Wednesday, October 29, 2014

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የእስር ቅጣቱን በመቃወም ይግባኝ ሊጠየቅ ነው


  • 415
     
    Share
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳትና ሀሰተኛ መረጃን በመስጠት በሚል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበት የ3 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠበቃው አቶ አመሀ መኮንን አስታወቁ። ጠበቃው አክለውም፤ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ሕጉ እስከፈቀደው ድረስ ማንኛውንም መድረክ አሟጠን እንጠቀማለን ሲሉ ተናግረዋል። ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠቁመው ያም ሆኖ የተለየ ውጤት ካልተገኘ እስከሰበር ችሎት እንደርሳለን ብለዋል።
በተከሳሹ ላይ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ብይን ከሰጠ በኋላ ስለምን የቅጣት ማቅለያ አላቀረባችሁም ተብሎ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ በመርህ ደረጃ ጥፋተኛ መባል አልነበረበትም፤ አሁን ጉዳዩ ብዙ ዓመት የመታሰርና ትንሽ ዓመት 
የመታሰር ብቻ ሳይሆን በዋናነት ለቅጣት ቅነሳ መከራከሪያችን ለህግ ጥፋቱን የማመን ምልክት ስላለው አልፈለግንም።

Temesghen Desalegn (CPJ)cropped
አመፅን ለመቀስቀስ በመሰናዳት ወንጀል ተሳትፎ፤ ሕገ-መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን በቀድሞዋ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ሲያሰፍር ነበር በሚል የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ጥፋተኛ የተባለበት ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ወንጀል ሥር በ3 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ፍርድ ቤት ባሳለፍነው ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።
ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ሶስት ክሶችን በጋዜጠኛው ላይ አቅርቦ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች 
አስረድቷል። ተከሳሹም ከተከሰሰባቸው ወንጀሎች ነፃ ያወጡኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ የተከራከረ ቢሆንም፤ ችሎቱ የግራ ቀኙን መረጃ መርምሮ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ጥፋተኛ ነህ ብሎት እንደነበር ይታወሳል።
በዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር የተጠቀሱት ፍሬ ሀሳቦች መካከል በአንደኛው ክስ ሥር “ሞትን የማይፈሩ ወጣቶች” በሚል ርዕስ ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፃፈው ሀተታ ውስጥ ወጣቶች ለአብዮትና ለለውጥ እንዲነሳሱ በማድረግ፤ በአረቡ አለም ወጣቶች የነበራቸውን ሚና በመጥቀስ አሁን ያለውን ስርዓት ለመቀየር ወጣቶች ለአመፅ እንዲነሳሱ አድርጓል የሚል ነው።
በ2ኛ ክስ ስር የተዘረዘረው ሀሳብ ደግሞ “የሁለተኛ ዜግነት ህይወት በኢትዮጵያ እስከመቼ?” በሚል ርዕስ ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም በፍትህ ጋዜጣ ባወጣው ሀተታ ስር መንግስት በተለያዩ ክልሎች የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅሟል በማለት የአገሪቱን መንግስት ስም በማጥፋትና በሀሰት ወንጅሏል የሚል ክስ ተመስርቶበታል።
ዐቃቤ ሕግ 3ኛ ክስ አድርጎ ያቀረበው ደግሞ በመጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በታተመችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ “ሲኖዶሱና መጅሊሱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቂያ” ሲል ባሰፈረው ፅሁፍ መንግስት የሃይማኖት ተቋማቱን ለፖለቲካዊ ዓላማ እየተጠቀመባቸው ስለመሆኑ በማተት የህዝብን እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል ሲል ይከሰዋል።
ተከሳሹ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧቸው በነበሩ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አማካኝነት በጥቅሉ፤ የጋዜጠኝነት ተግባሩን እየተወጣ በመሆኑንና በዚህም ህገ መንግስቱ የሰጠውን ኀሰብን የመግለፅ ነፃነት ተጠቅሞ ሥራውን ማከናወኑን ባቀረባቸው የመከላከያ ምስክሮች ጭምር አስረድቷል።
ሆኖም የግራ ቀኙን ክርክር ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ጥፋተኛ ማለቱን ተከትሎ ባሳለፍነው ሰኞ የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል። በዚህም የውሳኔ ንባብ ወቅት ፍርድ ቤቱ እንዳለው፤ ምንም እንኳን ተከሳሹ ጥፋተኛ ቢባልም የቀረቡበት 3 ክሶች በአንድ ሃሳብ ሊጠየቅ የሚገባው ነው በሚል፤ በወንጀል ህጉ የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ወንጀል ብቻ ይቀጣ ማለቱን ተከትሎ ምንም አይነት የቅጣት ማቅለያ ባላቀረበው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ፈርዶበታል።
በተያያዘም አሳታሚው ማስተዋል የህትመትና ማስታወቂያ ኃ/የተ/የግ ማህበር ላይ ዐቃቤ ሕግ አቅርቦት የነበረው የንብረት ይወርስልኝ ጥያቄን ፍርድ ቤቱ ወደጎን በመተው የ10ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ጥሎበታል።

ምንጭ፦ ሰንደቅ ጋዜጣ

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/35812#sthash.Ryk2P5za.HSP249Ld.dpuf

No comments:

Post a Comment