Sunday, June 29, 2014

‹‹ያለ ፈቃድ መሬቱንም ፎቶ ማንሳት አይቻልም›› ፖሊስ



የጦማሪያኑን የፍርድ ውሎ የሚከታተለው ሰው ዛሬም እንደወትሮው በጠዋት ነው የተገኘው፡፡ አራት ሰዓት ካለፈ በኋላ የጦማሪያኑ ጠበቃ ‹‹መዝገብ ቤቷ ስለሌለች ነገ ከሰዓት ተብሏል›› ብለው ሲነግሩን በርካታ ህዝብ በተገኘበት አንዲት መዝገብ ቤት በመቅረቷ ብቻ የፍርድ ውሎው እንዲራዘም መደረጉ ገርሞን ስለጉዳዩ እያወራን ለጥቂት ደቂቃዎች ግቢው ውስጥ ቆየን፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እየመጡ ነው ተባለ፡፡
የውሎው ትዕይንት እዚህ ላይ ነው የተጀመረው፡፡
ሶስቱም ጦማሪያን ሲመጡ ህዝቡ በጭብጨባ ተቀበላቸው፡፡ በድንገት እዚህ እዚያ የሚራወጡት ፖሊሶች ወደተሰበሰበው ሰው እየሮጡ በመምጣት የሰማያዊ ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ አባል የሆነችውን ምኞት መኮንንን ‹‹ፎቶ ግራፍ አንስተሻል፡፡›› በሚል ማንገላላት ጀመሩ፡፡ በኃይል እየጎተቱ ሲወስዷትም ዮናታን ተስፋዬ ‹‹እኔን ውሰዱኝ›› ብሎ ምኞትን በኃይል እየገፈተሩ የሚወስዱት ፖሊሶች መሃል ገባ፡፡ ፖሊስ ግን እሱንም ማንገላላት ጀመረ፡፡ እሱንም አብረው ወሰዱት፡፡ ምኞትና ዮናታን ጦማሪያኑን ተከትለው ችሎቱ ወደሚገኝበት ቦታ ከተወሰዱ በኋላ ፖሊሶቹ ህዝቡ እንዲበተን ማስፈራራት ጀመሩ፡፡
ፖሊሶቹ ከሚመጡበት በኩል የርዕዮት ዓለሙ አባት ጠበቃ አለሙ፣ እህቷ እስከዳር አለሙ፣ ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ፣ 6 ያህል የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አባላትና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ‹‹ወዴት ነው የምንሄደው?›› በሚል እንደማይወጡ አሳወቁ፡፡ ፖሊሶቹ ‹‹ታዘነ ነው፡፡ ትወጡ እንደሆነ ውጡ!›› እያሉ ማስፈራራት ጀመሩ፡፡ ከፊት ያሉት ሰዎች ‹‹ችሎት መከታተል መብታችን ነው!›› ብለው አንወጣም ሲሏቸው እነ ምኞት ላይ የተወሰደውን እርምጃ ትክክለኛነት ለመግለጽ ፎቶ ማንሳት ክልክል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ በተለይ አንዱ ፖሊስ ‹‹ያለ ፈቃድ ፎቶ ማንሳት አይቻልም፡፡ ሳይፈቀድ መሬቱንም ቢሆን ፎቶ ማንሳት አይቻልም›› ያለበት ሁሉንም ያስገረመ ነበር፡፡ በዚህ ፖሊስ አባባል የተሰበሰበው ሁሉ እያረረም ቢሆን ፈገግ ብሎበታል፡፡

No comments:

Post a Comment