Wednesday, May 7, 2014

ዛሬ 29/08/2006 ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ጋዜጠኞች እና የዞን9 ጦማሪያን ለግንቦት9/2006 ተቀጠሩ፡፡ May7,2014


ዞን9 ዜና ሚያዚያ 29/2006
ሚያዚያ17 እና ሚያዚያ 18 2006 በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት 3 የህትመት ሚዲያ ጋዜጠኞች እና 6 ‹‹ዞን9››ተብሎ በሚጠራው የጦማር መድረክላይ ይጦምሩ የነበሩ ጦማሪያን መካከል 3ቱ የህትመት ጋዜጠኞች እና 3ቱ ጦማሪያን ዛሬ 29/08/2006 ፍ/ቤት ቀረቡ፡፡
ችሎቱ ይውላል ተብሎ የነበረው ጠዋት 4፡00 ሠዓት ላይ ቢሆንም ያለምንም ምክኒያት ለ8፡00 ሠዓት የተዘዋወረ ሲሆን፤ከሠዓት በኋላ ላይ ልክ ችሎቱ ሲከፈት ቀድመው የገቡት በአንደኛው መዝገብ ላይ ያሉት ናትናኤል ፈለቀ፣ኤዶም ካሣዬ እና አጥናፍ ብርሃኔ ናቸው፡፡
ችሎቱ ላይ ለመታደም የመጣው ህዝብ ለመግባት ሙከራ ሲያደርግ በታጠቁ ፌደራሎች እንዳይገባ ተከልክሎ ችሎቱ በዝግ ተካሂዷል፡፡በመጀመያው የፍርድ ሂደት ላይ ከቀረቡት መሐከል ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፍ ብርሃኔ የዞን9 ጦማሪያን ሲሆኑ ኤዶም ካሣዬ ደሞ ጋዜጠኛ ናት፡፡
ቅድሚያ ችሎት የቀረቡት 2 ጦማሪያን እና አንድ ጋዜጠኛ ሲወጡ ሁለተኛው መዝገብ ላይ ያሉት፤ዘላለም ክብረት(የዞን9 ጦማሪ)፣ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ(ጋዜጠኞች) ሊገቡ ችለዋል፡፡እነዚህ የችሎት ቆይታቸውን ጨርሠው ሲወጡ ፎቶ ሊያነሣቸው የሞከረ አንድ ጋዜጠኛን ፌደራሎች ከእስረኞቹ ጋር አከታትለው እየደበደቡ እንደወሠዱት በቦታው የነበሩ የዞን9 ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የፍርድ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ቃላቸውን ውጪ ቆመው ለነበሩ ጋዜጠኞች፣ታዛቢ የውጪ ዜጎች እና በቦታው ለነበሩ ታዳሚያን እና ቤተሠቦች ስለ ፍርድ ሂደቱ የተከሣሾቹ ጠበቃ ያብራሩ ሲሆን የክሣቸው ይዘት በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡-
‹‹ውጪ ሃገር ድረስ ሄደው ስልጠና በመውሠድ የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡››
ችሎቱ በስተመጨረሻ አቃቤ ህግ ‹‹ያልተሟሉ መዝገቦች እስኪሟሉ፣እና የገዟቸው ኮምፒውተሮች አሉና እነሱ እስኪቀርቡ››ባለው መሠረት ለግንቦት 9/2006 ሌላ ቀጠሮ ተሠጥቷቸው የፍርድ ሂደቱ ተጠናቋል፡፡
ዞን9 ያነጋገራቸው ግለሠቦች በበኩላቸው ‹‹ዓለም ሠለጠነች በተባለበት 21ኛው ክፍለ ዘመን መጦመር ወንጀል ሆኖ ሲያሳስር እጅጉን ይቆጫል ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment