Monday, March 17, 2014

የቁልቁለት መንገድ! – ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ



… በማስመሰል ታጥሮ መሆን በጠፋበት
ምን አገባኝ የሚል በተከማቸበት
የባይተዋር መንፈስ ከሞላ ባገሩ
ዘመኑን ማወቂያ ይሄ ነው ሚስጥሩ
ይሄን ጊዜ ጠርጥር እንደጠፋ ዘሩ፡፡                                          
(ገጣሚ ደምሰው መርሻ/ያልታተመ)

አዎን፣ ገጣሚ ደምሰው እንዳለው እኔም በዚህ ዘመን “ዘሩ እንደጠፋ” አሊያም ሊጠፋ እንደተቃረበ እጠረጥራለሁ፡፡

ስለምን? ቢሉ …በኢትዮጵያችን ለህሊናው፣ ለሕዝብና ለሀገሩ የሚቆረቆር፣ የእውነት ተሟጋችና የሞራል ልዕልናን የተቀዳጀ ሙሉ ሰው ፈልጎ ማግኘት እጅግ አተካች ሆኗልና፡፡ የግል ጥቅም አሳዳጅ፣ አፋሽ-አጎንባሽ በሞላበት፣ እንደ ቴዎድሮስ ለሀገር ቤዛ መሆን፤ እንደ ግርማሜዎቹ እና ወርቅነህ የራስን ምቾት ወዲያ ጥሎ በጠገበ ሆድ    ከወገን ጋር መራብና ከጎኑ መቆም፤ እንደ አቶ ሽፈራው ደሳለኝ አስፈሪ ሞት ከከበበው ሸለቆ ውስጥ በህይወት ለመውጣት ሲባል የጠላትን ጫማ ከመላስና ያላመኑበትን ተናግሮ ምህረት ከመጠየቅ ይልቅ በድፍረት ሞትን ፊት ለፊት መጋፈጥ ወይም ግንባርን ለአረር መስጠት እንደ ተረታ-ተረት ከተቆጠረ ዘመናት አልፏል (አቶ ሽፈራው ደሳለኝ ማን ናቸው? ለሚለኝ አንባቢዬ ‹‹የታኀሣሡ ግርግር እና መዘዙ›› የተሰኘውን የብርሃኑ አስረስ መጽሐፍ ገፅ 302ን እንዲያነብ እጋብዘዋለሁ) አሊያም ደግሞ የሰው ዘር በመሆን ብቻ የሚገኘውን የሞራል ልዕልና ከትውልድና ሀገር ጥቅም አኳያ ለማጠየቅ በዚህ አውድ ለማነሳው ተጠየቅ በአንፅሮ ለማፍታታት ይጠቅመኝ ዘንድ እኔው ራሴ እዚሁ ጠቅሼው አልፋለሁ፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጊዜ የድጋፍ ንግግር አድርጋችኋል በማለት በመንግስት ተይዘው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት አንዱ የሆኑት…›› ብለው ከአቶ ሽፈራው ደሳለኝ ጋር ከአስተዋወቁን በኋላ እንዲህ በማለት ትርክታቸውን ይቀጥላሉ፡- ‹‹…አቶ ሽፈራው ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ተልከው ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ዳኛው ‹ሠርተሃል ለተባለው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ፣ አይደለህም?› ይላቸዋል፡፡ ‹የቱን ወንጀል?› ሲሉ አቶ ሽፈራው ዳኛውን ይጠይቃሉ፡፡ ዳኛው አቶ ሽፈራው ሠርተዋል የተባለውን የወንጀል ቃል ሊናገሩት አልወደዱም አልደፈሩምምና ‹አንተ የሠራኸውን?› ብለው ጠየቁ፡፡ አቶ ሽፈራው ‹እስቲ ወንጀል የተባለው ይነበብልኝ› ብለው አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄን ጊዜ ዳኛው ሳይወዱ ‹ይህን ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን፣ አወረደልን ማለትህን፤ …ለዚህ ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?› ይሏቸዋል፡፡ ‹የለም ተስተካክሎ ይጻፍልኝና እምነት ክህደቴን ልናገር› ይላሉ፡፡ ‹የለም በዚህ ላይ ጥፋተኛ ነኝ በል› ይሏቸዋል፡፡ ‹ትክክለኛ ቃሌ ይጻፍና ነው እንጂ እንዲሁ ጥፋተኛ ነኝ፤ አይደለሁም፤ አልልም› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹እሺ ምን ተብሎ ይስተካከል› ሲሏቸው፤ ‹ይህን የበሰበሰ የተጠረማመሰ አሮጌ ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን ነው ያልኩት› ሲሉ ዳኞቹ የተባለውን አልሰማንም ለማለት ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው ተደበቁ፡፡››

