Thursday, January 2, 2014

ይድረስ ለብአዴን አባላት::


ይድረስ ለብአዴን አባላት
Image
በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ ወደ ባህር ዳር አቅንተው ነበር። መቸስ በረከት ስምዖን አማራ ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ አለመንደሩ የአማራ ህዝብ መሪ እኔ ነኝ ብሎ ከአማራ ህዝብ ፊት ሲቆም አለማፈሩ ያስገርማል። አዲሱ ለገሰም እንደ በረከት ራሱን የአማራ ህዝብ ወኪል እኔ ነኝ ይላል።እነዚህ ሁሉት ህወሃት የሠራቸው ፍጡራን ባህር ዳር እንዲወርዱ ያደረጋቸው ብአዴን ተዳክሟል ተብሎ መታሠቡ ነበር።
እንግዲህ በእንበረከት የአስተሳሰብ ደረጃ ብአዴን ተዳከመ ሲባል ምን ማለት ይሆን?
ከጥቂት ደካማ ካድሬዎች በቀር ሌሎች እንደ ሰው ማሰብ የሚችሉ የብአዴን አባላት አገሪቷ እየሄደች ያለችበት መንገድ ያሳስባቸዋል። ህወሃት በአማራ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ የሚያንገበግባቸው በርካታ ናቸው። ጉርፋርዳ እና ቤንሻንጉል አገራችሁ አይደለም ተብለው አማሮች ከኖሩበት ቀየ ተፈናቀለው ሜዳ ላይ የመውደቃቸው ድርጊት የእግር እሳት ሁኖ የሚለበልባቸው ብዙዎች አሉ። በዚህ ሁኔታ ያዘኑና የተቆጡ የብአዴን ካድሬዎች ድርጅቱ ቆሜለታለው የሚለው ፍትህ የት አለ፤ እኩልነትስ ከወዴት አለ፤ ኢትዮጵያስ የሁላችን አገር ነች የምትባለው መገለጫው ምንድ ነው እያሉ ይጠይቃሉ። እነዚህ ጥያቄዎች በካድሬዎች መካከል መመላለስ ሲጀምሩ ድርጅቱ ተዳክሟል ተብሎ ግምገማ ይካሄዳል።
በረከት እና አዲሱ ነፃነትን ሳያውቁ ራሳቸውን ነፃ አውጪ አድርገው የሚቆጥሩ የህወሃትን ዙፋን ከመጠበቅ የዘለለ ምንም ሚና የሌላቸው ያልሆኑትን ለመሆን የሚውተረተሩ ደካሞች መሆናቸውን እናውቃለን። እነዚህ ግለሰቦች ስለ አማራ ህዝብ ነፃነትና ክብር ይሠራሉ ብሎ ማሰብ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። በረከትና አዲሱ በህዝብ መካከል እየኖሩ የህዝብ ፍቅር የሌላቸው፤ ከህዝቡ ጋር መኖርንም የማያውቁ፤ እለት ዕለት በሚፈጥሩት የፍርሃት አረንቋ ውስጥ የሚኖሩ እና ሠላም የራቃቸው ግለሰቦች ናቸው። ከእነዚህ ግለሰቦች እውነትን ፈልጎ ማግኘት፤ ነፃነትን ጠይቆ መቀዳጀት፤ ለፍትህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻል አይደለም። የአማራ ህዝብ ከጉራፋርዳ እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ምንድ ነው ተብለው ሲጠየቁ የጠባቦች ጥያቄ ብለው ይሳደባሉ። አያቶቻችን በደምና አጥንታቸው ያቆዩልንን ድንበር አፍርሳችሁ ለባእዳን ለምን ትሰጣላችሁ ሲባሉ የጦርነት ናፋቂ ጥያቄ እያሉ ይዘባበታሉ። እንደምን ሁኖ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ ከቁጥሩ ጎድሎ ተገኘ ሲባሉ የትምክህተኞች ወሬ እያሉ ይሳለቃሉ። አዎን እነበረከት ስምዖን የሚፈልጉት ዜጎች ስድባቸውን ተሸከመው እንዲኖሩላቸው እንጂ እውነትን፤ ፍትህን እና እኩልነትን እንዲጠይቁ አይደለም።
