Sunday, October 12, 2014

የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ቀጠና ኃላፊ በደህንነት ሰዎች ተደበደቡ ....


     *************         ***********      ***********

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የሰሜን ቀጠና ኃላፊ የሆኑት አቶ አዕምሮ አወቀ ሐሙስ ዕለት ከሥራ ወደ ቤታቸው ሲጓዙ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍኖተ ነፃነት ገለጹ፡፡

እንደ አቶ አዕምሮ ገለፃ ይህ ድርጊት በየጊዜው እንደሚከሰትና በሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴ በደሴ ከተማ በመኪና ለማፈን በተደረገው ግብግብ መኪና ውስጥ አስገብተው እንደተደበደቡ ራሳቸውን ለመከላከል በሚታገሉበት ወቅትም ጋቢና የተቀመጠውን ሹፌር መኪናውን ለማስነሳት ቁልፍ እንደያዘ እጁን ሲረግጡት በመጎዳቱ፣ ሁለቱ ከኋላ የያዟቸውን ደህንነቶች ለመከላከል ባደረጉት ግብ ግብ ስላየሉባቸው ገፍትረው ከመኪናው እንደጣሉዋቸውና ወደ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ ወንድማችንን ደብድበሃል የትም አታመልጥም በሚል ለገሃር አካባቢ በቡድን ድብደባ እንደፈጸሙባቸው ገልጸዋል፡፡ 
በተመሳሳይ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ከሰሜን የሚመጡ የፓርቲው አባሎችን ለመቀበል ዝግጅት በሚያደርጉበት ታህሳስ 17/2006 ዓ.ም ቤታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተሰብሮ ንብረቱ በሙሉ ከቤት ተጭኖ ተወስዷል፡፡ ሐሙስ ዕለትም ከሥራ ወጥተው በትራንስፖርት ወደ ቤታቸው በሚሄዱበት ወቅት አየር ጤና አካባቢ ከአውቶቡስ ሲወርዱ ሁለት ደህንነቶች ግራና ቀኝ እጃቸውን በመያዝ እንዳይንቀሳቀሱ ካደረጉዋቸው በኋላ ሦስተኛው ደህንነት በድንጋይ ከጉልበታቸው በታች ደጋግሞ በመምታት ቀኝ እግራቸው ላይ ጉዳት አድርሰው ሦስቱም ከአካባቢው እንደተሰወሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ህገ ወጥ ድርጊት በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ መታገሌን እንዳቆም እንደማያደርገኝ ሊያውቁት ይገባል በማለት ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment