Saturday, February 22, 2014

አንጋፋ ታጋዮች ስለ ህወኃት ይናገራሉ “ታጋዮች የተሰውለት ዓላማ ተረግጧል


“ታጋዮች የተሰውለት ዓላማ ተረግጧል”
ህወኀት የተመሰረተበት 39ኛ ዓመት በዓል ባለፈው ማክሰኞ በመቀሌ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርአት አክብሯል፡፡ በዚህ በአል ላይ በትግሉ ወቅት የተሰው ቀደምት ታጋዮች የታወሱ ሲሆን የህወኀት ታሪክም በተለያዩ የፓርቲው አባላት ተነግሯል፡፡ ከህወኅት ምስረታ ጀምሮ በትግሉ ውስጥ የቆዩና በተለያዩ ጊዜያት ከፓርቲው የተለዩ አንጋፋ ታጋዮች ግን ህወኃት አላማውን ስቷል ሲሉ ይተቻሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኞች አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ ከእነዚህ አንጋፋ ታጋዮች መካከል አቶ ገብሩ አስራት እና አቶ አሰግደ ገ/ሥላሴን በህወኀት የትግል ዓላማ ዙርያ  አነጋግረዋቸዋል፡፡
“ታጋዮች የተሰውለት ዓላማ ተረግጧል”
አቶ ገብሩ አስራት (የህወኀት አንጋፋ ታጋይ እና የአረና ፓርቲ መስራች)
መነሻው ላይ የህወኀት አላማ ምን ነበር?
በሃገሪቱ ላይ የሰፈነውን ጭቆና ማስወገድ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ስርዓት የግለሰብና የቡድን መብትን የማያከብር በመሆኑ የሃይማኖት መብትን ጨምሮ እነዚህን ሰብአዊ መብቶች ማረጋገጥ ነበር ዓላማው። መብቱ ብሄሮች እስከ መገንጠል የሚያደርሳቸው ጥያቄ ካለም መገንጠል ይችላሉ የሚል ሆኖ፣ ወሳኙ ግን ነፃነት የሚለው ነበር፡፡ የትግሉ ርዕዮተ ዓለም ማርክሲዝም ቢሆንም ማጠንጠኛው ነፃነትና የሰው ልጆች መብቶችን ማረጋገጥ ነበር፡፡
ትግሉ የትግራይ ሪፐብሊክን የመመስረት አላማ እንደነበረው ይነገራል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የህወሃት ታጋዮች ግን ይሄ ዓላማ አልነበረም ይላሉ። እውነቱ የትኛው ነው?
ህወኀት ለአንድ ዓመት ያህል የተፃፈ አላማና ፕሮግራም አልነበረውም፡፡ በኋላ ግን አንድ ማኒፌስቶ ተዘጋጀ፡፡ በዚህ ማኒፌስቶ የትግራይ ሪፐብሊክን የማቋቋም አላማ ተቀምጦ ነበር፤ ነገር ግን በጉባኤ አልፀደቀም፡፡ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች አፅፈው ያሰራጩት ሲሆን በታጋዮች ዘንድ ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ተቃውሞ ስላጋጠመውም ለስድስት ወር ብቻ ነው በስራ ላይ የዋለው፡፡ “ይሄ ትክክል አይደለም፤ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንደመብት እንጂ እንደ አላማ መቀመጥ የለበትም” የሚል ተቃውሞ ከቀረበበት በኋላ የሪፐብሊክ ምስረታ አላማ ውድቅ ተደረገ፡፡
እርስዎ ለየካቲት 11 የሚሰጡት ትርጉም ምንድነው? አላማውንስ አሳክቷል?
ትልቁ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በዘንድሮው አከባበር ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ ስለጠላቶች ነው የሚያወሩት፡፡ የትኞቹ ጠላቶች እንደሆኑ አልገባኝም፡፡ አካሄዳቸውን የሚቃወመውን፣ መብቴ ተነክቷል ወይም ሙስና ተንሰራፍቷል እያለ የመልካም አስተዳደር ችግሩን የሚተቸውን ሁሉ በጠላትነት እየፈረጁት ነው ማለት ነው? ይሄ የየካቲት 11 አላማ አይደለም፤ መስተካከል አለበት። አሁን ያሉት አመራሮች ከስልጣናቸው በላይ የሚያሳስባቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ሃሳባቸው እሱ ብቻ ነው፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ህይወታቸውን የገበሩለት ዓላማ አሁን በቦታው አለ ብዬ አላምንም፡፡
የህወኀት ትግል ያመጣው ውጤት እንዴት ይገመገማል?
ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ ህወኀት ብቻ ሳይሆን በርካቶች ታግለዋል፡፡ ኢህአፓ አለ፤ ሌሎችም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ ህወኀት ብቻ ውጤታማ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ማንኛውም ፍትህና እኩልነትን አመጣለሁ ብሎ መስዋዕትነት የከፈለ ሁሉ የራሱ ቦታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ደርግን መጣሉ አስፈላጊ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎች የተሰውለት አላማ ተረግጧል፡፡ በተለይ በትግራይ የተቃውሞ ፖለቲካ ነውር ሆኗል፡፡ መውጫና መግቢያ ታጥቷል፡፡ ስብሰባ ማካሄድ አልተቻለም። የካቲት 11 ደግሞ ስልጣን ላይ ለመቆየት ህዝቡን ማስፈራሪያ ነው የሆነው፡፡ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ እየዋለ ነው፡፡ በሰማዕታትና በተሰውት ታጋዮች ስም እየተነገደ ነው፡፡
የህወኀት የትግል ታሪክ በትክክል ለትውልድ የሚተላለፍበት መንገድ ተመቻችቷል ይላሉ?
በእርግጥ ብዙ የታሪክ መዛግብቶች አሉ። በትግሉ የነበሩና ዛሬ ወደ ጎን የተገፉ ወገኖችም ይህን ታሪክ የማረቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን ታሪክ እየተቀለበሠ ነው፡፡ እንደውም ታሪኩ እየተነገረ ያለው ትግሉን በማያውቁ፣ ታሪኩን ባልተረዱ ግለሰቦች ነው፡፡ ሺዎች የተሰዉለትን መራር ትግል ተረት እያደረጉት ነው፡፡ እንደተረት ውሸት እየቀላቀሉ እያወሩት ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ይህን መሰል የታሪክ ቅልበሳ እየፈፀመ ያለው ጉልበት እና ገንዘብ ያለው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው ራሱን የዚህ ታሪክ ብቸኛ ባለቤት እያደረገ ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች በትግሉ ወቅት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እንኳ አይነገርም፡፡ ጭራሽ ሺዎች የተሰዉበት ታሪክ ወደ አንድ ሰው እየተጠቃለለ ነው፡፡ መለስ እና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት እኩል እንኳ እየታዩ አይደለም፡፡ ይሄ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡
ከ1983 በኋላስ ህወኀትን እንዴት ይገመግሙታል?
ይሄ በአጭሩ መገለፅ የሚችል አይደለም፤ የራሱ ትንታኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡
ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በህወኀት ላይ የታዩ ለውጦች አሉ?
አይ የለም! ዋናው ጥንስሱ ያለው የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለው ነገር ዜጎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ማህበረሰቦችን ሁሉ ይፈርጃቸዋል፡፡ እሱን የሚያገለግሉትን ወዳጅ ሲላቸው፣ በተቃራኒው የተሰለፉትን ጠላት ሲል ይፈርጃቸዋል፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ ችግሩ ርዕዮተ ዓለሙ ላይ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለም የተዋቀረ መንግሥት ፀረ-ዲሞክራሲ ነው የሚሆነው፡፡ መጀመሪያ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ፕሬሶች ነፃነት ተሰጥቷቸው ተቋቁመው ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ይሄን መፍቀዱ ለስልጣናቸው አስጊ ሆኖ ስላገኙት ይበልጥ አምባገነንና ጨቋኝ ስርአት መገንባትን አማራጭ አድርገዋል፡፡ “ቀይ መስመር”፣ “ፈንጂ ወረዳ” በሚል እነዚህ መብቶች ተሸራርፈው ቀዳሚው ትኩረት ስልጣንን ማስጠበቅ ሆኗል፡፡
የዘውድ ስርአቱ ካከተመ 40 ዓመት ተቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያት በተደረጉት የተለያዩ ትግሎች የተገኙት አንኳር ለውጦች ምንድን ናቸው?
የ1966 አብዮት ያመጣቸው መሰረታዊ ለውጦች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ማህበረሰባዊ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ የፊውዳል ስርአት ተሰብሯል፡፡ የመሬት ስሪቱ አዲስ አቅጣጫ እንዲይዝ ተደርጓል፤ አዲስ ማህበራዊ ኃይል ተፈጥሯል፡፡ ገበሬዎች አዲስ ማህበራዊ ኃይል ነበሩ፤ ነገር ግን በደርግ ታንቀዋል። ይሄ ባይሆን ኖሮ በደርግ የ17 ዓመት የስልጣን ዘመን ብዙ ለውጥ ይመጣ ነበር ብዬ አምናለሁ። ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ በኢኮኖሚ ፖሊሲው ትንሽ የተሻለ ነገር ታይቶ ነበር፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከጥቅም አንፃር ስለሚያየው እንደገና ኢኮኖሚውን ሁሉ የመቆጣጠር ፍላጎት እያሳየ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የኢኮኖሚ ለውጦች መኖራቸው የማይካድ ነው፤ ይሁን እንጂ ለውጡ በጠንካራ ፖሊሲዎች የተደገፈ አይደለም። ፓርቲው ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር አባዜ ስለተጠናወተው በእድገቱ ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያሳረፈ ነው፡፡
አሁን ስላለው የፖለቲካ ትግል የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ቻርተር፣ በአለማቀፍ ደረጃ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር ማንኛውንም አይነት መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ጨቋኝ ስርአትን መታገል ተገቢ ነው፡፡ እኛ በደርግ ጭቆና ጊዜ የነበረን አማራጭ ትጥቅ ስለነበረ በዚያ መንገድ ሄደናል። አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ስንመለከተው ግን ይሄ አካሄድ ወይም በጠመንጃ የመጣ ስልጣን ዲሞክራሲን ያሰፍናል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ መንግስት መቀየር ይችላል ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ማምጣት የተለየ ነገር ይፈልጋል፡፡ ጠመንጃ ያነሳ ወገን፣ መብት ሁሉ ለሱ ብቻ እንደሚገባ ነው የሚያስበው፡፡ እኛ ከሌላው ይበልጥ ሞተንለታል የሚል ትምክህት ውስጥ ነው የሚከተው፡፡ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የትጥቅ ትግልን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ ድሮ “የፖለቲካ ስልጣን ከጠመንጃ አፈ ሙዝ ይመነጫል” ነበር የሚባለው፤ አሁን ግን የተገላቢጦሽ መሆን አለበት፡፡ የጠመንጃ አፈሙዝ በፖለቲካ ተገዢ መሆን ነው ያለበት፡፡
addisadmas

No comments:

Post a Comment