Monday, April 14, 2014

የእንግሊዝ መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነትና የበጎ አድራጎት ሕጎች ተቃዋሚዎችን ፀጥ አሰኝተዋል አለ

April 14/2014

የእንግሊዝ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝንና ዲሞክራሲን በተመለከተ ባለፈው ሐሙስ ባወጣው እ.ኤ.አ. የ2013 ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምርጫ 97 በኋላ ሥራ ላይ ያዋላቸው የፀረ ሽብርተኝነት፣ የበጎ አድራጎትና ሌሎች ሕጎች ተቃዋሚዎችን ለመቆጣጠርና ፀጥ ለማሰኘት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው በማለት ክፉኛ ተቸ፡፡
ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምርጫ 97 በኋላ የወጡትን ሕጎች በመጠቀም ተቃዋሚዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና፣ የእንግሊዝ መንግሥትን ክፉኛ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነትና የበጎ አድራጎት ሕጎችም በሪፖርቱ ከፍተኛ አጽንኦት ተሰጥቷቸው ተዳሰዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከወጣ በኋላ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችና ሌሎች ለእስር መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ገልጾ፣ የበጎ አድራጎት ሕጉም በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል በማለት የሕጎቹን አፋኝነት አትቷል፡፡
የሪፖርቱ ክፍል 11 በዋነኝነት በአገሮች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ እንደማሳያነትም የ28 አገሮችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተንትኗል፡፡ ከእነዚህም አገሮች መካከል ተጠቃሽ በሆነችው ኢትዮጵያ የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ ባቀረበው ትንተና የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የእስረኞ መንገላታት መኖሩን አስረድቷል፡፡
ይህ የእስር ቤቶችን ሁኔታ የሚዘረዝረው ሪፖርት የተጠናቀረው 170 የሚሆኑ እስር ቤቶችን በመጐብኘት መሆኑን፣ ምርመራው የተካሄደውም ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት በተለምዶ ‹‹ማዕከላዊ›› የተሰኘው እስር ቤት በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በእስረኞች አያያዝ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ወቀሳ ይሰነዘርበታል በማለት ሪፖርቱ አትቶ፣ በእስር ቤቱ ውስጥ ግርፋትና መንገላታት መኖሩን ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ‹‹ልዩ ፖሊስ›› የተባለው ኃይልም እያደረሰ ያለው የመብት ጥሰት ሪፖርቱ ዋነኛ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡
ምንም እንኳን የተጠናከረ የፀጥታ ቁጥጥር መኖሩ ለክልሉ ያመጣቸው የመሠረታዊ አገልግሎትና የመሠረተ ልማት ዕድገትና አንዳንድ ጠቀሜታዎች መኖሩን ሪፖርቱ አስረድቶ፣ ‹‹በልዩ ፖሊስ›› ኃይል አባላት በክልሉ ተፈጸሙ ያላቸው ግርፋት፣ ማሰቃየትና ግድያ መኖራቸውን በመግለጽ ክፉኛ ይኮንናል፡፡
በዚህ የተነሳም የ‹‹ልዩ ፖሊስ›› አገልግሎቱ እንዲሻሻል የእንግሊዝ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም መስማማቱንና ችግሩን ለማሻሻል ቃል መግባቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

No comments:

Post a Comment