የሰሞኑ የባህር ዳር አስቸኳይ ስብሰባ ምክንያትም በብአዴን ካድሬዎች መካከል የፍትህ፤ የነፃነት እና የእኩልነት ጥያቄዎች ሥር እየሰደዱ መምጣታችው ነው። በካድሬዎቹ መካከል እንደ እሳት ሰደደ እየተሰራጩ ላሉ የፍትህ፤ የነፃነት እና የእኩልነት እጦት ጥያቄዎች ከህወሃት መራሹ “መንግስት መሰል” አካል በቀላሉ መልስ ማግኘት የሚቻል አይደለም። ይሄ ቡድን ነፃነትን ሳያውቅ ነፃ አወጣኋችሁ ማለትን ብቻ የሚያውቅ፤ራሱ ለሠራው ህግ መገዛትን ሳይወድ ስለ ህገ-መንግስት የበላይነት የሚሰብክ፤ ራሱ ከሁሉ በላይ እኔ ነኝ ብሎ ሲያበቃ ስለ እኩልነት ለመስበክ የማያቅማማ የነውረኞች ስብሰብ ነው። በረከትና አዲሱም የዚህ ነውረኛ ቡድን አካል እንጂ የአማራ ህዝብ አካል ናቸው ለማለት ለአማራ ህዝብ የሠሩት በጎ ነገርን ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።
የብአዴን ካድሬዎች ሆይ !
ብአዴን ከተመሠረተ በኋላ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ መጥፋቱን በፓርላማ ሪፖርት መደረጉን ሰምተችኋል።ለመሆኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማራ የት ጠፋ? በአገሪቷ ካሉ ብሄረ ብሄረሰቦች መካከል እንደምን ሁኖ የአማራ ቁጥር ብቻ ሊቀንስ ቻለ? ከአማራ ክልል ወጥተው በሌላ ክልል የሚኖሩ አማሮች ይሄ አገራችሁ አይደለም፤ ወደ አገራችሁ ሂዱ ተብለው የሚባረሩት ለምንድ ነው? ኢትዮጵያ አገራቸው ካልሆነች የእነዚህ አማሮች አገር ወደየት አለች? ከጉራፈርዳ እና ከቤንሻንጉል ተነቅለው ሜዳ ላይ እንዲወድቁ የተደረጉ አማሮች በደላቸው ምንድ ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች አማራ ካልሆንን ሞተን እንገኛለን የሚሉት በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ መልስ አይሰጡም። እነርሱ የቆሙት በህወሃት “የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት አማራ ነው” ተብሎ የተያዘውን እምነት በተግባር ለማስፈፀም እንጂ ለአማራ ህዝብ ደህንነት እንዳለሆነ ምግባራቸው ህያው ምስክር ነው።
