Friday, December 5, 2014

በትግራይ፣ አማራ ክልሎች የሃይማኖት መሪዎች የተሰጣቸውን የደህንነት ስራ በትክልል አልሰሩም በሚል ተተቹ // የከምባታ ጠንባሮ ዞን ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ተገለጸ

በትግራይ፣ አማራ ክልሎች የሃይማኖት መሪዎች የተሰጣቸውን የደህንነት ስራ በትክልል አልሰሩም በሚል ተተቹ
ኀዳር ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ባዘጋጀው የ2006 የጸጥታ የደህንነት ግምገማ ላይ የተገኙ የተለያዩ ክልሎች የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች ባቀረቡት ሪፖርት በአዲስ አበባ የሃይማኖት አባቶች የተሰጣቸውን የደህንነት ተልእኮ በፈቃደኝነት አምነው ሲፈጽሙ በትግራይና ፣ በአማራ ክልሎች ግን የሃይማኖት አባቶች ተልእኮዋቸውን በአግባቡ ሳይወጡ ቀርተዋል።
የትግራይ ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ እንደተናገሩት በክልሉ አብዛኛው ህዝብ የኦሮቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ቢሆንም፣ የሃይማኖት አባቶች ሽማግሌዎች በመሆናቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ እንደ ፌደራል የሃይማኖት አባቶች በአግባቡ እንደማይፈጽሙና ከአመራሩ መመሪያ የሚጠብቁ የራስ ተነሳሽነት የሌላቸውና የአቅም ውስንነት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ይህንኑ ሃሳብ የአጠናከሩት የአማራው ክልል የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደሴ አሰሜ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን ከክልል እስከወረዳ ለማደራጀት ቢሞከርም ተነሳሽነት በመጥፋቱ የታሰበው ሊሳካ አለመቻሉን ገልጸዋል። በተለያዩ ቦታዎች መስኪዶችን ከአክራሪዎች እጅ እየነጠቁ ለመጅሊሱ ማስረከባቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል ። በኦሮምያ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ደግሞ የፌደራል መጅሊስ አመራሮች መከፋፈላቸውን ገልጸው፣ ክፍፍሉ እስከታች በመውረዱ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሄ መውሰድ ይገባል ብለዋል
በአዲስ አበባ 7ቱም የሃይማኖት ተቋማት ለመንግስት የደህንነት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወቃል።


በገዥው ፓርቲ አድሏዊ አሰራር ምክንያት ልማትና መልካም አስተዳደር ባለመኖሩ የከንባታ ጠንባሮ ነዋሪዎች ዛሬ ህዳር 26/2007 ዓ.ም ዱራሜ ከተማ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን የከምባታ ህዝብ ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዲሎ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ህዝብ ያለ ማንም ቀስቃሽና አስተባባሪ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱን የገለጹት አቶ ኤርጫፎ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አከብራለሁ በሚል ለፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ከማድረጉ ውጭ በተግባር ግን በህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የከንባታና ጠንባሮ ህዝብ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ተቃዋሚዎችን በተለይም የከምባታ ህዝብ ኮንግረንስን ትደግፋላችሁ በሚል በደል እንደሚደርስበት የገለጹት አቶ ኤርጫፎ ‹‹ህዝቡ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በደል እየደረሰበት ነው፡፡ ምርጫ ሲደርስ መንገድ፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ይሰራልሃል ይባላል፡፡ ምርጫው ሲያልፍ ለማታለያነት ይሰራሉ የተባሉ ነገሮች ተግባራዊ አይሆኑም፡፡ እስካሁን ከ1993 ዓ.ም አንስቶ ይሰራል የተባለ መንገድ አልተሰራም፡፡ በምርጫ ወቅት አርሶ አደሮችን እያፈናቀሉ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ እንሰራለን ይላሉ፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን ይህ መሬት የሚሰጠው ለሹመኞች ነው፡፡ ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሮች የምርጫ ሰሞን በየ ቦታው የመሰረት ድንጋይ ተክለዋል፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን ለሹመኞች ይሰጣል፡፡ ዛሬ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣውም ከዚህ አንጻር ነው፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ ህዝብ ባለፉት ምርጫዎች ተቃዋሚዎችን በመምረጥ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ እንዳሳየ የገለጹት አቶ ኤርጫፎ ‹‹ወጣቶች ልማትና የትምህርት እድል ስለማያገኙ ወደ ደቡብ አፍሪካና አረብ አገራት እየተሰደዱ መንገድ ላይ እየሞቱ ነው፡፡ በቀን 11 አስከሬን የመጣበት ጊዜ አለ፡፡ በስርዓቱ አድሏዊ አሰራር ምክንያት ከንባታ ጠንባሮ ወጣቱ ከቀየው እየተፈናቀለ የሚሰደድበት ትልቁ ዞን ነው ማለት ይቻላል፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው እለት አርሶ አደሩ፣ ተማሪውና ነጋዴው የዞኑ ጽፈት ቤት ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረጉም ባሻገር በቀጣይነት በየወረዳዎቹ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚየደርግ ገልጾአል ሲሉ ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡


 የሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳ ቀጥሎ አምሽቷል የአዳር ሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳ ምሽቱን ጭምር ተጠናክሮ እንደቀጠለ በሰማያዊ ፓርቲ በኩል የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ እንደገለጹት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህዝብ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሰላማዊ ሰልፉን ቅስቀሳ እንዲያግዝ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ህዝብ የቅስቀሳ ወረቀቶችን በማባዛት ዛሬ ህዳር 26/2007 ዓ.ም ምሽቱን ወረቀት ሲበትን ማምሸቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት በአራት ኪሎ፣ ከስላሴ ጀምሮ በፒያሳና ማዕከላዊ ጀርባ በሚገኙ ሰፈሮች እንዲሁም በአዲሱ ገበያ ወረቀቶች እንደተበተኑ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት የ9ኙ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ ያዘጋጁት ስቲከር በተለያዩ የከተማይቱ አካባቢዎች እንደተለጠፉ መገለጹ ይታወቃል፡

No comments:

Post a Comment