Sunday, January 19, 2014

* የቻይና ኩባንያ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተነጠቀ *



የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከስምንት ዓመት በፊት ለቻይናው ኩባንያ ሲኖ ኃይድሮ ሰጥቶት የነበረውን የጨሞጋ ያዳ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክትን አዲሱ ማኔጅመንት ነጠቀ፡፡

በቅርቡ የተቋቋመው ኢንተርፕራይዝ ማኔጅመንት ፕሮጀክቱ ሌሎች ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጨረታ እንዲወጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 

ሲኖ ኃይድሮ በ1999 ዓ.ም. የጨሞጋ ያዳ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራርሞ መረከቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ይህንን ፕሮጀክት የቻይናው ኤግዚም ባንክ ፋይናንስ እንደሚያደርግ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ጨሞጋና ያዳ ወንዞች የዓባይ ገባር ናቸው በሚል ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ ለማድረግ የያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መቸገሩ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ሲኖ ኃይድሮ ገንዘቡ ይለቀቃል በሚል ይህንን ፕሮጀክት በእጁ ቢያቆየውም፣ መንግሥት ተስፋ ቆርጦ ፕሮጀክቱን ነጥቋል፡፡ በዚህ መሠረት ለፕሮጀክቱ አዲስ የፋይናንስ ምንጭ እንዲፈለገና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጨረታ እንዲወጣ ተወስኗል፡፡

ሲኖ ኃይድሮ የራሱን የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርጐ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎችን ሲያናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በታለመለት ጊዜ አለመሄዱ እንዳሳሰበው አሠሪ መሥርያ ቤቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብለትም፣ ሲኖ ኃይድሮ ስድስት ጊዜ በጻፈው ደብዳቤ የፕሮጀክቱ ፋይናንስ እንደሚለቀቅ በመግለጽ ተማፅኖውን ያቀርብ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የሚጠበቀው ፋይናንስ የውኃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ ተስፋ የቆረጠው መንግሥት በመጨረሻ የመንጠቅ ዕርምጃ ወስዷል፡፡

በወቅቱ ፕሮጀክቱ በአራት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ከመባሉም በላይ፣ ግንባታው እውን ቢሆን 278 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት 555 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ በመሆኑ የቻይናው ኤግዚም ባንክ ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ለማድረግ ተስማምቶ ነበር፡፡

የጨሞጋ ያዳ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአማራ ክልል ምሥራቅ ጐጃም ዞን፣ ደብረ ማርቆስ ከተማ መውጫ ላይ ይገኛል፡፡ የኃይል ማመንጫው የሚገኝባቸው ወንዞች የዓባይ ገባር በመሆናቸው በዚህ ምክንያት የቻይና ኤግዚም ባንክ ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ እንዳያደርግ በነግብፅ ጫና ተደርጐበት ሊሆን ይችላል ሲሉ ምንጮች ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡

ምንጭ: ሪፓርተር

No comments:

Post a Comment