Thursday, October 23, 2014

ሰበር ዜና – በምዕ. ወለጋ በቤተ ክርስቲያን ላይ በሚፈጸመው ግፍ ፓትርያርኩ መንግሥትን አሳሰቡ


  • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጉዳዩን በጥብቅ ይነጋገርበታል
  • በመንግሥት ባለሥልጣናት ስለሚፈጸሙ በደሎች ከአህጉረ ስብከት የሚቀርቡ አቤቱታዎች የፍትሕ አካሉን አፋጣኝ ውሳኔ ያገኙ ዘንድ ቅ/ሲኖዶሱ ግፊት እንዲያደርግ አጠቃላይ ጉባኤው ዐደራ ጥሎበታል
  • አህጉረ ስብከት ያቀረቧቸውን የአስተዳደር፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት በደሎችና ተጽዕኖዎች አጣርቶ መፍትሔ የሚሰጥ÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዋቀር አጠቃላይ ጉባኤው በአቋም መግለጫው ጠይቋል
  • ‹‹ይህ ዐይነቱ ጊዜ የማይሰጠው ችግር ወደ ሌላ ከመዛመቱ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡›› /የ፴፪ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ/
  • ‹‹ድርጊቱ የመቻቻልን ሕግ እያፈረሰ ነው፤ በአካባቢው ያለው መንግሥታዊ አስተዳደር ሊያስብበት ይገባል፡፡›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
  • የምዕ/ወለጋ ሀ/ስብከት በሪፖርቱ የዘረዘራቸውን ችግሮች ከዘገባው በታች ይመልከቱ
His Holiness Abune Mathias0000በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ባለው ፈታኝ ችግር በአካባቢው ያለው መንግሥታዊ አስተዳደር ሊያስብበት እንደሚገባ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስጠነቀቁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ማሳሰቢያውን የሰጡት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተውን ፴፪ ዓመታዊ ስብሰባውን ዛሬ፣ ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ቀትር ላይ ባጠናቀቀበት ወቅት ባሰሙት የመዝጊያ ንግግር ነው፡፡
‹‹በምዕራብ ወለጋ ዐይን ያወጣ፣ ይሉኝታ የሌለው ግፍ እየተፈጸመ ነው፤›› ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በካህናትና ምእመናን ላይ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመው ግፍ ‹‹በዚያ አካባቢ መንግሥት አለ ወይ ያሰኛል?›› በማለት ነው በአስተዳደር፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት የሚፈጸመውን በደልና ተጽዕኖ የገለጹት፡፡
‹‹ድርጊቱ የመቻቻልን ሕግ እያፈረሰ ነው፤›› ያሉት ፓትርያርኩ በአካባቢው ያለው የመንግሥት አስተዳደር ሊያስብበት እንደሚገባ በቃለ ምዕዳናቸው አስጠንቅቀዋል፤ በጉዳዩ ላይ ከጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳነት ይዞ በጥብቅ እንደሚነጋገርበትም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለ36 ነጥቦች የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ በማውጣት ዓመታዊ ስብሰባውን ያጠናቀቀው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ እንደ ምዕራብ ወለጋ ባሉ አህጉረ ስብከት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተከሠቱ ያሉ ችግሮች ፈታኝ መኾናቸውንና በቤተ ክርስቲያን ልማትና በሐዋርያዋ አገልግሎቷ የመጠናከር ጥረት ላይ ተጽዕኖ ማድረሳቸውን በአቋም መግለጫው ላይ በአጽንዖት አስፍሯል፡፡ የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከትን ሪፖርት በአብነት የጠቀሰው መግለጫው፣ በሀገረ ስብከቱ፡-
  • በየትምህርት ቤቱ የሚማሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የኾኑ ወጣቶች እምነታቸውን የሚያስለውጥ ዘዴ በመጠቀም ቅስቀሳ የማካሄድ፤
  • በጠመንጃ አፈ ሙዝ እያስፈራሩ የድብደባ ወንጀል የመፈጸም፤
  • በቤተ ክርስቲያን ስም የተተከለውን የዕጣን አዙርና የዓመታውያን በዓላት ማክበርያ ቦታዎችን እየነጠቁ ለሌላ እምነት ተከታዮች አሳልፎ የመስጠት፤
  • የተሠራውን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ ሙከራ የማድረግ፤
  • ባልተጠበቀ የትንኮሳ መንገድ እየተጓዙ እስከ ነፍስ ግድያ የሚያደርስ ከባድ የወንጀል ድርጊት በእምነታችን ተከታዮች ላይ እንዲደርስ የማድረግ፤
ከባድ የወንጀል ድርጊት በሕገ ቤተ ክርስቲያን በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደርያ ደንብ የተቀመጠውን ድንጋጌ ይልቁንም ሕገ መንግሥቱን እንደሚጥስ አመልክቷል፡፡ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ የሕግ ክትትል እያደረገ መኾኑ ቢታወቅም፣ ይህ ዐይነቱ ጊዜ የማይሰጠው ችግር ወደ ሌላ ከመዛመቱ በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በምልአተ ጉባኤው፣ በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት የተከሠተውንም ኾነ ከሌሎች ተመሳሳይ ችግር ካለባቸው አህጉረ ስብከት የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች በመቀበል በሚመለከተው የፍትሕ አካል እንዲያስወስን አጠቃላይ ጉባኤው ታላቅ ዐደራ ጥሎበታል፡፡SGGA wound up
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚለው የአጠቃላይ ጉባኤው መርሐ ግብር ላይ ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ በሦስት ተወካዮቹ አማካይነት ሰፊ ገለጻ ማቅረቡን ያስታወሰው የአቋም መግለጫው፣‹‹በሃይማኖት መቻቻል ዙሪያ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ጥፋትና ጉዳት በማስረጃ የተደገፈ ኾኖ ሲቀርብ ጉዳዩ በሚመለከተው የፍትሕ አካል እየተመረመረ እንደሚወሰን፣ በሌላም በኩል እንደ አሁኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና የሚፈታተን ችግር ሲያጋጥም በኢትዮጵያ የሃይማኖትተቋማት ጉባኤ በኩል እየቀረበ መፍትሔን ማግኘት እንደሚችል›› በተወካዮቹ መገለጹን አትቷል፡፡
በዚሁም መሠረት ክትትሉ እንዲቀጥልና ለችግሮቹ እልባት እንዲደረግላቸው÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተውጣጣ ኮሚቴተዋቅሮ ጉዳዮቹ እንዲጣሩና የመጨረሻ መፍትሔ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የአፈጻጸም ውሳኔ እንዲሰጥ ጉባኤው በከፍተኛ ድምፅ ጠይቋል፡፡
*                         *                     *
የምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ለአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ ባቀረበው ሪፖርት በሀ/ስብከቱ መንግሥታዊ የአስተዳደር፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት ስለሚፈጸሙ በደሎችና ተጽዕኖዎች የዘረዘራቸው ችግሮች፤
1)  መናፍቃን ባላቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም በፖሊቲካና የመናፍቃን አባላት በኾኑ ባለሥልጣናት በመደገፍ በሥነ ልቡና ጦርነት ሕዝቡን መንጠቅ፤
2)  የቤተ ክርስቲያን የዕጣን አዙር መሬት ክልል በመናፍቃን መደፈር፣ በክሥ ለከፍተኛ ወጪ መዳረግ፤
3)  መናፍቃን መምህራን በትምህርት ቤት ከሕፃናት አንገት ማዕተብ መበጠስ፣ ማሰር አይቻልም የሚል የሌለ መመሪያ ማውጣት፤
4)  በባቦ ገምቤል ወረዳ ሓላፊነት በማይሰማቸው የፖሊስ ሠራዊት ምእመናን ተደብድበው ከአንገታቸው ማዕተብ መበጠስ፣ ወጣቱ በቅድስቲቷ እምነት እንዲያፍር ማድረግ፣ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር፤
5)  ካህናት በጸሎተ ቅዳሴ አገልግሎት ላይ ሳሉ በወረዳው ባለሥልጣናት ተይዘው እስር ቤት መወሰድ፣ ቤተ ክርስቲያኑ ያለቊልፍ ውሎና አድሮ በሕዝብ መጠበቅ፤
6)  የካህናት በባለሥልጣናት ትእዛዝ መንበርከክ፣ መቀጥቀጥ፣ ለከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ አደጋና ሥቃይ መዳረግ፤
7)  በዕለተ ሰንበት ካህናት አገልግሎት ላይ እያሉ ምእመናንን ‹‹ውጡና ወደ ስብሰባ ሂዱ፤ ለቅዳሴ ቄሶች ይበቃሉ›› ከማለት አልፎ ጥዋት ከኪዳን መልስ መኪና መንገድ ላይ አቁመው የ10 ዓመት ዕድሜ ካላቸው የሰንበት ት/ቤት አዳጊዎች ጀምሮ በመኪና ጭነው ወደ ቀበሌው እስር ቤት መውሰድ፤
8)  በቅዱስ ሚካኤል የወርኃዊ መታሰቢያ በዓል ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጎን የእርሻ ቀን አድርገው በማመቻቸት ‹‹በአማራ አገር ቄሶች ጥላ ይዘው ገበሬ ማኅበር እርሻ ላይ ተገኝተው ያሳርሳሉ›› በማለት ቅዳሴ እየተቀደሰ አንድን ቄስ በማስገደድ ጥላ ይዘው እንዲወጡ አስገድደዋል፡፡ በዚህም የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት እንዲስተጓጎል፣ በቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ የመናፍቃንና የሙስሊም አባላት በልማት አስመስለው በሆታና በጫጫታ በመረበሽ ካህናቱ ተደማምጠው ቃለ እግዚአብሔሩን እንዳያደርሱ ማወክ፤
9)  ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ቦታ ይዛ ሌላው በጠባብ መቸገር የለበትም›› በማለት የቤተ ክርስቲያኑን አጥር አስፈርሰው መስጊድ እንዲሠራ መፍቀድ፤
10)   አንድ ሙስሊም ሚልሻ የካህኑን ሚስት ከማሳ ላይ ይዞ ‹‹ባልሽ ያለበትን ቦታ አሳይኝ›› ብሎ በማስገደድ ካህኑ በዐቢይ ጾም በቤተ መቅደስ በውሎ ቅዳሴ በማገልገል ላይ እያሉ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ካህኑን በመስኮት በኩል ባለቤታቸውን እያሳየ ማሣቀቅ፤
11)   በወረዳ አስተዳደሩ መምሪያ የቀበሌ ሥራ አመራር አባላት፣ በዐቢይ ጾም ወቅት ካህኑን አስገድደው ለስብሰባ ወስደው በቅዳሴ ሰዓት አትሄድም ብለው ከቅዳሴ ማስቀረትና አገልግሎቱን ማስታጎል፤
12)   ምእመናን አባቶች በእርሻ ላይ እያሉ ፖሊሶች፣ ‹‹እዚህ አካባቢ የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት የት ነው፤ አሳየን?›› ሲሉ ‹‹እኔ አላውቅም›› ሲሏቸው እርሻቸው ከመኖርያ ቤታቸው አጠገብ ነበርና  አንበርክከው በዱላ ደብድበዋቸዋል፡፡ ለኻያ ደቂቃ ወደ ፀሐይ አንጋጥጠው እንዲያዩ አድርገዋቸዋል፡፡ ይህን አይተው የተደናገጡት ባለቤታቸው ምርር ብለው እያለቀሱ ወዲያውኑ ታመው ሰውዬው በተደበደቡ በሦስተኛው ቀን ሕይወታቸው አልፏል፡፡
13)   የቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሚልሻዎች፣ በመጋቢት ፳፯ ቀን ክብረ በዓል ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመግባት፣ ‹‹ታቦት ለማክበርና ለማንገሥ ቄሶች ይበቃሉ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ስብሰባ ይሂድ›› በማለት ሕዝቡን አስገድደው ወስደው ክብረ በዓሉ በካህናት ብቻ ውሏል፡፡
14)   በጊምቢ ከተማ ውስጥ በአራት ዓመት ውስጥ ሦስት መስጊዶች ያለፈቃድ ሲሠሩ፣ የሕዝብና የመንግሥት ጎተራ ላይ የፕሮቴስታንት አዳራሽ ሲሠራ በዝምታ ያለፉ የመንግሥት አካላት በከተማው ውስጥ የግለሰብ ቦታ አግኝተን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ስንጠይቅ ‹‹ቤተ ክርስቲያናችኹ በመንግሥት ለመታወቋ በዘንድሮው ዓመት ያሳደሰችውን የዕውቅና ወረቀት/ደብዳቤ አምጡ›› በማለት የ3000 ዓመት ባለታሪኳን ቤተ ክርስቲያን መድፈር፤
15)   ጊምቢ ደብረ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለልማት ሠርቶ ከሚያከራያቸው ሕንጻዎች የመንግሥት ግብር ክፈሉ ማለት፤ ይህ ሁሉ በተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ተከታይ የመንግሥት አመራር አባላት መመሪያ ሰጭነት በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሚፈጸም የግፍ ግፍ ነው፤ በዚህም ሀገረ ስብከቱ በሐሳብ፣ በጉልበት፣ በኢኮኖሚ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰበት መኾኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአንክሮ እንዲገነዘብልን እንጠይቃለን፡፡
16)   የቃለ ዐዋዲው ሕግ ይሻሻል፤ እኛ በራሳችን በጀት ስለምንሠራ ሀ/ስብከትና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምን ያደርጉልናል በሚል ሕዝብ ማሳመፅና የሀ/ስብከት ዕቅድ ተግባራዊ እንዳይኾን ዕንቅፋት መኾን
የተወሰዱ ርምጃዎች
1)  የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ መላው የሀ/ስብከታችን ሠራተኞች ሁሉ በኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማር ስለሚችሉ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና በበዓላት ላይ ሁሉም ሠራተኛ ወደ ወረዳ ወርዶ እንዲያስተምር ተደርጓል፤
2)  በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደረሰው ከአንገት ላይ ማዕተብ የመበጠስ ድፍረት በፍርድ ቤት ክሥ መመሥረት፤
3)  በባቦ ገምቤል፣ በቤጊ እና ነጆ ወረዳዎች ለደረሰው ከፍተኛ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰትና ሥርዐተ አልበኝነት በብፁዕ አባታችን መሪነት ልኡካንን አስከትሎ ካህኑ የተደበደበበበት ቦታ ድረስ በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ በመሄድ መንግሥት አካላትን ይዘን ነገሩን አጣርተን ከወረዳ አስተዳደሮች ጋራ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር የችግሩን ፈጣሪዎች ለይተን በማውጣት ለሕግ አቅርበናል፡፡West Wollega Hagere Sibket annual report01

No comments:

Post a Comment