ብአዴን ከተመሠረተ ዘመን ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ እናውቃለን። የአማራን ቅስም መሰበር፤ ትምክህቱን ማስተንፈስ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ማዋረድ የሚሉት የእነበረከት ስምዖን ዋነኛው መፈክሮቻቸው ናቸው።በዚህ መፈክር መሪነት ከሁለት ሚሊዮን በላይ አማሮች ጠፍተዋል፤ኢትዮጵያ አገራችሁ አይደለችም ተብለው ከጉራፈርዳ እና ከቤንሻንጉል ውጡ ተብለው ሜዳ ላይ ተጥለዋል። ከንግዱ አምባም ሳይቀር ቀስ በቀስ አማሮች እንዲጠፉ ተደርገው ሥፍራቸውን ለሌላ እንዲለቁ ሁነዋል። ከፕሮፌሰር አሥራት ጀምሮ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምልክት እና ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አማሮች ቀስ በቀስ እንዲጠፉ መደረጋቸውን በአይናችን አይተናል በጆሮአችንም ሰምተናል። ብአዴን የተባለው ድርጅት በአማራ ስም ቢቋቋምም አማሮችን ከውርደትና ከሚደርስባቸው በደል ሊታደጋቸው አልቻለም።እንዲያውም ግፉንና በደሉን ለማስፈፀም የተወከለ ድርጅት ሁኗል።
እንግዲህ የብአዴን ካድሬዎች ሆይ እናንተም ከበረክተ ስምዖንና ከአዲሱ ለገሰ ጋር ተሰልፋችሁ ህዝባችሁን ትወጉ ዘንድ አይገባም። ዙሮ መግቢያችሁ ዛሬ እንወክለዋለን ያላችሁት ግን ደግሞ በአሣር በመከራ ውስጥ ያለው ህዝብ እንጂ ሌላ ዙሮ መግቢያ እንደሌላችሁ እወቁ። የወከላችሁት ህዝብ ሲረገጥ የለም ህዝቤን አትበድሉ ማለት ይጠበቅባችኋል። አማራ ከቁጥሩ ጎደለ ሲባል ምን ሆኖ እንደጎደለ በመጠየቅ የችግሩን ምንጭ ማወቅ ሥራችሁ ነው። አማራ ወደ “አገርህ” ሂድ ተብሎ ከኖረበት ሲነቀል ኢትዮጵያ አገሩ ካልሆነች የአማራ አገሩ የት ነው ብላችሁ መጠይቅ አለባችሁ።
ዛሬ እናንተን ትምክህተኞች እያለ የሚገመግማችሁ በረከት ስምዖን አያሌው ጎበዜን አስነስቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲተካ አድርጓል። የአያሌው መሄድና የገዱ መምጣት ለአማራ ህዝብ ነፃነት እና ክብር የሚፈይደው አንዳችም ቁም ነገር የለም። አያሌውም ሆነ ገዱ ለቆሙለት ህዝብ ይቅርና ለራሳቸውም ክብር የሌላቸው ደካሞች መሆናቸው የታወቀ ነው። ለራሱ ክብር ያለው የህዝብ ወኪል እወክለዋለው የሚለው ህዝብ ከኖረበት ቀየ እየተነቀለ ሜዳ ላይ ሲጣል አይቶ ዝምታን አይመርጥም። አያሌውና ገዱ ከአማራ ህዝብ አብራክ ወጥተው ደሃውን አማራ በሙሉ ነፍጠኛ፤ ትምክህተኛ፤ ሌላም ሌላም እያሉ እየሰደቡ ለሳዳቢ አሳላፈው የሰጡ ደካሞች ናቸው። ካድሬ ሆይ ስማን! የገዱ በአያሌው መተካት የተዋረደውን ክብርህን አይመልሰውም። ያጣኸውን ነፃነት መልሶ አያቀዳጅህም። ለሱዳን ተቆርሶ የተሰጠውን በአያቶችህ ደምና አጥንት የቆየውን መሬትም አይመልስልህም። የብአዴን ካድሬዎች ሆይ ስሙ ለክብራችሁ፤ ለማንነታችሁ፤ ለነፃነታችሁ ቀናዒ እንድትሆኑ ሁኑ እንጂ የህወሃትን ትርፍራፊ የምትለቃቅሙ አትሁኑ።
በብአዴን ውስጥ ያላችሁ የንቅናቄያችን አባሎች ሆይ !!