በዚህ ዘመን ራሳቸውን ጠረጴዛ ስር አግብተው እንደ ሰጎን አንገታቸውን ቀብረው በፍርሃት የሚኖሩ አድር፣ እበላ-ባይ፣ ፈሪ ሰዎች የአቶ ሽፈራውን ባመኑበት መቆም እንደ አጎል ጀብደኝነትና ሞኝነት ቢቆጥሩት አስገራሚ አይሆንም፡፡ የሆነው ሆኖ እንደ ብልህነት አሊያም ብልጥነት ተደርጎ የሚወሰደውን የአድርባይነት ‹‹ስልት›› ለማሳየት አንዲት ሀገርኛ ምሳሌ እዚህ ጋ ለንፅፅር ላቅርብና እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ለራሴ ጽሑፍ ‹‹F›› ከመስጠቴ በፊት ወደ አጀንዳዬ ልዝለቅ፡፡

ታሪኩ ዝናው በስፋት የናኘ ሽፍታ የመሸገበትን (ግዛቱ ያደረገ) ጥቅጥቅ ያለ ጫካ አቋርጦ ስለሚያልፍ መንገደኛ ገጠመኝ ነው፡፡ መንገደኛው ለሰዓታት ከተጓዘ በኋላ ድንገት ሽፍታው እጅ ይወድቅና ስንቅ የቋጠረበትን ስልቻ ጨምሮ ከላይ እስከታች ይበረበራል፤ ሆኖም ሰባራ ሳንቲም ሊያገኝበት ባለመቻሉ ከመጠን በላይ የተበሳጨው አያ ሽፍታ ሆዬ ንዴቱን ለማብረድ ሲል ‹‹ውዳሴ ዜማ አቅርብልኝ!›› በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጠዋል፤ በፍርሃት ነፍሱ እጉሮሮው የተወተፈችበት መንገደኛም ተንፈስ ብሎ ለመረጋጋት እየሞከረ እንዲህ ሲል አቀነቀነለት ይባላል፡-

‹‹አይኑ የተኳለ ጠላት የሚጋረፍ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ 2

ጠብ-መንጃ ገስጋሽ ጉብታ ተሻግሮ
ከዘብጥ የሚናደፍ
እንደሚካኤል ነህ ጠላትህም አይተርፍ!››

እነሆም የሀገሬ ምድር እንዲህ ባሉ ሀሞተ-ቢስ አወዳሾችና አስመሳዮች ተጥለቅልቃ እጆቿን ወደ ሰማይ ከዘረጋች (ሱባኤ ለመግባት) ሰነበተች፡፡ በርግጥም ከብዙሀኑ በተሻለ ማንሰላሰል ይሳናቸዋል ተብለው የማይታሰቡ ‹‹ምሁራን››ም ሆኑ ‹‹መንፈሳዊ››ነታቸው የበዛ የኃይማኖት መሪዎች በግል ጥቅመኝነት ታውረው ከስርዓቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን የጭቆና አገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም በሀሰት መስካሪነት የቅጥፈት ምላሳቸውን ሲያንበለብሉ መስማት ‹እግዚኦ› የሚያስብል አስደንጋጭ መናፍቅነት መሆኑ ቀርቶ እንደ ተራ ነጋዴ ንግግር፣ ተራ የዕለት ተዕለት አጋጣሚ ከሆነ ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ‹‹መንፈሳዊያን›› አባቶች በተከበረው ቤተ-መቅደስ ምኩራብ ላይ ከመእምናኑ ፊት ለፊት ቆመው ቃየልን ‹‹አቤል››፣ በርባንን ‹‹መሲህ›› በማለት ሲሰብኩም ለአመል እንኳ ድንቅፍ አያደርጋቸውም፤ ከግላዊ ጥቅማቸው አሻግረው የግፉአንን የስቃይ እሮሮ ማድመጥም ሆነ ለሌላው ማሳወቅ ጭራሹንም አይሞክሩትም፡፡ ‹‹ምሁራን›› ተብዬዎቹም አርቲስት ሰለሞን ተካልኝ ‹‹ውበት ከቅንድቡ የሚፈስ›› እንዲል፤ ‹አይኑ የተኳለ› እያሉ በሕፃናት ደም ሳይቀር የጨቀየውን ኢህአዴግ መራሹን መንግስት እንዴት እንዴት ‹ብፁእ› አድርገው የውዳሴ ከበሮ ሲመቱለት እንደሚያድሩ እዚህ ጋ ዘርዝሮ ለማቅረብ ማሰብ አባይን በጭልፋ አጋብቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ያለ ዕብደት ያስቆጥራል፡፡

ወጣም ወረደ እንዲህ አይነቱ የሞራል ዝቅጠት በትላንት ወይም በዛሬ የእድሜ ገደብ የሚለካ አለመሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፤ ምክንያቱም በነገሥታቱ የአገዛዝ ዘመን የጀመረና በጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅት እንደወረርሽኝ የተስፋፋ ስለመሆኑ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ‹‹ሀገር›› ለተሰኘ ማህተም መስዋዕት የሆኑትን አቡነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ታሪክ በታላቅ አክብሮት የሚዘክራቸውን ቀዳማይ አባቶችና እናቶችን ሳንዘነጋ ነው፡፡ እናም የሩቁን ትተን ከ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ወዲህ ያለውን እንኳ ብንመለከት ይህን መሰሉ ክስረት ዙሪያችንን ከቦ ሊውጠን የቀረው ስንዝር ታህል ርቀት ብቻ መሆኑን ለመረዳት የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁራን ትንታኔን ማገላበጥ አይጠይቅም፡፡ ያኔ ገና በለውጡ ማግስት ህወሓት እና ሻዕቢያ በአንድ አንቀልባ ካልታዘልን በሚሉበት የ‹‹ጫጉላ›› ዘመን፣ ከኤርትራ ምድር የወርቅ ጥርሳቸው ሳይቀር በጭካኔ ወልቆ ባዶ እጃቸውን የተባረሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በጉምቱው ምሁር ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ የተመራው አጣሪ ቡድን ‹‹ውሸት ነው! ይህ አይነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኤርትራ ይኖሩ
በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አልተፈፀመም!!›› በማለት አይኑን በጨው አጥቦ በድፍረት ሲያስተባብል፣ አንጀታችን እያረረ ‹‹ይሁና!›› ብለን በትዝብት ማለፋችን እውነት ቢሆንም፤ የዝምታችን ውስጠ-መልዕክት ያልገባው ፕሮፌሰሩ ግን ያረረው አንጀታችን ይበልጥ እርር ይል ዘንድ በተለመደው ቅጥፈቱ ታላቁ የዐድዋ ድል ባለቤትነትን ከሀገር ከፍታ፣ ቁልቁል ወደ ጎጥ ለማውረድ ያልፈነቀለው ቋጥኝ፣ ያልማሰው ስር አልነበረም (በነገራችን ላይ ህወሓት ዛሬም ከዐድዋ ድል ጀግኖች ጋር ጥቁር ደም እንደተቃባ በግላጭ የሚያመላክተው በዘንድሮው 118ኛው ክብረ በዓል ላይ የተስተዋለው አሳፋሪ ትእይንት ነው፡፡ ይኸውም በታሪካዊቷ ዐድዋ ከተማ በሚገኘው ሶሎዳ ተራራ ስር ‹ድሉን ለመዘከር› ከተሰቀሉት የእቴጌ ጣይቱ፣ የራስ አሉላ አባነጋ፣ የባልቻ አባነፍሶ እና የባሻ አውዓሎም ግዙፍ ምስሎች መሀል የተሸናፊው ሀገር ህዝብ ሳይቀር በድሉ ዕለት ሮማ በተሰኘው አደባባዩ ‹‹ቪቫ ምኒሊክ›› እያለ በታላቅ ጩኸት ያወደሰው የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ምስል አለመካተቱ ነው፡፡ …መቼም ይህ ለምን ሆነ? ብለን የክልሉን አስተዳዳሪ ጓድ አባይ ወልዱን ብንጠይቀው ‹‹በጦርነቱ ወቅት ምኒሊክ መሸሽ ጀምሮ ነበር›› የሚለውን ዝነኛ ህወሓታዊ ትርክት ገልብጦ፣ ‹‹በስራ መደራረብ በተፈጠረ ስህተት ነው›› ብሎ በክፍለ ዘመኑ ታላቅ ሽርደዳ አንጀታችንን ይበልጥ ድብን እንደሚያደርገው ቅንጣት ታህል አትጠራጠሩ)
ለማንኛውም እንደ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ያሉ በድሃው ሕዝብ ጥሪት የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዕድል ማግኘት የቻሉ በርካታ እበላ-ባይ ‹‹ምሁራን›› ስርዓቱ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚያምታታበትን ‹‹የሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት›› የፈረንጅ ጥናቶችን በጥራዝ-ነጠቅነት እያጣቀሱ ምክንያታዊ መስለው ሊያሳምኑን በከንቱ ብዙ ደክመዋል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሠራዊቱ ለባዕድ ሀገር ጥቅም ሲባል ሶማሊያን በወረረበት ወቅት አንዳንድ የዩንቨርስቲ መምህራን እና ‹‹የፖለቲካ ተንታኞች›› በመሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ ይሁነኝ ብለው ወደጎን ገፍተው አገዛዙ ቀን ከሌት ‹‹እመኑኝ!›› በሚል ጩኸት ያሰለቸንን ሰበብ፣ በጥናት እንደተረጋገጠ አስመስለው ለመተንተን ያደርጉት የነበረው እሽቅድምድም ሁሌም በሀዘን የምናስታውሰው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment