Saturday, February 22, 2014

የአዲስአበባ አስተዳደር ጋዜጠኞች ለአባይ ግድብ ገንዘብ እንዲያዋጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀሩ


የካቲት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የመገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ለአባይ ግድብ ቦንድ ግዥ በድጋሚ እንዲያዋጡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የአስተዳደሩ ሹማምንትና ካድሬዎች ከሁለት ዓመት በፊት ሠራተኛውን ካወያዩ በኃላ በራሳቸው ውሳኔ ሠራተኛው የአንድ ወር ደመወዙን በአንድ ዓመት ከፍሎ ለማጠናቀቅ እንደፈቀደ አድርገው በመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው ሰፊውን ሠራተኛ በማስቆጣቱ ወዲያውኑ ስብሰባ እንዲጠራለት በመጠየቅ ተቃውሞውን ገልጾአል፡፡ በዚህ ተቃውሞ መሰረት በአንድ ዓመት ይቆረጣል የተባለው የአንድ ወር ደመወዝ መዋጮ ወደሁለት ዓመት ሊሸጋገር ችሎአል፡፡

ሰራተኛው በሁለት ዓመት የከፈለው የአንድ ወር ደመወዝ መዋጮ በሀምሌ ወር 2005 ዓ.ም ከተጠናቀቀ በሃላ እንደገና መዋጮው እንዲቀጥል የአስተዳደሩ ካድሬዎች በተደጋጋሚ ሰራተኛውን ለማግባባት ሙከራ ያደረጉ ቢሆኑም አብዛኛው ሰራተኞች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ሊሳካ አለመቻሉ ምንጫችን ጠቁሞአል፡፡

አንድ የመገናኛ ብዙሃን ባልደረባ ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን እንደተናገረው ሠራተኛው ወርሃዊ ገቢው ከእጅ ወደአፍ መሆኑን፣ አዳዲስ ምሩቃኖች ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የተማሩበትን ዋጋ ክፍያ ለመክፈል የሚቆረጥባቸው በመሆኑ ምክንያት መዋጮውን ለማዋጣት አቅም እንዳጠራቸው ገልጸው ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ነገር ግን ካድሬዎቹ ከሌሎች ቢሮዎች እንዴት እንለያለን በሚል በተደጋጋሚ ስብሰባ በመጥራት ለማግባባትና ለማስፈራራት የሞከሩ ቢሆንም በሰራተኛው አቋም ምክንያት ሊሳካላቸው ሳይችል ቀርቶአል፡፡

በመጨረሻም ሰራተኛው በራሱ ፈቃደኝነት መስጠት የሚፈልገውን መቶኛ ያሳውቅ በሚል አንድ ቅጽ አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፡፡

ይህ ቅጽ እያንዳንዱ ሰራተኛ የሚያዋጣውን መቶኛ በመጻፍ በፊርማው አረጋግጦ እንዲመልስ የተደረገ
ሲሆን በዚህ ሒደት ሰራተኛውን በመከፋፈል ብዙዎቹ እንዲያዋጡ ለማድረግ ይቻላል በሚል ስሌት የተገባበት እንደነበር ታውቋል፡፡ ቅጹን አንዳንድ የፈሩ ሰራተኞች ከአንድ ወር ደመወዛቸው 30 በመቶና ከዚያ በታች የሆነ መጠን በሁለት ዓመት እንዲቆረጥባቸው ተስማምተው የሞሉ ሲሆን ብዙዎቹ አሁንም ቅጹን ለመሙላት ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው በተለይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችን እንዳስደነገጠ ታውቋል፡፡ የመስተዳድሩን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment