"በዘንድሮው ጥምቀት ሎሚ ባለመወርወር ለሴቶች መብት ዘብ መቆምህን አረጋግጥ!"
ነገ ከተራ፣ ከነገ በስቲያ ጥምቀት ስለሚከበር ቢሮ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያውያን ጥምቀትን አይተው ለማያውቁ ፈረንጅ ባልደረቦቻችን ስለ በአሉ ዘርዘር አድርገን እያወራን ነበር፡፡
ወሬው ሲሟሟቅ አንዱ ልጅ “the best part is throwing lemon (lime) on the girls!” አለ፡፡ ‹‹ከሁሉ ከሁሉ ደስ የሚለኝ ግን ልጃገረዶች ላይ ሎሚ መወርወር ነው›› እንደማለት ፡፡
ፈረንጆቹ ግራ ተጋቡ፡፡
‹‹በበአል ምድር ምን ይሁን ብላችሁ ነው ሴቶች ላይ ሎሚ የምትወረውሩት?›› ብሎ ጠየቀ አንዱ፡፡
‹‹ለፍቅር ለመጠየቅ ነዋ!…ሎሚ የተወረወረባት ሴት ደስ ይላታል፡፡ እንደውም ልጃገረዶች ወደ ጥምቀት ሲሄዱ አዲስ ልብስ ወይ ያላቸውን አጥበውና ተኩሰው ለብሰው፣ ተኳኩለው ነው የሚሄዱት፡፡ ያውም፤ ‹‹ እንደው ቀንቶኝ ሎሚ የሚወረውርብኝ አገኝ ይሆን!›› ብለው አልኩት፡፡
ይባስ ግራ ተጋቡ፡፡
‹‹ይሄማ በሴቶች ላይ የሚደረግ ጥቃት ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሴቶቹም ይሄን አሳዛኝ ባህል ተቀብለው መሳተፋቸው ነው››‹ አለች አንደኛዋ ፈረንጅ፡፡
ተንጫጫን፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጥምቀት ቀይ ሳይሆን ነጭ ለብሰን የምናከብረው የኛ ‹‹ቫላንታይን ደይ›› እንደሆነ አስተምረናቸው ወደ ቢሯችን ተመለስን፡፡
ነገሩ ገርሞኝም አስቆኝም ስለነበር፤ እነዚህ ነጮች እንዲህ ‹‹እንደሱ አይደለም›› የሚላቸው ባይኖር ኖሮ ሀገራቸው ሲሄዱ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች ለጥምቀት ለጥምቀት በወንዶች ይደበደባሉ›› ብለው ሊፅፉም ሊያወሩም ይችሉ እንደነበር አሰብኩ፡፡
ማን ያውቃል! ትንሽ ብር ካገኙ ዘመቻም ሊጀምሩ ይችሉ ነበር፡፡
‹‹በሴቶች ላይ የሚደረግ አካላዊ ጥቃትና ትንኮሳ ይቅር! በዘንድሮው ጥምቀት ሎሚ ባለመወርወር ብልህ ወንድ መሆንህን አረጋግጥ›› የሚል ወንዶችን ያማከለ ዘመቻ!
ለሁሉም መልካም የከተራ እና የጥምቀት በአል ይሁንላችሁ፡፡
ሎሚውና ደረቱ እስካለ ድረስ ወንዶችም ሲወረውሩ፣ እኛም ስንሽኮረመም እንውላለን፡፡
No comments:
Post a Comment