ ያውቃታል። አንድ ቀን ወደ እናት ድርጅቱ እንደሚመለስ ያም ቀን እየቀረበ እንደመጣ ተረድቷል።
ፋይሳል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ሌላ ከፍተኛ ሃላፊነት ተሰጠው። የዲያስፖራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር። ጃዋር አልጀዚራ ላይ ቀርቦ ኦሮሞ ፈርስት ብሎ አውጇል። ከዚያም በፊት በሚኒሶታ አንድ መድረክ ላይ የሜንጫ አብዮት ቀስቅሷል። ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ተለይቶ ወደ ጽንፈኛው የኦሮሞ ጎራ ጠቅልሎ ገብቷል። አቧራው መጬስ ጀምሯል።
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ፈተና ውስጥ ገብቷል። ከሀገር ቤትና ከባህር ማዶ የለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ነው። ዲያስፖራው ወያኔን በየመድረኩ ማሳፈር፡ ማባረር ጀምሯል። የህወሀት ወንበር እየተነቃነቀ ነው። ዲያስፖራው የማይገፋ ተራራ ሆኗል። እነፋይሳል አሁን መነቃነቅ አለባቸው። ጃዋር የሚባል በዲያስፖራው ላይ የዘመተ ሃይል ተነስቷል። ፋይሳል ስልኩ አነሳ። ኢሜይሉን ከፈተ:: ….ጃዋር;;
መረጃ ሁለት
በኒውዮርክ የሚገኘው በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተልእኮ ጽህፈት ቤት ብዙ ሰራተኛ የለውም። አምባሳደሩ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ ለይስሙላ ይቀመጡ እንጂ እውነተኛ ስልጣኑ ያለው በሁለት ሰዎች እጅ ነው። ኮነሬል ገብሬ ገብረጻዲቅ የወታደራዊ አታሼውና የጽህፈት ቤቱ አንደኛ ጸሀፊ አቶ ኪዳነማርያም ግደይ የህወሀት ልዩ ተልእኮ አስፈጻሚ ናቸው። ዶክተር ተቀዳ ፕሮቶኮል ጠብቀው በየስብሰባው ይገኛሉ። እነኮነሬል ገብሬና ኪዳነማርያም ዋሽንግተን ዲሲ ካለው ኤምባሲ ጋር በመሆን የስለላና ሌሎች ድርጅታዊ ስራዎችን ያከናውናሉ።
ተቃዋሚዎችን በመሰለል፡ በገንዘብ እየሸነገሉ በማስከዳት፡ የተለያዩ ተለጣፊ ድርጅቶችን በማቋቋም የዲያስፖራውን እንቅስቃሴ የማዳከም ሃላፊነቱ እነዚህ ሁለቱ የህወሀት ሰዎች ላይ ወድቋል።
ጊዜው ለህወሀት ከባድ ሆኗል። ተቃውሞው በየቦታ ጠንከር ብሎ ተነስቷል። ህወሀት አደጋ ውስጥ ነው። እነኮነሬል ገብሬ የቤት ስራ ተሰጥቷቸዋል። ዲያስፖራው መበጠበጥ አለበት። ዘረኝነት ክፉ ነው። የኦሮሞ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ራሱን ተጠቂ አድርጎ  የሚኖር በተለይ በአማራው ላይ ቂም ቋጥሮ የተቀመጠ ነው የሚል ድምዳሜ ህወሀት ዘንድ አለ። እናም ይሄን መቀስቀስ አንዱ ህወሀት እፎይታ የሚያገኝበት መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ሰው ጃዋር ነው። ኮነሬል ገብሬ ስልካቸውን አነሱ። ጃዋር የሚኖረው እዚያው እሳቸው ካሉበት ከተማ ነው ኒውዮርክ።
ፋይሰል ከአዲስ አበባ ይደውላል። ኮነሬል ገብሬ ከኒውዮርክ ስልኩን እየመቱ ናቸው። ሁለቱም ከአንድ ቦታ ነው የሚደውሉት። ጃዋር ዘንድ።
ጃዋር አሁን ስራውን ጀመረ። የእናት ድርጅቱን ውለታ ለመመለስ ተዘጋጀ። አቧራውን አጬሰው። እንደተፈለገው እንደታቀደው የኦሮሞ ማህበረሰብ ብድግ አለ። ጽንፈኛው ሆ ብሎ ተነሳ። ህወሀት ለጊዜው እፎይ ያለ መስሏል።
በመረጃ ደረጃ ያገኘሁት እንደሚያመለክተው ጃዋርን ጨምሮ የተወሰኑ የኦነግ መሪዎች አዲስ አበባ ይገባሉ። ለዚህም አባዱላ ገመዳ እና ግርማ ብሩ ስራውን እየሰሩት ነው። ምናልባትም በቅርቡ ጃዋርና የኦነግ መሪዎቹ ኦህዴድን ይዘው ብቅ ሊሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
እንግዲህ ይህ መረጃ በማስረጃ ተደግፎ ይመጣል። እነጃዋር ከህወሀት ጋር የፈጸሙት ጋብቻ ኢትዮጵያን በመበጥበጥ ላይ ያተኮረ ነው። ጊዜውን ልብ በሉ። ህወሀት ተዳክሟል። እያጣጣረ ያለውን ስርዓት ወደ መቃብሩ ሸኝቶ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነው እነጃዋር የዘረኝነት ካርድ አንስተው ህወሀትን ለማዳን ወገባቸውን ታጥቀው በማህበራዊ መድረኮች ላይ የዘመቱት።
ዘረኝነት ልብንም አይንንም ያውራል። የሰከነ ውይይት ለማድረግ የሚፈቅድ ትዕግስት አይሰጥም። በእርግጥ የተነሳው አቧራ ይጠፋል። ሰማዩም ይጠራል። እነጃዋር ለህወሀት ከቆሙለት ዓላማ ጋር በታሪክ ጥቁር ስም ታቅፈው ይኖሩዋታል። መልካም ንትርክ!!
source http://ecadforum.com

No comments:

Post a Comment