Wednesday, January 1, 2014

ዶ/ር ነጋሶ ከፓርቲ ፖለቲካ ለመሰናበት ከጫፍ ደርሰዋል


በታሪክ ትምህርት ከጀርመን ሀገር በፒኤችዲ በላቀ እውቀት የተመረቁት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከተማሪዎች ንቅናቄ፣ በኦነግ፣ በኦህዴድ/ኢህአዴግ እና በአንድነት/መድረክ የፖለቲካ ቆይታ ያደረጉት፣ በግል ስብዕናቸው በገዢውም በተቃዋሚውም አባላት ከበሬታንና ተወዳጅነትን ያተረፉት የ70 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከፓርቲ ፖለቲካ ለመሰናበት ከጫፍ ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።
ዶ/ር ነጋሶ ለሁለት ዓመት በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን (አንድነት) የምርጫ ጊዜያቸውን በማጠናቀቅም ኃላፊነታቸውን ለተተኪያቸው ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አስረክበዋል። የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ከገዢው ፓርቲ ጋር በሃሳብ ከተለዩ በኋላ ለእምነታቸው በርካታ ውጣ ውረድን ማሳለፋቸው ይታወቃል። ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ፓርቲው አዲስ አበባ ውስጥ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው መጠናቀቂያ ላይ በፓርቲው ለነበራቸው ገምቢና አዎንታዊ ቆይታ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
ዶ/ር ነጋሶ ፓርቲው በቅርቡ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚለው ሕዝባዊ ንቅናቄ በቀዳሚነት በመሳተፍ አባላት ሲታሰሩ በመታሰር ጭምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ተወዳጅነትና ተደናቂነትን አትርፈዋል።
ይሁን እንጂ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወደተቃዋሚው ጎራ በመቀላቀል ሲጀመር የስድስት ፓርቲዎች አሁን ደግሞ የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነውን “መድረክ” እውን እንዲሆን በርካታ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን ጥረታቸው በብዙሃኑ የአንድነት አባላትን ያሳመነ ባለመሆኑና ውትወታቸው ሚዛን ባለመድፋቱ በ1993 ዓ.ም ከገዢው ፓርቲ ጋር ገጥሟቸው ከነበረው የኀሳብ ልዩነት ጋር ሊቀራረብ የሚችል የኀሳብ ልዩነት አጋጥሟቸዋል።
የኀሳብ ልዩነቱ በዶ/ር ነጋሶ በኩል መድረክ “በግንባር” አደረጃጀት መቀጠል ሲፈልጉ ብዙሃኑ የአንድነት አባላት ግን በሦስት ወር ውስጥ አንድነት ከመድረክ ጋር ያለውን ግንኙነት ላይ እልባት እንዲሰጥ፣ ውህደትም ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚል ውሳኔ በፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ በኩል አሳልፏል።
“በብዙሃን የኀሳብ የበላይነት እገዛለሁ” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ መድረክ በግንባርነት መቀጠሉ ይጠቅማል በሚል የፀና አቋም መያዛቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋግጠዋል። የእሳቸው ኀሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሚያጣ መሆኑንም ሲያረጋግጡ ከአንድነት ፓርቲ እንደሚለቁና ከእንግዲህ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንደማያደርጉ፣ በግል ተሳትፎአቸው ድምፃቸውን በልዩ ልዩ መንገድ እያሰሙ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

No comments:

Post a Comment