Tuesday, December 3, 2013

የኢህአዴግ የድርድር ጥያቄና የግል እይታዬ – ከፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)


December 3/2013

አንድ፣ ኢሳት ፣ ኢህአዴግን እና ግንቦት7ትን የተመለከተ ዘገባ ካቀረበ በሁዋላ አንዳንዶች ዜናውን ሲጠራጠሩት ተመልክቻለሁ፣ ያሽሟጠጡም አልታጡም። መጠራጠርም፣ ማሽሟጠጥም የሰውልጅ ባህሪ በመሆኑ አልገረመኝም። ትንሽ የገረመኝ አንዳንድ “ጋዜጠኞች” መረጃውን ካገኙ በሁዋላ በራሳቸው መንገድ አጣርተው ሀቁን ማውጣት ሲችሉ እነሱም እንደሌላው መልሱን በማንኪያ እንዲቀርብላቸው መፈለጋቸው ነው። ጋዜጠኛ “ጥቆማ” ከተሰጠው ተመራምሮ፣ የምርምር ስራውን ይጽፋል እንጅ እንደ አንባቢ መልሱ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት አይጠብቅም፣ ጥያቄ መጠየቅማ ማንም ይጠይቃል፣ ጋዜጠኛን ጋዜጠኛ ወይም ተመራማሪ የሚያደርገው ለጠየቀው ጥያቄ ላይ ታች ብሎ መልስ ማቅረብ ወይም በአሰባሰባቸው መረጃዎች ላይ ተንተርሶ ትንተና መስጠት ሲችል ነው ( በሁለተኛው መስፈርት መሰረት ተመስገን ደሳለኝን እና በእስር ላይ የሚገኘው ውብሸት ታየን አደንቃለሁ)።
ሁለት፣ ዜናውን እንደሰማሁ መጀመሪያ የመጣልኝ ጥያቄ “እና ምን ያስገርማል?” የሚለው እንጅ፣ “ድርድሩ የተጠየቀው መቼና በእነማን በኩል ነው?” የሚለው አልነበረም። የአለም የፖለቲካ ታሪክ በግጭትና በድርድር የተሞላ ነው። “ድርጅቶች ይጋጫሉ፣ ይደራደራሉ፣ ምን ያስገርማል?”፣ በፖለቲካ ትግል” በመቃብሬ ላይ ..” የሚባል ነገር የለም። “ለምን ሰበር ዜና ሆነ ታዲያ?’ እንዳትሉኝ፣ ሰበር ዜና ማለት አስገራሚ የሆነ ዜና ማለት አይደለም ።
ሶስት፣ ቀጥሎ የመጣልኝ ጥያቄ “ኢህአዴግ ከግንቦት7 ጋር መደራደር ለምን ፈለገ?” የሚለው ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ” የፖለቲካ ድርጅቶች የእንደራደር ጥያቄ የሚያቀርቡት መቼ ነው?” የሚለውን ማየት ነበረብኝ። የፖለቲካ ድርጅቶች በአብዛኛው ለድርድር የሚቀመጡት ህልውናቸውን ለማቆየት ወይም ተደራድሮ የሚገኝ ጥቅም ሳይደራደሩ ከሚገኝ ጥቅም ( ጉዳት) የተሻለ ሆኖ ሲያገኙት ነው። በዚህ ንድፈሀሳብ ላይ ተመስርቶ ኢህአዴግ እና ግንቦት7 አሁን ያሉበትን ቁመና መፈተሽ ይገባል። ኢህአዴግ ከመለስ በሁዋላ ኢህአዴግ አለመሆኑ ይታወቃል።ሊቀመንበሩ ድርጅቱን ይዞ ለመቀጠል ተቸግሯል፣ (ምናልባትም በቅርቡ ይፋ የሚሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አጋጥሞታል)፣ የ ህዝቡ ልብ እንደሸፈተ አውቋል፣ ወጣቱ ለውጥ እንደሚፈለግ ተረድቷል፣ ሰራዊቱ የሚተማመንበት ሀይል እስኪያገኝ እንጅ እንደሚከዳው ተገንዝቧል። በአጠቃላይ መጪው ጊዜ ለኢህአዴግ ብሩህ አለመሆኑን ግንባሩ ጠንቅቆ ያውቃል። በዚህ አደጋ ውስጥ ሆኖ ጊዜ ለመግዛትና ድርጅቱን ለማጠናከር የድርድር ጥያቄ ቢያቀርብ አይገርምም።
ግንቦት7 ለኢህዴግ “አጣዳፊ ጠላት” (immediate threat) ሆኗል እያልኩ አይደለም፣ ነገር ግን እምቅ ጠላት ( potential threat) መሆኑን አልጠራጠርም ። አንድ ድርጅት ለሌላው ድርጅት አጣዳፊ ጠላት የሚሆነው ፣ አሁን ባለበት ሁኔታ፣ ከተቃራኒው ድርጅት የበለጠ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የሀይል ሚዛን ሲኖረው ነው። ግንቦት7 ኢህአዴግን ዛሬውኑ ለማስወገድ አይችልም ምክንያቱም ከኢህአዴግ የሚበልጥ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ ሀይል የለውምና ፤ ነገር ግን በጊዜ ሂደት እንደሚያስወግደው መገመት ይቻላል፣ ከመለስ በሁዋላ ያለውን ሁኔታ ብታጠኑ የኢህአዴግ የሀይል ሚዛን ወደ ታች እየወረደ፣ በአንጻራዊ መልኩ የግንቦት 7 የሃይል ሚዛን ደግሞ ወደ ላይ እየወጣ ነው፣ የ ግንቦት7 መሪዎች በዚህ አመት የሀይል ጥቃት እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል፣ በዚህ አመት ቀርቶ በሚቀጥሉት 3 አመታት ጥቃት ከፈጸሙ እያደጉ መሆኑን የሚያሳይ ነው ( 4 ፓይለቶች መክዳታቸውንም አንዘንጋ)። የፖለቲካ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ሁለት አይነት ሀይል አለ። አንዱ መቺው ሀይል ( hard power) ሲሆን ሌላው ደግሞ መለስተኛው ሀይል ( soft power) ነው። መቺው ሀይል የሚባለው ወታደራዊው ሀይል ነው። በዚህ በኩል ኢህአዴግ ከግንቦት7 በብዙ እጅ የሚልቅ ጉልበት አለው። ነገር ግን ግንቦት7ትም በዚያው ጎዳና እየተጓዘ መሆኑን መርሳት የለብንም።
መለስተኛ ሀይል (soft power) የሚባለው ደግሞ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎችን፣ ጥራት ያለው የሰው ሀይልን ( መሪም ተከታይም)፣ ህዝባዊ ድጋፍ ፣ የካፒታል አቅም ፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የመሳሰሉትን ያካትታል። ግንቦት7 በዚህ በኩል ከፍተኛ ጉልበት መገንባቱን መመስከር ይችላል። ከኢህአዴግ ተመጣጣኝ የሆነ ካፒታል ባይኖረውም፣ ከሌሎች ድርጅቶች የተሻለ ካፒታል( ገንዘብ)እንደሚኖረው ከስራዎቹ መገመት ይቻላል ። የተማሩ ሰዎችን በመያዝ በኩልም፣ ከኢህአዴግ ቢበልጥ እንጅ አያንስም። በፕሮጋንዳውና በህዝብ ድጋፍ በኩልም እንዲሁ። እንዲያውም የግንቦት7 የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች ከኢህአዴግ የተሻሉ ለመሆናቸው ብዙ አስረጅ አይጠይቅም፣ የግንቦት7 ራዲዮና ዌብሳይት እስከዛሬ ሳያቋርጥ እየሰራ ነው፣ ጠንካራ የፓልቶክ ደጋፊዎችም አሉት። ኢህአዴግ ራሱ የሚሰራላቸው ፕሮፓጋንዳም ቀላል አይደለም። ኢህአዴግ ቢያንስ በውጭ ያለውን ድጋፉን፣ በተለይም ለጀመራቸው የአባይ እና ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ገንዘብ ለመለመን ሲል ግንቦት7ን ለድርድር ቢጠይቀው አይገርምም። ኢሳት የግንቦት7 ነው ብሎ ስለሚያስብም፣ ኢሳትን እንዲያስቆምለት ልደራደርህ ቢል አሁንም አይገርምም። (በኢሳት ላይ እንኳ ቀልድ የለም፣ መደራደር ከፈለገ ከኢሳት ጋር እንጅ ከግንቦት7 ጋር ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም ግንቦት7 ስለኢሳት ምንም የሚያገባው ነገር የለምና፣ ከኢሳት ጋር ድርድር ከተጀመረም ለኢሳት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ዙሪያ እንጅ፣ ከስራው ጋር የተያያዘ እንደማይሆን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ)
አራት፣ ኢህአዴግ ከግንቦት7 ጋር ብቻ ነው ወይ ድርድር የመረጠው? እኔ ባለኝ መረጃ ኢህአዴግ በእነ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅ በኩል ላለፉት 4 ወራት ከእነ አቶ ሌንጮ ለታ ድርጅት ጋር ሲነጋገር ነበር። ይህን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ከኦብነግ ጋርም እንዲሁ ተደጋጋሚ የድርድር ጥያቄዎች ቀርበዋል። እነዚህ ድርጅቶች በፓርላማ “አሸባሪ” የተባሉ ናቸው። እና ለግንቦት7 ጥያቄ ቢያቀርብ ምን ይደንቃል? ፖለቲካ እኮ ፊት ለፊት የምትናገርውና በውስጥ የምታደርገው የተለየ ነው። That is politics. በነገራችን ላይ ” አንደኛው የአለም ጦርነት የተጀመረው በድብቅ በሚካሄድ ፖለቲካ የተነሳ ነው” ተባለና ፖለቲካ ግልጽነት እንዲኖረው ተብሎ አዲስ አስተሳሰብ ለረጅም ጊዜ ተራመደ። ፖለቲካ ግን ዛሬም ፊትና ጀርባ እንደያዘ ቀጥሎአል።
አምስት፣ “ጥያቄው በእነማን በኩል ቀረበ?’ የሚለውንም ለራሴ አንስቻለሁ። የድርጅቱ መሪዎች መልሱን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፣ ነገር ግን የራሴን ግምቶች አስፍሬአለሁ። አንድ፣ በቅርቡ በእነአቦይ ስብሀት የተመራ ቡድን አሜሪካ ከርሞ ሄዷል። ሁለት፣ ፕ/ር ኤፍሬም አሜሪካ ከርመዋል፣ ኦነጎችን ለማስታረቅም ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል። ሶስት፣ በቅርቡ የአውሮፓ እና የካረቢያን አገሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፣ ብዙ ዲፐሎማቶችም አዲስ አበባ ነበሩ። አራት፣ ኖርዌይና ሆላንድ ሁሌም ተቃዋሚዎችን ለማቀራረብ ይሰራሉ። ይዋል ይደር እንጅ ትክክለኛውን መልስ እናገኛለን። መልሱ ግን ከጠቀስኳቸው ሰዎች ወይም አገሮች በአንዱ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። የእንደራደሩ ጥያቄ ለመቅረቡ ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ። እስከዛው እንደ ጋዜጠኛ መላ ምት በማስቀመጥ ምርምራችን መቀጠሉ ተገቢ ነው።
ስድስት፣ ግንቦት7 ለምን ይህን ድርድር ይፋ ማድረግ ፈለገ? ኢህአዴግ አስቀድሞ በኢቲቪ ” ከግንቦት7 ጋር ሲያደርግ የነበረው ድርድር ከሸፈ” ብሎ መግለጫ ቢሰጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት? የግንቦት7 ደጋፊዎች የድርጅቱን መሪዎች በጥሩ አይን የሚያዩዋቸው አይመስለኝም፤ ግንቦት7ትም ውስጥ አለመተማመን ይፈጠርና ድርጅቱን ከሁለት ሊከፍለው ይችል እንደነበር መገመት ይቻላል፣ ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚል ድርጅት ከአባሎቹና ከህዝቡ የሚደብቀው ነገር መኖር የለበትም። ግንቦት7 በመግለጫው “ድርድር መደረግ ካለበት ከሁሉም ድርጅቶች ጋር ነው፣ ሁሉንም ነገር ግልጽ እናደርጋለን የምንደብቀው የለንም” ብሎአል። ትክክል ነው። እውነተኛ ድርድር ሲጀመር ለጊዜው ይፋ የማይወጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ድርድር ተጠየቅሁ ብሎ መግለጫ መስጠቱ ግን የሚገርም አይመስለኝም። ግንቦት7 መረጃውን ከኢህአዴግ ቀድሞ ይፋ ማድረጉ ድርጅቱን ከመከፋፈል ማዳን ብቻ ሳይሆን ንቅናቄው ከኢህአዴግን አንድ እርምጃ ቀድሞ የ ሚያስብ መሆኑን ለማሳየትም ጠቅሞታል።
በአገር ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች በኢህአዴግ በኩል ያለውን መልስ ይዘውልን እንደሚቀርቡ ተስፋ እናድርግ።

No comments:

Post a Comment