Wednesday, December 3, 2014

“ከኦሮሚያ አንፃር፤ ከኢሕዴአግ ደርግ ይሻላል” – ዶ/ር መረራ ጉዲና


ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ ምርጫ 97 እና ምርጫ 2002 በተመለከተ የራሳቸውን ግምገማ ማስፈራቸው የሚታወቅ ነው። ካሰፈሩት ነጥቦች እና መደምደሚያዎች አንፃር ቀጣዩን ምርጫ 2007 እንዴት ይመለከቱታል? ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ ምንስ ይላሉ? የኦሮሞ ሕዝብ ትግልን በተመለከተ ምን ይላሉ? ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኃይል አሰላፍ አንፃር የኦሮሞን ሕዝብ የፖለቲካ ሂደት እንዴት ይገልጽታል? የቀኝ ኃይሎች የፖለቲካ አካሄድን እንዴት ይረዱታል? እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ተወያይተwል። ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ፋኑኤል ክንፉ ያካሄደው ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
merara_gudina_vtim
ሰንደቅ፡-የኢትዮጵያን ምርጫ ሂደት “ምርጫ” እና “ቅርጫ” በሚል አባባል ሲገልፁ ይሰማል። ምን ለማለት ፈልገው ነው?
ዶ/ር መረራ፡-በሀገራችን በበዓላት የቅርጫ ሥጋ የመካፈል ባህል አለ። ቅርጫ ሲካፈል ሁሉም እንደ አቅሙ ይወስዳል። ትልቅ ብር የከፈለ ትልቅ ይወስዳል። ትንሽ ብር የከፈለ በከፈለው መጠን ድርሻውን ያነሳል። በኢትዮጵያ ምርጫ ግን አንድ ጎበዝ ሁሉንም ጠቅልሎ ይወስዳል። ይህን የተዛባ ሁኔታ ለመግለጽ ነው፤ ምርጫ እና ቅርጫ በሚል ለመግለጽ የፈለኩት።
ሰንደቅ፡- በመጽሐፍዎ፤ “በአፍሪካ ሀገር የመንግስት ጥያቄ የአቅም ጥያቄ ነው” በማለት ጽፈዋል። ፅንሰ ሃሳቡ ምንድን ነው?
ዶ/ር መረራ፡-አቅም ሲባል፣ ወታደራዊና ድርጅታዊ አቅም ነው። በተለይ ወታደራዊ አቅም። በአፍሪካ ወታደራዊ አቅም እስከሌለህ ድረስ በሕዝብ ድጋፍ ብቻ የመንግስት ስልጣን አታገኝም። ስልጣን ላይ አትወጣም። በተለይ ተቃዋሚ ከሆንክ ከእስር ቤት ወይም ከስደት አታመልጥም።
ሰንደቅ፡- ይህ የእርስዎ መሰረታዊ አስተሳሰብ ከሆነ፣ በ1997 ዓ.ም፣ በ2002 ዓ.ም አሁን ደግሞ በ2007 ዓ.ም ምርጫ መሳተፍ ለምን አስፈለጋችሁ? የፖለቲካ መጫወቻ ክፍት ቦታ እናገኛለን የሚልስ መነሻ እንዴት አገኛችሁ?
ዶ/ር መረራ፡-የምርጫ ፓርቲዎች በመሆናችን በምርጫው ገፍተናል። ወታደራዊ አቅምም ስለሌለን ከምርጫ ውጪ አማራጭ የለንም። ወደ ምርጫ የገባነው በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እንጂ የፖለቲካ መጫወቻ ክፍተት እናገኛለን ከሚል መነሻ አይደለም።
ሰንደቅ፡- በመፅሐፍዎ ላይ፣ በምርጫ 97 እና በምርጫ 2002 የተቃዋሚውን ጐራ ያልሰራቸው የቤት ስራዎች መኖራቸውን አስፍረዋል። በተለይ የተቃዋሚው ጐራ በትብብር አንድ መሆኑንና ጠንካራ አደረጃጀት አለመያዙ ያስከፈለውን ዋጋ አንስተዋል። አሁንስ በ2007 ዓ.ም ምርጫ የተቃዋሚው ጐራ ይህን ስህተት አርሟል?
ዶ/ር መረራ፡- የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ያላለፉት የታሪክ ፈተና፣ ማሸነፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና በተለይም ተባብሮ የመስራት፣ አቅም ገንብቶ የመስራት፣ ልዩነቶችን አቻችሎ አብሮ የመስራት፣ ተባብሮ ገዢውን ፓርቲ የመግፋት ፖለቲካው አሁንም ድረስ ያላለፉት ታሪክ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም አላለፍነውም። እንደውም ከ97 ጋር ሲተያይ ደከም ብለን የምንታይበት ሁኔታ ነው ያለው።
ስለዚህም ከአሁን ጀምሮ የተቃዋሚው ኃይሎች ቁጭ ብለው አሰላስለው ያለንበትን ሁኔታ መመልከት ተገቢ ነው። በተለይ ትግሉ ወደ ፊት እንዲገፋ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይህን የታሪክ ፈተና ለማለፍ በምንችልበት አቅጣጫ መንቀሳቀስ አለብን። ይህን የታሪክ ፈተና ማለፍ ካልቻልን የትም መድረስ አንችልም። ኢትዮጵያም የትም መሄድ አትችልም። እየተቋሰሉ፣ እየተጣሉ፣ እየተጠላለፉ በተተበተበ ፖለቲካ ውስጥ እየዋዠቁ መኖር፣ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን የተሻለ ስራ እየሰራን እንዳልሆነ ይሰማኛል። የበለጠ ወደ ኋላ ቀርተናል።
ሰንደቅ፡- በመጽሐፍዎ በቀኝ ኃይሎች መቸገርዎን አስፍረዋል። እንደሚታወቀው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ቤት ከመድረክ ጋር ያለውን ግንኙነት በገመገመበት ወቅት በብሔር ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ለመስራት እንደማይችሉ ከስምምነት መድረሳቸው መዘገቡ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር አሁንስ መድረክ ከቀኝ ኃይሎች ጋር ያለው ልዩነት እንደቀጠለ አድርገን መውሰድ እንችላለን ወይ?
ዶ/ር መረራ፡- አንድነት ውስጥ ያሉም ሌሎች በተቃዋሚ ጐራ ያሉ ጓደኞቼን ለመምከር ሞክሬአለሁ። ወደፊት ለመሄድ፣ ወንዝ ለሚያሻግር ፖለቲካ ለመስራት፣ የታሪክ ፈተናን ለማለፍ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የዴሞክራሲ ኃይሎች ነን የሚሉት ተባብረው ካልሰሩ፣ አቅም ገንብተው ካልሰሩ፣ የመቻቻል ፖለቲካ እስካልፈጠሩ ድረስ ለብቻቸው የትም አይደርሱም። ይህ በግልጽ መቀመጥ ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጪ ትርፉ ልፋት ብቻ ነው።
merera_gudina
ተባብረው ካልታገሉ አንድም ገዢውን ፓርቲ አስገድደው ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲቀበል ማስገደድ አይችሉም። ገዢው ፓርቲ እንኳን በድንገት ከስልጣን ላይ ቢወርድ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመምራት የሚችሉበት ሁኔታ አይፈጠርም። ኢትዮጵያን ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት አንድ ፓርቲ ለብቻው እገዛለሁ፣ አስተዳድራለሁ የሚለው ነገር ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይ ማብቃት አለበት። ኢሕአዴግ ሚሊዮን ሰራዊት ይዞ፣ የሀገሪቷን ሃብት ተቆጣጥሮ ሁሉንም ነገር ይዞ፣ ኢትዮጵያን በፈለገበት መንገድ መግዛት አልቻለም። ሃያ ሦስት ዓመት ለፋ እንጂ በሕዝብ ፈቃድ በተፈለገው መንገድ ማስተዳደር አልቻለም። ለሰላምና መረጋጋት በሚል ከፍተኛ የሀገሪቷ ሐብትም እየባከነ ነው የሚገኘው።
ከዚህ መለስ ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ የሕልም ጉዞ ከመጓዝ ውጪ ኢሕአዴግ ከስልጣን አውርዶ የተሻለች ኢትዮጵያን፣ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከተፈለገ የግድ ተቃዋሚዎች ተባብረው መስራት አለባቸው። ልዩነቶችን አቻችለው ከወዲሁ የሞኝ ጉዞአቸውን አቁመው የተደቀነባቸውን የታሪክ ፈተና ለማለፍ መስራት አለባቸው። ይህን ማድረግ ካልቻሉ የትም አይደርሱም። ከዚህ ውጪ ያለው መንገድ አላስፈላጊ ሐብታችንን፣ ገንዘባችን እውቀታችንን ለማባከን ነው የሚሆነው። ተቃዋሚው ኃይል ከገቡበት የታሪክ እስር ቤት ሰብረው መውጣት አለባቸው። የዛሬ አርባ አመት ያልቻልነው ይሄንኑ ነው። ዛሬም ያልቻልነው ይህኑኑ ነው። ያ ቡድን… ይህ ቡድን… ነፃ ያወጣል የሚባለውን የሕልም ጉዞ መብቃት አለበት። በተባበረ ትግል ያልተመራ ተቃውሞ መጨረሻው፣ ሁሉንም ነገር በገዢው ፓርቲ በጎ ፈቃድ የሚወሰን ነው የሚሆነው። ይህን በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በመጪው ምርጫ መታረም አለበት።
ሰንደቅ፡- የአረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣም ሰፊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ የፈለግነው ውጤት ላይ አያደርሰንም ብለዋል። ለዚህ መከራከሪያዎ የሚያነሱት ኀሳብ ምንድን ናቸው?
ዶ/ር መረራ፡- በግልፅ እየታየ ያለ ነገር ነው። ወደግራ፣ ወደቀኝ፣ ወደጎን፣ ወደላይ እየተሄደ ነው። ይህ የገመድ ጉተታ ፖለቲካም ኢሕአዴግ የልብ ልብ እየሰጠው ነው፤ በአላስፈላጊ መንገድም እንዲሄድ እያደረገው ነው፤ ራሳቸውንም ተቃዋሚዎቹን ገመድ ጉተታ ውስጥ ከቷቸዋል። ይህን የመሰለ የፖለቲካ ክፍተት ቀዳዳው ካልተሸፈነ ምንም አይነት ለውጥ ቢመጣ የትም መሄድ አይቻልም። ቀዳዳዎችን ደፍኖ ወደ አንድ መስመር መምጣት ከተቻለ መንግስትንም መለወጥ ይቻላል።
ዴሞክራሲ የሚባለው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው። ሀገራችን እንዴት ትመራ? ምን አይነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያስፈልገናል? የፖለቲካ መቻቻል የብሔር ብሔረሰቦች መብት? የፌደራሊዝም አይነት? ቁጭ ተብሎ መነጋገር ስትችል ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ማንኛውም አይነት ለውጥ ቢመጣ ወደተፈለገው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንደርስም። ለውጥ ቢከሰት የተለመደው የገመድ ጉተታ ፖለቲካ መከሰቱ አይቀሬ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የግብፅ የፀደይ አብዮት ነው። ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አወረዱ፤ ቢያንስ እስከ ማውረድ ተስማምተው ነበር። በዚህ መልኩ ከእኛ ይሻላሉ።
ከለውጡ በኋላ ግን እያየን ያለነው የሙባረክ ወታደሮች ናቸው፤ ሃገር እየገዙ ያለው። ይባስ ብለው ሙባረክን ነፃ አውጥተው ለለውጥ የተነሱ ኃይሎችን እየገደሉ፣ እያሰሩ ይገኛሉ። ለዚህ ምክንያቱ የለውጥ ኃይሉ ሙባረክን እስከማውረድ እንጂ ቀጣይ የግብፅ መንግስት እና ሕዝብ እንዴት መመራት እንዳለባቸው የደረሱበት ስምምነት አልነበረም። የለውጡ ኃይል ብሔራዊ መግባባት አልነበረውም። በተመሳሳይ መልኩ በዚህም ሀገር ተመሳሳይ ለውጥ ቢከሰት ኢሕአዴግን ከማውረድ በዘለለ የተደረሰ ብሔራዊ መግባባት ባለመኖሩ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ሊከስት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። እንደው ጠዋት እና ማታ አንድነት፣ አንድነት ስለተባለ ብቻ ቀውስ ማቆም አይቻልም። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል እንዳለባት አሁን ላይ ነው ምላሽ መስጠት ያለባቸው፣ አሁን ላይ ነው መግባባት መተባበር የሚያስፈልገው። ቢያንስ ምን አይነት የፖለቲካ ስርዓት ያስፈልጋል? ምን አይነት ፌደራሊዝም ያስፈልጋል? የሁሉም አስተዋፅኦ ምን መሆን አለበት? ለዚህም ነው ኢሕአዴግ ተገፍቶ እንኳን ከስልጣን ቢወርድ ይህን ታሪካዊ ፈተና እስካላለፍን ድረስ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር አንችልም የሚለውን መናገር እፈልጋለሁ። ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ለውጥ ውስጥ ያሉ ኃይሎችም እንዲረዱኝ የምፈልገው ይህንኑ እውነት ነው።
እንደተባለው አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ከዚህ ቡድን ጋር፣ ከዛ ቡድን ጋር አልሰራም አሉ ነው የተባለው። ከመስራት ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም። ሌላው አማራጫቸው ኢትዮጵያን ማጥፋት ብቻ ነው። እድልም ቢገጥማቸው እና ወደስልጣን ቢጠጉ ኢትዮጵያን ቢያጠፉ እንጂ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተባብረው በመሀል መንገድ ላይ ካልተገናኙ በስተቀር ኢትዮጵያን የትም አይወስዷትም። ለምሳሌ ከእኛ አይነት የፖለቲካ ኃይል ጋር ካልሰሩ፣ ከነፃ አውጪ ድርጅቶች ጋር ምን ሊሆኑ ነው? ከኦነግ፣ ከኦብነግ፣ ከጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባሮች ጋር ምን ሊያደርጉ ነው? ስለዚህም መሬት ላይ ያለውን የኃይል አሰላለፍ ምንድን ነው ብሎ መፈተሸ ተገቢ ነው የሚሆነው። ከዚህ ውጪ ለመብታቸው የሚታገሉትን ጡረታ ለማስወጣት ከሆነ መጀመሪያ ጉልበቱ እንዳላቸው ማረጋገጥ ነው። ጉልበት እንኳን ቢኖራቸው ደርግ የኤርትራን ጥያቄ ገፍቶ ገፍቶ አሁን ወደላበት ደረጃ እንዳደረሰው ሁሉ፤ እነዚህም የቀረችውን ኢትዮጵያ ገፍተው ለሁላችን የማትሆነውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ነገር ያላቸው አይመስለኝም። ለዚህም ነው የመተባበር፣ ሰጥቶ የመቀበል፣ የመቻቻል ፖለቲካ ውስጥ መግባት ካልተቻለ ቢያንስ ቢያንስ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን አናገኛትም። ምን አልባትም ከዚህ የበለጠ አደጋ ሊመጣ ይችላል። ኢትዮጵያን የሚበታትን አደጋም ሊፈጠር ይችላል።
Dr merera gudina Book
ሰንደቅ፡- በመፅሐፍዎ መደምደሚያ ሶስት ምክረ ኀሳብና ወቀሳ አስቀምጠዋል። ከእነዚህ ውስጥ “የትግራይ ሊሂቃን ስልጣን ወይም ሞት የሙጥኝ” ብለዋል የሚለው አንዱ ነው። ለዚህ አገላለፅዖ ማሳያው ምንድን ነው?
ዶ/ር መረራ፡- በግልፅ ነው የሚታየው። የኢትዮጵያን ዋና የስልጣን መዘውር የያዙት እነሱ ናቸው። በየትኛውም ሁኔታ ብትወስደው በበላይነት እነሱ ናቸው የሚመሩት።
ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያን መንግስት የሚመራው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። በዚህ ምክር ቤት ውስጥ እርስዎ ከሚሏቸው የትግራይ ሊሂቃን ከሶስት አይበልጡም። ከዚህ አንፃር ድምዳሜዎትን እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር መረራ፡- ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ ቁልፍ ስልጣንም ያላቸው፣ የመወሰንም ስልጣን ያላቸው ተቋማቱንም የሚያንቀሳቅሱት የሚያስወስኑትም በዋናነት ከትግራይ የመጡ ሊሂቃን ናቸው ለማለት ነው።
ሰንደቅ፡- የአማራው ሊሂቃን አሁንም ድረስ “ከበላይነት አስተሳሰባቸው መላቀቅ አልቻሉም” ብለዋል። ከአማራው ሕዝብ የወጡ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በዚህ አገላለጽዎ እንዴት ያስተናግዷቸዋል?
ዶ/ር መረራ፡- የአማራ ሕዝብ ትላንትም ዛሬም ሲጨቆን አውቃለሁ። እዚህ ላይ ጠብ የለኝም። ዋናው ጉዳይ እኔ ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ የአማራ ሊሂቃን የበላይነት አስተሳሰቡ አለቀቀውም። ከሌሎች ኃይሎች ጋር ብሔራዊ መግባባት ፈጥሮ እናንተም እንዲህ ሁኑ እኛም መሐል መንገድ ላይ እንመጣለን ብሎ በጋራ ለመስራት እና ልዩነቶችን መሃከል ላይ አድርሶ የመታገል ፍላጎት አላይባቸውም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በጎሳ የተደራጁ በምን የተደራጁ ቡድኖች ጋር አንሰራም የሚለው የአማራው ሊሂቃን አስተሳሰብ፣ ከማን ጋር ሊሰሩ ነው? ስለዚህም የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ተቀብሎ በጋራ መስራት ነው የሚያስፈልገው። እኔ በግሌ ሂሳብ የማወራረድ ፖለቲካ አልፈልግም። ሆኖም ግን አንድ የተወሰነ ማሕበረሰብ ተበድያለሁ ሲል አልተበደልክም የሚል ድርቅ ያለ መከራከሪያ ከማንሳት ቢያንስ ወደፊት ማንም የማይበደልበት ሀገር እንግባ ማለት የተሻለ ነው የሚሆነው። አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር መስራት ነው የሚጠበቅባቸው።
ሰንደቅ፡- የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ውስጥ ያሉ የአማራ ሊሂቃን የአማራ ሕዝብ እንደማንም የተጨቆነ፣ ኋላ የቀረ ሕዝብ መሆኑን ተረድተው ከሌሎች ብሔሮች ጋር ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት እየታገሉ እንደሚገኙ የድርጅታቸውም ሰነድ ሆነ ሊሂቃኑ በአደባባይ የሚናገሩት ነው። የአማራ የበላይነት መጠበቅ አለበት ሲሉም አይደመጡም። ከዚህ አንፃር ድምዳሜዎ ሁሉኑም የአማራ ሊሂቃን ማጠቃለሉን እንዴት ያዩታል? ብአዴን እየተጠቀመ ያለውን የፖለቲካ መጨወቻ ሜዳስ (political space) እንዴት ይገልጽታል?
ዶ/ር መረራ፡- ብአዴን የሚሰራው በዚህች ሀገር ውስጥ የበለጠ ችግር የሚፈጥር ነው። ምክንያቱም የሚያስፈጽሙት የኢሕአዴግ ፖሊሲዎችን ነው።
ሰንደቅ፡- ኢሕአዴግ ከመሰረቱት ፓርቲዎች አንዱ ብአዴን ነው። ስለዚህም ራሱ የተሳተፈበትን ፖሊሲ ማስፈጸሙ እንዴት ጉዳት ይሆናል?
ዶ/ር መረራ፡- ብአዴን ትንሽ ከኦህዴድ ይሻል ይሆናል እንጂ የተለየ ሚና የላቸውም። ከዚህ ውጪ የአንድ መንግስት አስፈፃሚዎች ናቸው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከዚህ የዘለለ ሚና የላቸውም።
ሰንደቅ፡- እርስዎ ካስቀመጡት መደምደሚያ መነሻነት ወስደን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጦች አሉ። በማሕበራዊም በፖለቲካውም አንፃራዊ ለውጦች አሉ። በብቸኛ መንግስትነት ያስቀመጡዋቸው “የትግራይ ሊሂቃን” እነዚህን ተግባሮች በዚህች ሀገር ውስጥ መፈጸማቸው ከምን መነሻ የመጣ ነው? በእርስዎ አረዳድ የትግራይ ሊሂቃን በኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ ተልዕኮ ወይም ራዕይ አላቸው ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር መረራ፡- ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ እነዚህ ኃይሎች በሀገሪቷ ውስጥ ብሔራዊ መግባባት ካልፈጠሩ፣ ሀገሪቷን ወደ ብሔራዊ ዕርቅ ካልመሩ፣ ሀገሪቷን ወደ ብሔራዊ ስምምነት ካልመሩ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሩህ ነው የሚል ግምት የለኝም።
ሰንደቅ፡- ገዢው ፓርቲ ብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ሲነሳ የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ከማስታረቅ ጋር መያያዝ የለበትም። በፖለቲካ መስመርም የተጣላ የለም የሚል መከራከሪያ ያነሳል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዶ/ር መረራ፡- እንደዚህ እያሉን ኢሕአዴግ እንዲሁም በበላይነት የሚመራው ህወሓት ተጣልተው አገኘናቸው። ለምሳሌ ሕወሃት ብትወስድ አንዱን ጎኑ በልቶ ነው ስልጣን ላይ ያለው፣ የቆየው። እነአቶ ተወልደ የመለስ ሁለተኛ ሰው ነበሩ። አቶ ስዬ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ነበር። አቶ ገብሩ አስራት የትግራይ መስተዳድር ፕሬዝደንት ነበረ። ከዚህ አንፃር ግማሽ ጎኑን በልቶ ሕወሃት ስልጣን ላይ የቆየው። ብሔራዊ ርዕቅ ለራሱም ለኢሕአዴግ ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ኢሕአዴግ ከጫካ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ድረስ ያመጡ ሰዎች ናቸው። አሁን ከሚታዩት ባለስልጣናት የበለጠ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ስለዚህም የተጣለ የለም የሚሉት ቀልድ ነው። ቀልዳቸውን መቀጠል ይችላሉ።
በድርጅቶች ደረጃ ከወሰድነው ላለፉት አርባ አመታት የተቋሰሉ ድርጅቶች ያለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለነው። በማሕበረሰብ ደረጃም ከወሰድነው ብዙ ቅራኔዎች እንዳሉም እናውቃለን። ስለዚህም የተጣለ የለም እየተባለ ግጭት በአፍጫችን ላይ ጠዋት እና ማታ እየፈነዳ ነው ያለው። ለምሳሌ በጉራፈርዳ፣ በመዠንገር፣ በጋምቤላ፣ በሱማሌ እና በኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች ተነስተዋል። ሰዎችም ተፈናቅለዋል። ነገር ግን ጉዳዩ ተዳፍኗል።
ሰንደቅ፡- የእርስዎ መከራከሪያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስካሁን ካለፍናቸው መንግስታት ለኦሮሚያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመዘርጋትና ተጠቃሚ በማድረግ አሁን ያለው መንግስት የተሻለ መሆኑን አንስተው የሚከራከሩ ምሁራን አሉ። እርስዎ ከዚህ አንፃር እንዴት ነው የሚመለከቱት?
