ጥር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አባይ ወንዘን ተንተርሶ በሱዳናዊው ባለሀብት የተቋቋመው የስጋ ፣ የዶሮ፣ የዘይት፣ የአትክልትና ፍራፍሮ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ላለፋት አምስት ዓመታት የተወራለትን ያህል ማምረት እና ማሰራጨት ባለመቻሉ የክልሉ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቤሮ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ወስኗል። የከተማ አሰተዳደረም ቦታውን ለሌላ አልሚ እንዲሰጥ ታዟል፡፡
የክልሉ መንግስት ለሱዲናዊው ባለሃብት ሚ/ር አሽራፍ፣ በባህርዳር የሚገኘውን የዘይት ፋብሪካ እና የግንባታ ቦታ በ65 ሚሊዬን ብር እንደሸጠላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለሀብቱ በሰራተኞች ላይ ከባድ ጥፋት ሲፈጽሙ መንግስት አይቶ እንዳላየ ሲያልፋቸው ቆይቷል። ባለሀብቱና በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት የሱዳን ዜጎች ከአባይ ወንዝና ከፖለቲካ ጉዳዩች ጋር በተያያዘ የደህንነት ሚስጥሮችን ለሱዳን አሳልፈው ይሰጣሉ እየተባሉ ይጠረጠሩ ነበር። ድርጅታቸውም ሁለተኛው ኢምባሲ ተደርጎ በክልሉ ባለስልጣኖች ዘንድ ይቆጠር ነበር፡፡
ድርጅቱ 234 ሰራተኞችን ያለምን ካሳ እና ተገቢ ውሳኔ ማባረሩን ተከትሎ ስራውን አቋርጦ እንዲወጣ የቀድሞው የክልሉ ኘሬዝዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ከአሁን በፊት ደብዳቤ ቢጽፉም፣ የፊደራል መንግስት ጣልቃ በመግባት ”ቦታውን የሰጠው የፊድራል መንግስት እንጅ ክልሉ አይደለም በሚል የፕሬዚዳንቱ ማስጠንቀቂያ ውድቅ ተደርጎ ባለሀብቱ ይቅርታ እንዲባሉ ተደርጓል።
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ድርጅቱ 5ዐ ሚሊዩን ብር ኢንቨስት በማድረግ ጁሶችን ማምረት ጀምሮ እንደነበረ ገልጸው፣ ይሁን እንጅ ለ 2 ዓመታት በገበያ እጦት የተነሳ ምርቶቹ ለብልሽት ተዳርገዋል። የአሠራር ስርዓቱ ምቹ አለመሆኑንና መንግስት ሆን ብሎ የደህንነት ሰራተኛችን በመመደቡ ለስራው እንቅፋት መሆኑን ስራአስኪያጁ ይናገራሉ።
በባለሀብቱና በክልሉ ባለስልጣናት መካከል የተጀመረው እሰጥ አገባ እየጨመረ የመጣው ባለሀብቱ ጨረጨራ ግድብ ዳር የእንግዳ ማረፊያ ቤት ለመገንባት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ክልሉ ውድቅ በማድረጉ ነው። መንግስት ጥያቄያቸውን ከስለላ ለይቶ ባለመመልከቱ ሙሉ በሙሉ የመኖሪያ ቤት ግንባታው በፋበሪካው ውስጥ ብቻ እንዲወሰን አድርጎ ቆይቷል፡፡
መንግስት በባለሃብቱ ላይ ከኩርፊያና ከግሳጼ የዘለለ ርምጃ ሳይወስድ ቆይቶ በመጨረሻ ባለሀብቱ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ውሳኔ ላይ መድረሱን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።
No comments:
Post a Comment