የህወሃት ስንቅና ትጥቁ ጥላቻ መሆኑን ታውቃላችሁ። ህወሃት “አማራ የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው” ብሎ የሚያምን ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት ያለመስዋእትነት እንደማይገኝ መዘንጋት አያስፈልግም። እስከ አሁን የንቅናቄያችንን መሠረት ለማሲያዝ ያደረጋችሁት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በህወሃት የተነጠቀው ነፃነታችን፤ የተዋረደው ክብራችንና ማንነታችን በቀላሉ እንደማይመለስ መገንዘብ ይኖርብናል። ትግሉ መራራ የሚሆንበት ግዜ መጥቷል። ለነፃነትና ለማንነት የሚከፈል መሥዋእትነት ደግሞ አስፈላጊ መሥዋዕትነት ነው።ጥቂት ዘረኞች አንገታችንን አስደፍተው በማንነታችን ላይ ተሳልቀው፤ ህዝባችንን አጎሳቁለውና ረግጠው ሲገዙ በአይናችን እያየንና በጆሮአችን እየሰማን ተንጋለን ለመተኛት አልተፈጠርንም። እንዲህ ዓይነቱን ሥንፍና ከቀደሙት ከኩሮዎቹ አያቶቻችንና አባቶቻችን አልተማርንም።
በአውሬው መረብ ውስጥ ሁናችሁ የለውጥ ኃዋሪያ ለመሆን መነሳታችሁ የሚደነቅ ነው።የለውጥ ኃዋሪያነት ትልቅ ሸከም ያለው ነው።ጥላቻን ወደ ፍቅር የሚቀይር፤ ለይቅርታ ራስን ማዘጋጀት፤ ከግዜያዊ ጥቅም ይልቅ ትውልድን አሻግሮ የማየት ራዕይን የሚጠይቅ ነው። ህወሃት አገሪቷን እያፈረሰ ያለው ከፍቅር ይልቅ በጥላቻ ስለተሞላ፤ ከይቅርታ ይልቅ በበቀል ልቦና የሚመላለስ በመሆኑን፤ ትውልድን አሻግሮ ከማየት ይልቅ የስግብግብነት ስሜቱ ያየለበት ሆኖ በመገኘቱ ነው። ንቅናቄያችን ይህን ከመሰለ አገር አጥፊ አስተሳሰብ በላይ ነው። ንቅናቄያችን ሁል ግዜ ለይቅርታ የተዘጋጀ ልቦና አለው። ይሄ ሲባል ግን የበቀለኞችን ሠይፍ ለመመከት ራሱን አያዘጋጅም ማለት አይደለም። እንዲያውም ሰይፋችን ከእነርሱ ሠይፍ በላይ የሳለ መሆኑን ያውቁት ዘንድ እንወዳለን። ንቅናቄያችን ትውልድን አሻግሮ የሚያይ ባለ ረዥም ራዕይ ነው። እንደ ህወሃት ለዘረፋ የተሠለፈ፤ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል የሚል አይደለም። ዘራፊውንና እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይበቀል የሚለውን ሁሉ ነቅሎ ሥፍራውን ለማስለቀቅ ሳያቅማማ በፅናት የሚሠራ ነው።
በብአዴን ውስጥ ያላችሁ የንቅናቄው አባላት ሆይ!!
የገዱ በአያሌው መተካት የሚያመጣው ለውጥ የለም።አያሌው ሄደ ገዱ መጣ ሁለቱም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ደካሞች ናቸው። ገዱ የነፃነትን፤የፍትህንና የእኩልነትን ዋጋ የሚያውቅ አይደለም። ገዱ ሲሊኩት ወደየት፤ ሲጠሩት አቤት ከማለት የዘለለ ለዚያች አገር ለውጥ የሚፈይደው አንዳችም ነገር እንደማይኖር እወቁ። ስለሆነም የተጀመረውን ትግል ከዳር ለማድረስ ሳታቅማሙ በፅናት ቁሙ። ፍርሃትን ግደሉት። ከፍርሃት አርነት የሚያወጣን ነፃነት፤ ፍትህና እኩልነት ብቻ ነው። እነዚህ ለሰው ልጆች መሠረታዊ ቁም ነገሮች በአገሪቷ ሰፍነው ዜጎች ሁሉ እፎይ እሰከሚሉ ድረስ የሚከፈለውን መሥዋ ዕትነት ለመክፈል ወደ ኋላ እንዳትሉ። በእኛም በኩል አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የጀመርነውንም ትግል ሳናቅማማ እና ሳናፈገፍግ እንቀጥላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment