Monday, October 6, 2014

ለባቡር ፕሮጀክት ሊሰጥ የነበረው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲዘገይ ተደረገ ...

በስዊዘርላንድ ባንክ ክሬዲት ስዊዝ የሚመራው የአውሮፓ አበዳሪ ባንኮች ጥምረት፣ ኢትዮጵያ ላቀደችው የአዋሽ – ወልዲያ የባቡር ፕሮጀክት ለማቅረብ የተስማማውን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አዘገየ፡፡



ባንኩ የተጠቀሰውን ብድር ያዘገየው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያቀረበው የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት ክሬዲት ስዊዝ ከሚከተለው ‹‹ኢኳቶሪያል ፕሪንሲፕል›› ከተሰኘ የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ መመዘኛ ደረጃ ጋር፣ ሙሉ በሙሉ መጣጣም ባለመቻሉ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ከምትገኘው አዋሽ አርባ በኮምቦልቻ በኩል ወልዲያ ሃራ ገበያ የሚደርስ 447 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር በመዘርጋት፣ የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል በቀጥታ አዲስ አበባን ሳይረግጥ ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚደርስበትን የትራንስፖርት አማራጭ ለመዘርጋት አቅዷል፡፡

ይህ የባቡር መስመር በአጠቃላይ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ የውጭ ብድሩን ለማግኘት የውጭ አበዳሪዎች የሚጠይቁትን ሰነድ ለማሟላት የሚያስችል የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት፣ የፕሮጀክቱ ርዝመት፣ በአራት ተከፍሎ በአራት ኩባንያዎች ጥናቱ መሠራቱንና ይህ ጥናትም ከብድር ጥያቄ ሰነዱ ጋር አብሮ በክሬዲት ስዊዝ ባንክ መቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በክሬዲት ስዊዝ መሪነት ሥር የተጣመሩ የተለያዩ የአውሮፓ ባንኮች ለአብነትም የስዌድሽ ኤክስፖርት ክሬዲት ጋራንቲ ቦርድ (EKN)፣ EKF፣ SERV፣ OEKB እና ሌሎችም በጋራ በመሆን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማቅረብ በተስማሙት መሠረት፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት ያቀረበው የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት በገለልተኛ ኩባንያ እንዲጠና አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት ፕራይስ ወተርሐውስ ኩፐር (PWC) የተሰኘ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር ጥናቱ እንዲገመገም አድርገዋል፡፡ በግምገማው ውጤት መሠረትም የስዊዝ ባንክና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በሚጠቀሙበት ‹‹ኢኳቶሪያል ፕሪንሲፕል›› መመዘኛ መሠረት፣ በአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናቱ 17 ንዑስ መገምገሚያ ርዕሶች የ‹‹ኢኳቶሪያል ፕሪንሲፕል›› ደረጃዎችን እንደማያሟሉ ግምገማውን የሠራው ድርጅት ማረጋገጡን ምንጮቹ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የአካባቢያዊና የማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናቱ በ37 ንዑስ ርዕሶች ተገምግሞ 17 ንዑስ ርዕሶች የአውሮፓ ደረጃን እንደማያሟሉ፣ የተቀሩት በከፊል ወይም ከሞላ ጐደል የሚያሟሉ መሆናቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

‹‹የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያቀረበው የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት በአሁኑ ወቅት ክሬዲት ስዊዝ ባንክ የሚከተለውን ‹‹ኢኳቶሪያል ፕሪንሲፕል›› ሆነ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ፐርፎርማንስ ስታንዳርድ አያሟላም፡፡ ይህ ማለት ግን የፕሮጀክቱ ዲዛይን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደረጃዎቹን የማያሟሉት 17 ንዑስ ርዕሶች ላይ ማስተካከያ ቢደረግ ደረጃውን አያሟሉም ማለት አይደለም፤›› የሚል ምክረ ሐሳብ ለባንኩ እንደቀረበለትና ባንኩም መረጃውን ለብድር ጠያቂው እንዳስተላለፈ ምንጮቹ አስታውቀዋል፡፡

የአውሮፓ ደረጃን እንደማያሟሉ ከተጠቀሱት 17 ንዑስ ርዕሶች መካከል ዜጎችን የሚያፈናቅልና የመሬት ይዞታቸውን የሚነካ፣ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ የፕሮጀክቱ አካባቢ ነዋሪዎችን ባህል፣ አኗኗርና ጥቅም የማይጐዳ መሆኑ አለመረጋገጡ ይገኙበታል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ከላይ የተባለው ነገር እንደሌለና ብድሩም እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ አባባላቸው ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአዋሽ – ወልዲያን የባቡር መንገድ ለመገንባት ያፒ መርከኒ የተሰኘ የቱርክ ኩባንያን በኢንጂነሪንግ ፕሮኪዩርመንት (ግዥ) እና ግንባታ (EPC) ስምምነት መሠረት ከሁለት ዓመት በፊት የቀጠረ ሲሆን፣ የቱርክ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክም 300 ሚሊዮን ዶላር ለፕሮጀክቱ ለማበደር ተስማምቷል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ እስካሁን ፕሮጀክቱ መጀመር እንዳልተቻለ የሚገልጹት ምንጮች፣ የቱርክ መንግሥት 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ቢለቅ ፕሮጀክቱን አስጀምሮ ቀሪውን እየገነቡ መጠባበቅ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ይህ ከቱርክ መንግሥት የሚጠበቅ ገንዘብ እስካለፈው ሳምንት አለመለቀቁ ተረጋግጧል፡፡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ አሜሪካ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከቱርኩ አቻቸው ጋር ተገናኝተው ብድሩ በፍጥነት እንዲለቀቅ ተነጋግረው መግባባታቸውን በትዊተር ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

አንዳንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባለሙያ ግን፣ ፕሮጀክቱ በይፋ በዚህ ሳምንት ሊጀመር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

የፕሮጀክቱ ብድር ተፈቀዶ ስምምነት ሳይፈጸም ወደ ሥራ መግባት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚገልጹ የሪፖርተር ምንጮች፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ መምጣቱን፣ ለአብነትም በመገንባት ላይ ያለው የአዲስ አበባ – ጂቡቲ አዲስ የባቡር መስመር ዝርጋታ ብድር ከቻይና ባንክ ሳይለቀቅ ፕሮጀክቱ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ፕሮጀክቱ የተጀመረው የቻይና ባንክ ብድሩን አይከለክልም በሚል ግምት የኢትዮጵያ መንግሥት ከራሱ ካዝና የመጀመሪያ ክፍያ ለኮንትራክተሩ በመክፈል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ኮትራክተሩና የኮንትራክተሩ የቀድሞ ተቆጣጣሪ የነበረው የስዊድን ኩባንያ ባለመግባባታቸው፣ የቻይናው ኤግዚም ባንክ ብድሩን መያዙንና የቻይና ተቆጣጣሪ ኩባንያ ካልተቀጠረ ብድሩን እንደማይለቅ ማስታወቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የስዊድኑ ኩባንያ ከተቆጣጣሪነቱ ተነስቶ ሌላ የቻይና ኩባንያ ተተክቶ ብድሩ መለቀቁን፣ ብድሩ ሙሉ በሙሉ ሳይገኝ ፕሮጀክቱ በመጀመሩ መንግሥትን ጫና ውስጥ ከቷል ሲሉ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት አንድ የቻይና ኮንትራክተርን ሌላ የቻይና ኩባንያ እየተቆጣጠረ የአዲስ አበባ – ጂቡቲ የባቡር መስመር እየተዘረጋ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ብድሩ ሳይገኝ ፕሮጀክቱ በሚጀመርበት አግባብ ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/35130

No comments:

Post a Comment