ከስምንት ወራት በላይ በፓርላማው ከፍተኛ ክርክር ሲደረግበት የቆየው የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ፣ ባለፈው ሐሙስ በተካሄደው መደበኛ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያለ ምንም ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ፀደቀ፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ለመጀመርያ ጊዜ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ረቂቁ በውስጡ ካካተታቸው አንቀፆች መሀል መሬትን የማስተዳደርና ሕግን የማውጣት ኃላፊነት በተመለከተ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል አይጋጭም በሚል፣ በፓርላማው ከፍተኛ የሐሳብ ክፍፍል በመፈጠሩ ምክንያት ነበር ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው፡፡
በተለይ ባለፈው ወር ፓርላማው በረቂቁ አዋጅ ላይ ሲወያይ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ምክንያት ፓርላማው ለሁለት መከፈሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የረቂቅ አዋጁ በተለይ አንቀጽ 42፣ 47፣ 49 እና 56 የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች በተመለከተ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተመራ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጁ በቀረበበት መንገድ እንዲቀጥል ይሁንታ መስጠቱንም ከሳምንት በፊት ተዘግቧል፡፡
አዋጁ የወጣው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ (7) በመጥቀስ ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ ማሻሻል ሙሉ መብት መስጠትን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት የአገሪቱ ከተሞች የይዞታና ንብረት ምዝገባና ማስተላለፍ ሥርዓት በአግባቡ በመያዝ፣ ከመሬት ይዞታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መብቶች፣ ክልከላዎችና ግዴታዎችን ሕጋዊነት ያረጋግጣል፡፡ ዜጎች በይዞታቸው ላይ ላፈሩት ቋሚ ንብረት የሕግ ዋስትና በመስጠት በከተሞች የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ቋሚ ንብረት ወደ ገበያ እንዲገባ ማመቻቸትና ዜጎች የእንቅስቃሴው አካልና ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ከአዋጁ ዓላማዎች ውስጥ ጥቂቶቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ነገር ግን በውይይቱ ወቅት ከፍተኛ ክርክርና የሐሳብ መከፋፈልን ያስተናገደው አዋጅ በቀላሉ ሲፀድቅ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልቀረበበትም፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment