Tuesday, December 3, 2013

በዱራሜ ከተማ በተነሳ ግጭት በርካታ ሰዎች ተጎዱ


ህዳር ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ቅዳሜ በከንባታ ጠንባሮ ዞን በዱራሜ ከተማ ገበያ ላይ በተነሳው ተቃውሞ አንድ ታዳጊ ሲገደል ሁለት ፖሊሶች ደግሞ ቆስለዋል። በርካታ ገበያተኞችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ግጭቱ የደረሰው የከተማው ግብር ሰብሳቢዎች አነስተኛ ነጋዴዎች ቡና መሸጥ እንዲያቆሙ ማስገደዳቸውን ተከትሎ ነው። አርሶአደሮች የተወሰኑ ኪሎ ቡናዎችን ወደ ገበያ በመውሰድ የመሸጥ የዘመናት ልማድ ያላቸው ሲሆን፣ የከተማው ግብር ሰብሳቢዎች ደግሞ ” ንግድ ፈቃድ ካላወጣችሁ ከእንግዲህ አንድ ኪሎም ቢሆን መሸጥ አትችሉም” በማለታቸው ለግጭቱ መነሳት ምክንያት ሆኗል። 

አርሶአደሮቹ ” ለዘመናት የኖረውን አሰራር አንቀይርም፣ የምንሽጠውም አንድ እና ሁለት ኪሎ እንጅ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና አይደለም፣ ይህም ቢሆን በአመት ለተወሱ ጊዜያት ብቻ ሚካሄድ በመሆኑ፣ ፈቃድ አናወጣም ” በማለት መልስ ሲሰጡ፣ ፖሊሶች ጣልቃ በመግባት አርሶአደሮች ሽያጭ እንዲያቆሙ ለማድረግ ሞክረዋል። ይህን ተከትሎ በህዝቡና በፖሊስ መካከል ግጭት የተነሳ ሲሆን ፖሊሶችም ጥይቶች ተኩሰዋል። 

በከተማዋ የሚገኙ ሁለት ትላልቅ የቡና መጋዝኖችም ተቃጥለዋል።
.

No comments:

Post a Comment