Thursday, September 18, 2014

የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም

መስከረም ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አብዲ ሙሃመድ 7 የስራ አስፈጻሚ የኮሚቴ አባላትን ማበረራቸውን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ በአስቸኳይ እንዲመጡ ቢታዘዙም፣ የቀረበላቸውን ጥሪ ባለመቀበል ጅጅጋ ውስጥ እንደሚገኙ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ተናግረዋል።

ለአቶ አብዲ ቅርበት ያላቸው የመከላከያ ባለስልጣኖች በተደጋጋሚ ስልኮችን በመደወል አቶ አብዲን ለማግባባት እየሞከሩ ሲሆን  አቶ አብዲ በበኩላቸው ” ኢትዮጵያ ውስጥ 30 መንግስት ነው ያለው እንዴ?” በማለት እስከመጠየቅ መድረሳቸውንና ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ታውቋል። በሌላ በኩል ድሬዳዋ ላይ ተሰብስበው አቶ አብዲን ከስልጣን ማንሳታቸውን ያስታወቁት 7 የስራ አስፈጻሚ አባላት ከፌደራል መንግስት በደረሳቸው ጥሪ መሰረት አዲስ አበባ መግባታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። አቶ
አብዲ የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ማባረር እንደማይችሉ ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እንደተገለጸላቸው ታውቋል።
በክልሉ ባለስልጣናት መካከል ያለው ሽኩቻ እየቀጠለ ባለበት በዚህ ጊዜ አቶ አብዲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ያሰሩዋቸውን ሰዎች እየፈቱ ነው። በየረር ባሪ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በልዩ ሚሊሺያ አባላት ከተገደሉት 50 ሰዎች ጋር በተያያዘ ከታሰሩት 19 የአገር ሽማግሌዎች መካከል 17 ቱ  በፕሬዚዳንቱ ልዩ ትእዛዝ መስከረም 4 ቀን ከምሽቱ 3 ሰአት ላይ እንዲፈቱ ተደርጓል። 2ቱ የአገር ሽማግሌዎች ቀደም ብሎ እስር ቤት ውስጥ መሞታቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። የአገር ሽማግሌዎቹ ኢሳት ጉዳያቸውን በመከታተሉም ምስጋናቸውን ገልጸዋል በክልሉ ውስጥ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ መቀጠሉን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment