(ጦማሮች)ይህን የድሮ ዘመን ተረት ሳመጣ እስስት የምትባለዋን እንስሳ ስነ ተፈጥሮ፣ ተፈጥሮአዊ ምድቧን /ከየትኛው የእንስሳት ክፍል እንደምትመደብ/ ከአጥቢ ወይም ከሌላኛው እንደሆነ ለማጥናት እንዳልሆነ በቅድሚያ ልብ ይበሉልኝ. . .
ድሮ ድሮ በልጅነታችን ኳስሜዳ ወጥተን ከኳስ በኋላ ለኛ ብርቅዬ የሆነችውን እስስት ለማየት ብዙ ቀናትን ማድፈጥ ይጠበቅብናል፣ እንስሳይቱ እንዲሁ እንደዋዛ የምትገኝ ባለመሆኗ፣ ብትገኝም አብዛኛውን ጊዜ ካለችበት አካባቢ ጋር ስለምትመሳሰል ስትንቀሳቀስ ካልሆነ በስተቀር እሷነቷን ለማወቅ እጅግ በጣም አዳጋች ነው
እንደውም አንድ ቅዳሜ አስታውሳለሁ፣ በጠዋቱ ተጠራርተን ኳስ ልንጫወት እኛ ደጅ ላይ ተሰባስበናል. . .እንደወትሮው ሜዳ መረጣ ጀመርን፣ በነገራችን ላይ እኔ ያደኩበት አካባቢ ዙሪያውን በብዙ ሜዳ የተከበበ ነበር የአሁኑን አያድርገውና፣ ጉቶ-ሜዳ፣ አለሙ-ሜዳ፣ 24-ሜዳ፣ ሚፍትዬ-ሜዳ፣ አዴ-ሜዳ. . . ሌሎች የተቀሩትን የሰፈሬ ልጆች ያስታውሷቸው፣ እናም በምርጫ “ጉቶ-ሜዳ“ እንሂድ ተባብለን ወደዚያው አመራን፣ ሜዳው ስያሜውን ያገኘው በዙሪያው ካሉት እድሜ ጠገብ የባህር ዛፍ ትልልቅ ጥርብ ጉቶዎች ነው፣ እነዚህ ዛፎች እድሜ ጠገብ ከመሆናቸው ባሻገር አንዳንዶቹን ለሶስት ተያይዘን እንኳን ዙሪያ ደርዙን መሙላት አንችልም ነበር፣ ያንጊዜ ባህር ዛፎቹን ማን እንደቆረጣቸው ባናውቅም /አሁን አሁን ስገምት የ25 ቀበሌ አስተዳደር ይመስለኛል/ ከመሬት በግምት 1 ሜትር ከፍ ተብሎ በልክ የተቆረጡ ነበሩ፣ ከተቆረጡም በኋላ ከጎንና ጎን እንዲሁም ከአናታቸው ላይ ብዙ በማደግ ላይ ያሉ ቅርንጫፎች አቆጥቁጠዋል
እንደተለመደው የመሬቱ አቧራ በአፍና ባፍንጫችን እስኪወጣ ተራግጠን ተራግጠን ሲወጣልን እንረፍ ተባብለን እዚያው የነበርንበት ሜዳ ላይ ተጋድመን ስለቀጣዩ ጉዞአችን ማውራት ጀምረናል፣ አንደኛው አቃቂ ወንዝ ሄደን እንዋኝ ሲል፣ አንደኛው ደግሞ አይ እሱ እሩቅ ስለሆነ ካሮት አጠባ ወንዝ ሄደን ካሮት እንልቀም ይላል፣ እኔ ደግሞ አባሲዮን /የአሁኑ ኦሜድላ ስፖርት ክለብ ሜዳ/ ሄደን ኳስ እንይ እያልኩ. . . አንደኛው ጓደኛችን በእጁ ጭራሮ ይዞ የአንዱን ባህር ዛፍ ጉቶ እየደጋገመ ይደነቁላል፣ መጀመሪያ ቅጠሉ ላይ አረንጓዴ መስላ የታየችውን እንስሳ በያዘው ጭራሮ ሲወጋት በቅጽበት ተስፈንጥራ ወደጉቶው ዘለለች፣ ጉቶው ላይም የጉቶውን የቅርፊት መልክ ስትይዝበት ጮክ ብሎ ጠራን እስስት. . . እስስት. . . ሁላችንም ከተጋደምንበት ዘለን ተነሳን አንዳንዶቻችን የቱጋ እንዳለች እንኳን መለየት አልቻልንም ነበር፣ እስስቷ ራሷን ለመከላከል ጉቶው ቆንጥጣ ተጣብቃለች፣ መልኳ ሙሉ በሙሉ የጉቶውን ቅርፊት ይመስል ነበር፣ ነገር ግን በመጀመሪያ እንቅስቃሴዋን ያየው ጓደኛችን በደንብ ለይቷት ነበርና በሱ ጥቆማ እኛም ያለችበትን ቦታ በደንብ ስለለየነው ከኔና ጓደኞቼ ጥቃት ማምለጥ አልቻለችም
እንግዲህ ይህ ከሆነ ዛሬ 18 አመት አልፎታል፣ ያኔ በልጅነት ዘመን የዚህችን እንስሳ ባህሪ /ጠባይ/ ማወቄ እንዲሁም የቀደመውን የአባቶች አባባል ማገናዘቤ ስለዚህች እንስሳ ጥቂት እንዳስታውስና የዚህችን እንስሳ ባህሪ /ጠባይ/ የተላበሱ በዘመኔ ያሉ የሰው ልጆችን ባህሪ እንዳጤን አስገደደኝ፣ እስቲ ከተለመዱት አባባሎቻችን እንነሳ
ቀን እስኪያልፍ ያባቴ ባሪያ ይግዛኝ
ከልጅነት ጀምሮ በስፋት የምንሰማው አባባል ነው፣ በተለይም በሃገራችን ፖለቲካ ቅኝት ነገሩን ስናዋዛው ራስን ከጥቃት ለመጠበቅና ከሚመጣው መንግስታዊ /የገዢዎች/ ቁጣ ለመዳን ራሳችንን የምናጉርበት ምሽግ ነው፣ የሃገራችን የፖለቲካ ባህል ከድሮ ጀምሮ የገዢና ተገዢ፣ ሲከፋም ንጉስና የንጉስ ሎሌ በመሆን አልያም፣ አብዮተኛና ጸረ አብዮተኛ፣ እንዲሁም አሸባሪና ሽብርተኛ በማለት በፍረጃ ያለፈ /እያለፈ ያለ/ ዘመን በመሆኑና ነቃ /ቀና/ ብሎ ለጥያቄ አፉን የከፈተ ካለ የንጉስ ጠላት፣ ጸረ አብዮተኛ፣ ወይም በአሸባሪነት ፍርጃ መጠቃቱን እያሰበ ቀኑ እስኪያልፍለት ባባቱ ባሪያም ቢሆን ለመገዛት የወሰነ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ ግድ ሆኖአል፣ ስለዚህም ሲልኩት ወዴት. . . ሲጠሩት አቤት እያለ የጌቶቹን ትእዛዝ ብቻ በማክበር ከሞያው ውጪም ቢሆን፣ አመነም አላመነበትም ይፈጽም ዘንድ ግድ እንዳለበት የተቀበለ ማህበረሰብ ተፈጠረ
በእርግጥም ይህን ያዩ ገዢዎች የልብ ልብ ተሰምቷቸው ማህበረሰቡን በፍርሃት ድባብ ማነቆ ውስጥ በማስገባት የእለት ተእለት ኑሮውን እንኳ በቅጡ እንዳይኖር፣ የእለት ፍጆታውን ሳይቀር በእጃቸው በማስገባት ለመኖሩም ላለመኖሩም የሚፈቅዱት አሊያም፣ ነፍሱ በእጃቸው እንዳለችና ሲፈልጉ ሊገድሉት ከቀኑ ደግሞ ሊምሩት እንደሚችሉ እንዲያስብ ግድ ሆነ፣ ዜጋውም ዜግነቱን ትቶ ተገዢ እንደሆነ አምኖ ራሱን አሳልፎ ሰጠ
የገዢዎች መለዋወጥ በጠመንጃ /በሃይል/ ሆኖ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ ባህል ሆኖ፣ ሃይሉን አሳይቶ አልያም ገድሎና ማርኮ ለመጣ ሃይል ራስን አሳልፎ መስጠትና ከሃይሉ በታች መንበርከክን ባህሉ ያደረገ ህብረተሰብም የዘወትር አባባሉ “ቀን እስኪያልፍ. . .“ እየሆነ ለነፍሱ ባርነትንና ተገዢነትን፣ ለመንፈሱም ደካማነቱን ነግሮ፣ ቤቱን ራሱ ዘግቶ በገዢዎቹ ፈቃድ ብቻ መክፈት እንደሚችል የሚያስብ ደካማና ከንቱ የማህበረሰብ ክፍል እንዲፈጠር ሆነ
ካለው ተወለድ ወይ ካለው ተጠጋ
ኢኮኖሚያዊ ቀፈትን ለመሙላት አሊያም የእለት እንጀራን ለመጋገር ገዢዎችን በተለያዩ መንገዶች መጠጋት፣ ለሙያ ተገቢውን ክብር ሳይሰጡ ለካድሬ በማሸርገድ አልያም የገዛ ጓደኛን ብሎም የስራ ባልደረባን በማሳጣት /አሳልፎ በመስጠት/ ራስን ለማቆየት የሚደረግ የእለት ተእለት ፍትጊያ ውስጥ ራስን በመዝፈቅ የራስ ጥቅም እስካልተነካ ድረስ የሌሎች ሞትና ስቃይ የራስ ምታት ያህል የማይሰማው ይህ የኔ ትውልድ ራሱን በኢኮኖሚ ከበለጸገ ማህበረሰብ ውስጥ ካላገኘው በቀጥታ ራሱን በመሸቀጥ ያለ አንዳች ሃፍረት ያላቸውን /ገንዘብ ወይም ስልጣን/ ሰዎች በመታከክ ኢኮኖሚያዊ ስልቻውን ለመሙላት ይታትራል፣ በተለይም በሃገሪቱ አንጡራ ሃብት ብሎም የኋላ ተረከዙ እንደንቃቃት ተሰነጣጥቆ፣ እጆቹ እንደኮረት አሸዋ ሻክረው ከማረሻና ወደል በሬ ጋር ታግሎ፣ ከወዙና ከላቡ ተጠርጎ ተወስዶበትና ሳይማር ያስተማራቸውንና ነጻ ያልወጣውን ገበሬ አባታቸውን ከገዢዎች ጭቆናና ጫና ነጻ ያወጣሉ ተብለው ሲጠበቁ “ወይ ካለው ተጠጋን . . .“ ብሂል በማቀንቀን ለጊዜው በትረ ስልጣኑን ለጨበጠው ገዢ በማደግደግ ሙያቸው የሚጠይቀውን ነጻ መሆንን /በነጻ የማሰብን/ በነጻነት አገልግሎት የመስጠትን ክብር አሽቀንጥረው መስሎ አዳሪነትን እንዲሁም ምሁራዊ ግልሙትናን የሚለማመዱ አድር ባይ ልሂቃን ተብዬዎችን ያከማቸ ትውልድ ሆነ
ነጻነት በምሁራዊ ግልሙትና ከሚገኝ የአገልግሎት ክፍያ ከኢኮኖሚያዊ ዝቅጠት ራስን ብቻ ነጻ ማውጣት በሚል አጉል አስተሳሰብ ተጠፍንጎ አፍንጫው ስር ካለው እስትንፋስ ውጪ የሌላውን ህይወት እስትንፋስ የማያይ ከንቱ ምሁር ተፈጠረ፣ የተጣበቃቸው ገዢዎች አድርባይ ብለው አንቅረው እስኪተፉት አልያም በሙስናና በሌሎች ሰበባ ሰበቦች የከርቸሌ ሲሳይ እስኪያደርጉት የማይነቃ ብኩን ምሁር ሆነ፣ በቅርቡ የሰማነው የገዢዎች ንግግርም ይህንን የሚያሳይ ነበር፣ “የስርዓቱ ችግሮች ከሚባሉት አንደኛው ሙስና ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አድርባይነት“ እንደሆነ የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ያስታውሷል፣ ይህም ተብሎ እንኳ ያልነቃና የእስስቷን ጠባይ ወርሶ የባለጊዜዎች ጭን ላይ ተጣብቆ ቢደነቁሉት የማይሰማው ሆኖ “ከራስ በላይ ንፋስ“ እያለ ያላዝን ገባ
የፊደል ገበታን ዘልቄያለሁ የሚለውንና አራት፣ አምስት፣ አልያም ሰባት ዓመት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቆይቶ እንደወጣ ተስፈንጥሮ የተጣበቃቸውን አፈጮሌ በማየት በ`ከማን አንሼ ስሜት ጨዋ /በትምህርታቸው ያልገፉ/ አድር ባዮችም በየደረጃቸው በቀበሌና በክፍለ ከተሞች በመኮልኮል ለጊዜው ስልጣኑን በሃይል እያስጠበቀ ያለውን ገዢ አንድም በህይወት ለመቆየት አሊያም የነተበ ኪሳቸውን ለማጠርቃት ሲሉ የሙጥኝ ተጣብቀው ወገኖቻቸውን በማስጠቃት ይኖራሉ
ያባትህ ንብረት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ
ይህን ብሂል አዝሎ የሚዞረው ከሃገር የወጣው ዲያስፖራም ካለፉት ዘመናት የወረሳቸውንና እራሱም ያካበተውን እንደእስስት ተቀያያሪ ጠባይ ይዞ በሁለት መልክ እየተጫወተ የሚኖር ሆኖአል፣ ተሟልቶለት የወረቀትና የመኖሪያ ፈቃድ ጉዳይ በቶሎ ካለቀለት ከተቃዋሚው ማህበረሰብ ሌላ የሚፈልገው አንድም ነገር ባለመኖሩ ራሱን ወዲያው ለስርዓቱ ቅርበት ካላቸውና ባለበት የአውሮፓ አልያም አሜሪካ ሃገራት አካባቢ ካሉ የኤምባሲ የቅርብ ሰዎች ጋር መገናኘት ይጀምራል፣ ለወትሮው ወይም የምእራቡን አለም ምድር እንደረገጠ አልባሳቱ፣ የእጅ አንባሩ እንዲሁም ቤቱ በሙሉ በኢትዮጵያ ባንዲራ ያሸበርቃል፣ ውሎው ሁሉ ስለሃገራቸው በቁጭት ከሚያወሩ ሰዎች ጋር ነው፣ ስለሃገሩ ሲያወራ ውሎ ቢያድር የማይደክመው ነው፣ ሲውል ሲያድር ወይም ሲሳካ በቅድሚያ የሚወልቀው እጁ ላይ ያጠለቀው ባለባንዲራው አንባር ነው፣ ሲቀጥልም ባለባንዲራ ቲሸርቶች /ጃኬቶች/ መልበስ ያቆማል፣ ከዚያም ሰልፎችና ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ምክንያቶች ይደረደራሉ፣ ወይም እሱ መምጣት ስለማይችል ለሚመጡት /በሱ እምነት/ ለአዳዲሶቹ ስደተኞች ትራንስፖርትና ለሌሎች ወጪዎች ስሙ ሳይጠቀስ ገንዘብ እንደሚደጉም ቃል ይገባል፣ ደፈር ብሎ ከመጣም ኮፍያና እስካርፍ አይለየውም
ከቆይታ በኋላ አልያም ከአንድ ጊዜ ሃገር ቤት ደርሶ መልስ በኋላ ከስርዓቱ የቅርብ ሰዎች ጋር በስውርም በግልጽም መገናኘት ይጀምርና፣ ምነው ሲሉት “ፍቅር ያሸንፋል“ የሚለውን የቴዲ አፍሮን Featuring ይነግራችኋል፣ በእርግጥም ፍቅር ያሸንፋል፣ ይህን ሲላችሁ ግን ጠርጠሩት ወይ መሬት ተመርቶአል አልያም 40/60 ተመዝግቦ እየጠበቀ ነው ማለት ነው፣ ከሃገር ቤት ደርሶ መልስ በኋላ በመጀመሪያ የሚነግራችሁ ስለተሰራው መንገድና ፎቅ ነው፣ምክንያቱም በተከራየው ኮንትራት መኪና መንደር ውስጥ መሽከርከር ስለማይችል ተዟዙሮ የመጣው አስፋልት አስፋልቱን እንደሆነና ሌላው ቀርቶ ያደገበትን ቤት እንኳን ያየው ማታ ሲጨላልም እንደሆነ የብዙ ጓደኞቼን እህትና ወንድሞች እማኝ ጠቅሼ መከራከር እችላለሁ፣ መሬቱ አልያም ኮንዶሚኒየሙ ባይሆን እንኳን ሃገር ቤት ደርሶ ለመምጣት በሩቅ ተስፋ ያለመው ደግሞ በሁለት አልያም ከዚያ በላይ ካርታ ስቦ የሚጫወት እንደ እስስቷ ያለም ሞልቶአል፣ እናም መጠርጠር ደግ ነው “ያልጠረጠረ . . . ነውና ነገሩ
ሳጠቃልለው ከላይ ያነሳነውን ጠባይ ከራስ ጸጉራቸው እስከእግር ጥፍራቸው የተዋረሱ አዕላፋት እንዳሉ ሁሉ ጥቂት እደግመዋለሁ ጥቂት ሃገር ወዳድ ሰዎች፣ በእውነት የሃገራቸው ፍቅር የሚያንገበግባቸው፣ የወጡበትን ምስኪንና ውድ ማህበረሰብ እንዲሁም የራሳቸውን ነጻነትና ለውጥ የሚናፍቁ እንዳሉና እንዲያውም አሁን አሁን በጥቂቱም ቢሆን ብቅ እያለች ያለችው “የነጻነት ጎህም“ በነዚህ ሃገር ውስጥም ውጪም ባሉ ጥቂት ቁርጠኞችና እውነተኛ ታጋዮች፣ እስስቷን ሳይሆን ሰው በሆኑ ሰዎች እንደሆነ ላስምርበትና፣ ጽሁፌን ልቋጭ
by ጥላሁን ዛጋ /Tilahun Zaga/
No comments:
Post a Comment