Saturday, October 18, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ የጠራውን ስብሰባ ረግጦ ወጣ


☞ «ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምህዳር እንዲኖር እንስራ!» የሚለው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፤
ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥቅምት 7/2007 ዓ.ም በ2007ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን 5ኛው አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ከአገራዊ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት በጊዮን ሆቴል የጠራውን ስብሰባ ረግጦ ወጣ። ሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባውን ረግጦ የወጣው የምርጫ ቦርድ ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን መስራት ያለበትን ነገሮች ሳይሰራና ፓርቲዎችም ያሉባቸውን ችግሮች አቅርበው መወያየት ሳይችሉ ስለ ጊዜ ሰሌዳ ማውራቱ አስፈላጊ አይደለም በሚል መሆኑን ስብሰባውን ለመሳተፍ ሄደው የነበሩት ተወካዮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ስለ ጊዜ ሰሌዳው ከመወያየት በፊት ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር በመስራት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን በ1997 ምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ያሉባቸውን ችግሮች በዝርዝር መወያየታቸው ቢያንስ ቅድመ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማገዙን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ1997 ምርጫ በኋላ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ችግራቸውን በዝርዝር በመወያየት፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ስለሚያስችሉ ጉዳዮች መነጋገር ባለመቻላቸውና ምርጫ ቦርድም በጉዳዩ በህገ መንግስቱና በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣቱ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደተዘጋም በመግለጽ ምርጫ ቦርድን ወቅሰዋል።
ፓርቲዎቹ በ2005 የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋና የአካባቢ ማሟያ ምርጫዎች በፊት ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ሳይወጣ አዳማ ላይ ‹‹ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንወያይ›› ብሎ ስብሰባ በጠራበት ወቅት ‹‹መጀመሪያ ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር መወያየት አለብን›› ብለው ጥያቄ ቢያቀርቡም ቦርዱ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ገልጸው በዚህ አመትም ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር እንዲኖር እንደሚፈልጉ አሳስበዋል።
ንግግር ካደረጉት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች የሚገኙበት ሲሆን የፓርቲው ጥናትና ስትራቴጅ ኃላፊ ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ «ምርጫ ቦርድ በህገ መንግስቱና በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም። ፓርቲዎች ስለሚደርስባቸው በደል በዝርዝር ተወያይተው ገዥው ፓርቲ የሚያደርስባቸው በደል መቆም ካልቻለ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምህዳር ሊፈጠር አይችልም። በመሆኑም 30ና 40 ደቂቃ ለማይፈጅ የጊዜ ሰሌዳ ድልድል ጊዜያችን ከማጥፋታችን በፊት ነጻ ምህዳር ስለሚፈጠርበት ሁኔታ መነጋገር ይገባናል።» ሲል የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችን አሳስቧል።
ኢንጅነር ጌታነህ አክሎም «የዘንድሮው አመት ከእስከዛሬው የተለየ ነው። ህዝቡ ከእስከ ዛሬው በባሰ ምሬት ውስጥ ይገኛል። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለውጥ ይፈልጋል። በመሆኑም ይህን አመት እንደስከዛሬ ሳይሆን በተለየ መልኩ ልናየው ይገባል። እንዲህ ባለው ወቅት ችግር ሊከሰትም እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምህዳር እንዳይፈጠር በመደረጉ በአገራችን ለሚመጣው ችግር ደግሞ ኃላፊነቱን የምትወስዱት እናንተ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ናችሁ። የፓርቲዎችንና የምርጫን ጉዳይ ተግባራችሁን መወጣት ባለመቻላችሁ በሚመጣው ችግር በታሪክ ተጠያቂዎች መሆናችሁ አይቀርም።» ሲልም አስጠንቅቋል።
«ከጊዜ ሰሌዳው በፊት ፓርቲዎች የሚደርሱባቸውን ችግሮች ዘርዝረው ስለመፍትሄው እንነጋገር፣ ነጻ ምህዳር ስለመፍጠር ከአሁኑ መስራት አለብን፣ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ይወጣ» የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱባቸው የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ ያሏቸውን የፓርቲ ተወካዮች እድል በመከልከል ከገዥው ፓርቲ ጋር በቅርበት ለሚሰሩ ፓርቲዎች እድል በመስጠት አጀንዳውን ለማስቀየስ መጣራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
በተለይ «የጋራ ምክር ቤት» ተብሎ በሚጠራው የፓርቲዎች ስብሰብ አባል የሆኑ ፓርቲዎች «አሁን ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንወያይ፣ በሌላ ጊዜ ስለ ችግሮቻችን በመወያየት ችግሮቹን መፍታት እንችላለን።» የሚል ሀሳብ በማቅረብ «መጀመሪያ ነጻ ምህዳር ለመፍጠር እንስራ። ያሉትን ፓርቲዎች ሀሳብ ሊሞግቱ እንደሞከሩ ታውቋል።
የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ያቀረቡትን «መጀመሪያ ነጻ ምህዳር እንዲኖር እንስራ» የሚል ሀሳብ በመግፋት ስለ ጊዜ ሰሌዳው ለመወያየት ሲመርጡ የአካሄድ ጥያቄ ቢነሳም ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ስብሰባው ላይ ተገኝተው የነበሩት ምክትል ፕሬዝደንትና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ስለሽ ፈይሳ እንዲሁም የጥናትና ስትራቴጅ ኃላፊ ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ «መጀመሪያ ስለ ምህዳሩ መነጋገር አለብን፣ ችግሮች መፈታት አለባቸው።» የሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ባለማግኘታቸው «ችግሮች ሳይፈቱ ስለ ጊዜ ሰሌዳ አንወያይም» ብለው ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል።
ምንጭ ፦ ነገረ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment