Thursday, December 18, 2014

የሰሞኑ አደናጋሪ ወሬዎች ,,በአባዱላ ገመዳ የተመራ "የፐብሊክ ዲፕሎማሲ" ልዑክ ቡድን ወደ ግብጽ አምርቷል ,,."የህዝብ ፍላጎት ከሆነ ጅቡቲን ከኢትዮጵያ ጋር እናዋህዳታለን"...



Fasil Yenealem
የሰሞኑ አደናጋሪ ወሬዎች
1- በአባዱላ ገመዳ የተመራ "የፐብሊክ ዲፕሎማሲ" ልዑክ ቡድን ወደ ግብጽ አምርቷል። "ፐብሊክ ዲፕሎማሲ" የተባለው "የህዝብ" ዲፕሎማሲ ለማለት ተፈልጎ መሰለኝ። አባ ዱላ ፖለቲከኛ ነው፣ ያውም አፈ ጉባኤ። ፓለቲከኛው እየመራ የወሰደውን ቡድን እንዴት ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልንለው እንችላለን?። ይሁን ግዴለም ብለን ብንቀበለው እንኳ " ፐብሊክ ዲፕሎማሲ" የሚሰራው ስራ ምንድነው? የሚለውን ለመመለስ በቀላሉ የሚቻል አይመስለኝም። በአለማቀፍ ግንኙነት ውስጥ ፐብሊክ           ዲፕሎማሲ የሚባል ነገር መኖሩን አላውቅም። ዲፕሎማሲ ጥቅምን ለማስጠበቅ ፖለቲከኞች የሚጫወቱት ጨዋታ ነው። የዲፕሎማሲን ጨዋታ የሚጫወቱት ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው። አሸናፊም ተሸናፊም ሆነው የሚወጡት እነሱ ናቸው፤ ጉልበትና እውቀት ያለው ብዙውን ጊዜ አሸናፊ ይሆናል፤ አልፎ አልፎ ጉልበት ሳይኖርህ እውቀት ካለህ ታሸንፋለህ፣ ልክ ኤርትራ በባድሜ ላይ የተደረገውን ክርክር እንዳሸነፈች ማለት ነው ። ፊርማ የማኖር ስልጣንም የእነሱ ብቻ ነው። ህዝብ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ከማድረግ ውጭ ሌላ ሚና የለውም።
ዲፕሎማቶች በቅድሚያ ስልጣናቸውን ከዚያም አገራቸውን ግምት ውስጥ አስገብተው ይደራደራሉ። ጥቅምና ጉዳቱን እየመዘኑ እየሰጡ ይቀበላሉ። ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ በህዝብ ጋጋታ ማስቀየር አይቻልም፤ አይደለም 20 ልኡካን፣ 90 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ግብጽ ቢገቡ እንኳ የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ጥቅማቸውን አስልተው ከሚወስኑት ውሳኔ አንድ ጋት ፈቀቅ አይሉም። ቴውድሮስ አድሃኖም የዲፕሎማሲውን ስራ መስራት ሲያቅተው "የህዝብ ዲፕሎማሲ" እያለ ያታልላል። በህዝብ ጋጋታ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፤ ራስን ለማታለል ወይም በአገር ሃብት ለመቀለድ ካልሆነ በስተቀር።
አንድ አገር የዲፕሎማሲ ሃይል እንዲኖራት ከተፈለገ በቅድሚያ ውስጣዊ ሃይሏን ማጠንከር አለባት። ውስጥህ ተዳክሞ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ልትገነባ አትችልም። በቅድሚያ አገራዊ አንድነት ካልፈጠርክ ባላንጣህ የውስጥህን ችግር ተጠቅሞ የራሱን ጥቅም ያራምድበታል። ግብጽንም ይሁን ሌሎች አገሮችን ደጅ የምንጠናው ውስጣዊ አንድነት ስለሌለን ነው፤ ውስጣዊ አንድነትን ለመመስረት በቅድሚያ አንድ ሊያደርጉን በሚችሉት ላይ መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ አለብን፣ ይህን ማድረግ የምችለው ደግሞ ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ስንችል ብቻ ነው፤ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ፍጹም ባይሆንም ከእርሱ የተሻለ አብሮ የሚያኖር ሌላ ስርዓት እስካሁን ስላልተፈጠረ እሱን ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ህወሃት መራሹ መንግስት፣ ውስጣዊ አንድነትን ሊያመጣ እንደማይችል አይተነዋል፤ ህወሃት እስካልተወገደና የሁሉም የሆነ መንግስት እስካልተመሰረተ ድረስ መቼውን ጠንካራ ዲፕሎማሲ መገንባት አንችልም።
2- ሌላው የገረመኝ የተከበሩ ብቸኛው የፓርላማ አባል የሚባሉት አቶ ግርማ ሰይፉ በዚህ "የፐብሊክ የዲፕሎማሲ" ቡድን ውስጥ መካተታቸው ነው። አቶ ግርማ ስለአባይ ግድብ ጠቀሜታ ግብጾችን ለማስረዳት ነው ወይስ ግብጽን ጎብኝቼ ልምጣ ብለው ነው የሄዱት? በዚህ አያያዛቸው ነገ ለአባይ ቦንድ ቅስቀሳ አውሮፓ ሳናገኛቸው አንቀርም። ሰሞኑን ህገመንግስታችን በነውጠኞችና በታጣቂ ሃይሎች እንዳይፈርስብን ኢህአዴግ ይታደገው እያሉ የጻፉትን የተማጽኖ ደብዳቤ አንብቤዋለሁ፤ ምናልባት ግብጽ እነዚህን ነውጠኞች " እባክሽ አትርጅብን" ብለው ሊለምኑዋት ይሆን ይሄዱት? የኢህአዴግን ፕሮፓጋንዳ አምነው ተቀበሉ ማለት ነው? የምር የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ አንድን የተቃዋሚ አመራር ማሳመን ከቻለ ዘመኑ ተለውጧል ማለት ነው። ለማንኛውም አቶ ግርማን በቅርቡ " ብቸኛው የግል ተወዳዳሪ የፓርላማ አባል" እያልን የምንጠራቸው ይመስለኛል፤ እንደምንም ከተመረጡ ማለቴ ነው።
3- "የህዝብ ፍላጎት ከሆነ ጅቡቲን ከኢትዮጵያ ጋር እናዋህዳታለን" የሚል ዜናም በሪፖርተር በኩል አይቻለሁ። ለጅቡቲው መሪ " ትዋሃዳላችሁ ወይ?" ብለው ጥያቄ የጠየቁት የእኛዎቹ ጋዜጠኞች ናቸው። የእኛዎቹ ጋዜጠኞች አላማቸው ይታወቃል። መንግስት " ጅቡቲ ወደቡዋን ልትዘጋብን ትችላለች" እያለ ለፈረንጅ ሲጽፍ፣ የእኛ ጋዜጠኞች ደግሞ " ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ልትዋሃድ ነው" እያሉ መጻፋቸው በአገዛዙና በወኪል ጋዜጠኞቻቸው መካከል ያለውን አለመናበብ ያሳያል። የጅቡቲ ጋዜጠኞች የእኛዎቹን ገዢዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ቢጠይቁዋቸው ኖሮ ትንሽም ቢሆን አመኔታ ይኖረው ነበር፤ የጅቡቲ ጋዜጠኞች ግን ያውቃሉ፣ መንግስታቸውም ህዝባቸውም ውህደቱን አይፈልገውም።
አንድ አገር ከሌላ አገር ጋር ከመዋሃዱ በፊት ቢያንስ ሶስት ጥቅሞችን እንደሚያገኝ ማረጋገጥ አለበት። አንዱ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ነው። ጅቡቲዎች የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ወደ 850 ዶላር ነው። የእኛ ደግሞ ከ400 ዶላር አይበልጥም። ታዲያ ተረቱም እኮ "ትንሽ ቆሎ ይዘህ ከትልቅ ተጠጋ ነው" የሚለው። ጅቡቲዎች ወደኛ የሚመጡት ድህነታችን ሊካፈሉን ነው? ቀልድ እኮ ነው የምር። ሌላው የመዋሃድ ጠቀሜታ የደህንነት ዋስትና ለማግኘት ነው። ጅቡቲ ደህንነቷን የሚያስጠብቅላት የፈረንሳይ ሚራጅ አለላት። መለዋወጫ የሌላቸው የእኛ ጄቶች እንደማያድኗት በደንብ ታውቃለች። ለደህንነቷ ሰግታ ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሃድበት ምክንያት በፍጹም የለም። ሶስተኛው ጠቀሜታ ስነልቦናዊ ነው። ጀርመኖች ከሁለት ሲከፈሉ የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸው ነበር፤ ኮሪያዎችም እንዲሁ። እነዚህ ህዝቦች ሲዋሃዱ ትልቅ የስነልቦና እረፍት አግኝተዋል። አንድ ህዝብ ናቸውና ዘመድ ከዘመድ መገናኘቱ ለጤና ጥሩ ነው። ጅቡቲ የኢሳና የአፋር መኖሪያ ናት። ስልጣን የያዙት ኢሳዎች ናቸው። ኢሳዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ይልቅ ቅርበታቸው ለእናት ሶማሊያ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ከሚዋሃዱ 5 ኮከብ ባላት ሶማሊያ ውስጥ ቢጠቃለሉ ይመርጣሉ። አፋሮች ስልጣን ቢይዙ ይሁን ብለን ልንቀበል እንችላለን። አፋር ልቡም እምነቱም ኢትዮጵያዊ ነው፤ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚሄድበት ሌላ አገርም የለውም። ኢሳዎች ወደ እኛ ከሚመጡ ወደ ሶማሊያ ቢያዘግሙ ይሻላቸዋል።

No comments:

Post a Comment