
በዛሬው እለት በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች የተበተነው የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት ህጋዊ ለተባሉትም ሆነ ህገወጥ ለሚባሉት ኢትዮጵያውያን የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ይላሉ እኝህ ጋዜጠኛ።
በሞባይል ስልኮች የተበተነው ኤስ ኤም ኤስ ኢትዮጵያውያንን ቀጥራችሁ የምታሰሩ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ያከራያችሁ ሁሉ በአስቸኳይ እንድታስወጡ፣ ይህን ባታደርጉ ግን 100 ሺ ረያል ትከፍላለችሁ የሚል እንደሆነ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል። ይህን መልእክት ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተከራዩበት ቤት ተባረዋል። 9 ኢትዮጵያውያንን ወደ አስጠጋው ኢትዮጵያዊ በመደወል መታሰቢያ ቀጸላ አነጋግራቸዋለች። እርሱ እንደሚለው መልክቱ መተላለፉን ተከትሎ ጓደኞቹ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርጎ በእርሱ ቤት ተጠልለዋል::
ከቤታቸው ከተባረሩት መካከል አንዱ ከ8 ወራት በፊት አባቱ ቤታቸውን ሸጠው ፣ በኪራይ ቤት እየኖሩ በህጋዊ መንገድ እንደላኩት ይናገራል። አሁን ቤትክን ለቀህ ውጣ ተብሎ ህይወቱ አደጋ ላይ ወድቋል::
የሳውዲ መንግስት በኦፊሴል እንዲህ አይነት መልክት ያስተላልፍ እንደሆነ የጠየቅነው ጋዜጠኛ፣ መንግስት በቀጥታ እንዲህ አያደርግም ነገር ግን እርሱ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት መልክቶችን እንደሚሰድ ይታወቃል ብሎአል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በማድረግ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት መታደግ ሲችል በቀን ይህን ያክል ሰው አስመጣሁ በማለት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል የሚለው ጋዜጠኛው፣ በሳውዲ የቀረው ኢትዮጵያዊ ወደ አገር ቤት የተመለሰውን በብዙ እጥፍ ይበልጣል ሲል በአገሪቱ ያለውን እውነታ አስረድቷል።
በሌላ በኩል ከሳውድ አረቢያ ወደ የመን የገቡ 3 ሺ ያክል ኢትዮጵያውያን በምግብ እጥረት ተጎሳቁለው እንደሚገኙ እስር ቤት ድረስ በመሄድ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሀይማኖት ጎብኝቷቸዋል።
No comments:
Post a Comment