ዶ/ር መረራ፡- የምትላቸው ወገኖች ምን ያህል ፖለቲካ ገብቶአቸው ይሁን አልገባቸው አላውቅም። ለምሳሌ ደርግ እና ኢሕአዴግን እንውሰድ። በኢትዮጵያ ደረጃ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ደርግ ከሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎች የባሳ ሊሆን ይችላል፤ ለኦሮሚያ ግን አልነበረም። እኔን ብትወስደኝ በደርግ ሰባት አመታት ታስሬያለሁ። ከእኔ ጋር መኢሶን ውስጥ የተገደሉም አሉ። በተወሰነ ደረጃ በኦነግም ውስጥ የነበሩ የተገደሉ አሉ። ግን በሰፊው ሲታይ በደርግ ጊዜ ከነበረው ይልቅ ኦሮሚያ ውስጥ አሁን ያለው ቀውስ ይበዛል። አሁን ያለው እስር ይበዛል። እስር ቤት ብትሄድ የእስር ቤት ቋንቋ ኦሮሚፋ ነው የሚባለው ለዚህም ነው።
በተለይ በስፋት ከወሰድነው ደርግ እና ኢሕአዴግን አታወዳድርም። በዚህ ዘመን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደል አታመዛዝነውም። በኢትዮጵያ ደረጃ ቀይ ሽብር ከወሰድክ የደርግ በደል ወንጀል አፈና ይበዛል። የበለጠም ነው። በኦሮሞ ደረጃ ግን ሁለቱን ስርዓቶች ስታወዳድረው በሚታሰረውና በሚገደለው ብዛትና በደረሰው መፈናቀል እና ሌሎችም ነገሮችን ስታይ የኢሕአዴግ ይብሳል የሚል እምነት አለኝ። ደርግ ምንም ይሁን ምንም የኢትዮጵያ ንቅናቄ ስጦታም ቢሆን መሬት ላራሹ በአብዛኛው ኦሮሞና የተቀረውን የደቡብ ሕዝብን ከጭሰኛነት አውጥቶታል፣ ጠቅሞታልም። በሌላ በኩል ደርግ ሁላችንንም ገድሏል። ወንድሜንም ገድሏል።
ሰንደቅ፡- ካስቀመጡት መከራከሪያ በመነሳት፣ ኦህዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ የሰራው ስራ የለም ብሎ መደምደም ይቻላል?
ዶ/ር መረራ፡- እኔም ሆንክ በሌሎች የኦሮሞ ሙሁራን ኦህዴድ የሚታወቀው፣ የኦሮሞን ሕዝብ በማዘረፉ፣ ሕዝቡን በማሳሰሩ፣ ሃብት በማስቀማቱ ነው። አሉታዊ በሆነ መልኩ ነው የሚታወቀው። የኦሮሞን ልጆች መብት በማስጠበቅና በማጎናጸፍ አይታወቅም። ይህን ስልህ በቀድሞ የኦህዴድ ባለስልጣናት ጭምር የተረጋገጠ ነው። በተለይ ከፓርቲው ከተለዩ በኋላ የሚሰጡት ለኦሮሞ ሕዝብ ውክልና እንዳልተሳካለት ነው።
ሰንደቅ፡- በኦህዴድ ፖለቲካ አመራር ክልሉ በቋንቋው እንዲጠቀም፣ የፍትህ ስርዓቱንም በቋንቋው እንዲዳኝ፣ ክልላዊ መንግስት እንዲኖረው፣ መሬቱን የማስተዳደር ስልጣን፣ መሰረተ ልማቶችን የመገንባቱ ስራዎች በመልካም ጎኑ ሊወሰድ አይችልም?
ዶ/ር መረራ፡- ዋናው ጉዳይ የኦሮሞን መብት ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ የኦሮሞ ኃይሎች እይታቸው ነው ችግሩ። የኦሮሞ ሕዝብ እነዚህ ኃይሎችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፈጥረውልኛል ብሎ ይመለከታቸዋል ወይ? መብትና ክብሬን እያስጠበቁ ነው ብሎ ይመለከታል ወይ? ሕዝብ ይህን መመስከር ካልቻለ ዋጋ የለውም። በቃለ መሃላ ብቻ እናደርጋለን ማለት የትም አያደርስም። ውሃም አይቋጥርም። እነሃሰን አሊ፣ አልማዝ መኮ፣ ጁነዲን ሳዶ፣ እንዲሁም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ ኦህዴድ የሚለውን የሚተገብር ሳይሆን ሕዝቡን የሚያስጠቃ ነው ብለዋል። ሕዝቡን ከመሬቱ እያፈናቀለው ነው። ሃብቱን እያዘረፈው ነው። በቀድሞ የኦህዴድ አመራሮችም በሕዝቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ይህ ነው። ስለዚህም ኦህዴድ የሚለው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሳይሆን የሞግዚት አስተዳደር ነው በኦሮሚያ ያለው። ችግሩ እዚህ ላይ ነው።
ሰንደቅ፡- በመፅሐፍዎ ላይ ኦነግን በተመለከተ ካልተነካካን በስተቀር ለሶስተኛ ወገን ብለን አንጋጭም ብለዋል። ይህ ምን ማለት ነው?
ዶ/ር መረራ፡- ኦነግን በተመለከተ እኛ የተለየ አቋም እንዳለን ይታወቃል። እነሱም ያውቃሉ። ሆኖም ግን የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱ እስከሚጠበቅለት ድረስ ለምን በዚያ፣ በዚህ መስመር ሄደው ታገሉ ብለን የምናገልበት ሁኔታ የለም። እነሱን ወደመግፋት መጣላት ውስጥ አንገባም ለማለት ነው። ዋናው ጉዳይ የኦሮሞ ሕዝብ ለነፃነቱ ለክብሩ እየታገለ ነው የሚገኘው። የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች ደግሞ በተለያየ ስትራቴጂ ፖሊሲ እየታገሉ ነው የሚገኙት። ስለዚህ በተቻለ መጠን የእኛ ድርጅት ካልተነካ እነሱ እኛ ላይ ድንጋይ ካልወረወሩ ከመሬት ተነስተን ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን ስላሉ ብቻ አንጋጭም። እንደስትራቴጂም አንከተለውም።
ሰንደቅ፡- በአንፃሩ ግን በመጽሐፍዎ ላይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እንደኦህዴድ ለሌሎች ኃይሎች የኃይል ሚዛን መጠበቂያ መሆን የለበትም ብለዋል። የዚህስ መነሻ አመለካከቶ ምንድን ነው?
ዶ/ር መረራ፡- ደጋግሜ እንደምለው የኦህዴድ ባለስልጣናት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ከማስከበር ወደ ማስጠቃት፣ ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንኳን በመቶ ሺዎች የሚሆኑ የኦሮሞ ልጆች ተፈናቅለዋል። በሺዎች ታስረዋል። ስለዚህም ነገ ከነገ ወዲያ አይጠቅማችሁም። የተወለዳችሁት ከኦሮሞ ልጆች ነው። የሚቀብራችሁ የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ያደጋችሁት የኦሮሞን ሕዝብ ወተት እየጠጣችሁ ነው። ሕዝባችሁን ለጊዜያዊ ጥቅም ብላችሁ አትጉዱ። እነዚህን ሌሎችን ለመፈጸም መሳሪያ አትሁኑ ለማለት ፈልጌ ነው።
ሰንደቅ፡- አሁን ካለው መንግስት በጠንካራ ጎን የሚያነሱት ይኖርዎት ይሆን?
ዶ/ር መረራ፡- ሲመጡ የገቡት ቃል ኪዳን ጥሩ ነበር። የብሔረሰቦችን እኩልነት እናመጣለን። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናመጣለን። የእዝ ኢኮኖሚን አስወግደን በተሻለ መንገድ የገበያ ስርዓት እንድንመራ እናደርጋለን ያሏቸው ቃል ኪዳኖች በጣም ጥሩ ነበሩ። በኋላ ላይ የሄዱበት መስመር ነው ከኢሕአዴግ የለያየን። ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ደጋፊው ነበርኩ። በመጸሐፌም አስፍሬዋለሁ። የተለያየነው የሽግግር መንግስት ምስረታ ላይ በተፈጸመው ቲያትር ነው። ያለፉት መንግስታት ሲሰሩት የነበረውን ድራማ አይናችን እያየ ደገመው። ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ የትም አይደርስም የሚል መደምደሚያ ላይ የደረስኩት ለዚህ ነው።
ቢያንስ ቢያንስ ግን ደርግን ስንታገል ለነበርነው ኃይሎች ደርግን ማስወገዳቸው በየትኛውም ሚዛን ትልቅ ድል ነው። ግን ደርግ የሰራውን ስህተት በቪዲዮ እያየ እሱኑ መድገሙ ትልቅ ወንጀል ነው። ይህን ስህተት ካላረመ ከደርግ የተሻለ የታሪክ ስፍራ ይኖረዋል የሚል ግምት ለመስጠት ያስቸግራል።

No comments:

Post a Comment