Saturday, November 9, 2013

ኢህአዴግ “አውራ ፓርቲ የሆንኩት በተቃዋሚዎች ጦስ ነው” አለ!

እናላችሁ — በሽብርተኝነት ዙሪያ በተደረገው ውይይት ላይ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ እንደተለመደው ኢህአዴግ “ከእንግሊዝ ከእነኮማው ቀድቼዋለሁ” የሚለውን የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ሞገቱ ሞገቱና ሲያቅታቸው “እንግዲህ ብታስሩንም እሰሩን እንጂ የታሰሩብንን አባላት ወህኒቤት ሄደን መጠየቃችን አይቀርም” አሉ፤ በተስፋ መቁረጥ። ለነገሩ ይህቺን እግረመንገዴን አነሳኋት እንጂ ዋና ጉዳዬስ ሌላ ነበር፡፡ ይኸውላችሁ —- በዚሁ ውይይት ላይ ከኢህአዴግም ከተቃዋሚም ጎራ የማይመስሉ አንድ “ሃኪም ነኝ” ያሉ ተሰብሳቢ፤ አስገራሚ አስተያየት ሰነዘሩ፡፡ (ምናለ የጦቢያን ፖለቲከኞች ቢያክሙልን?!) “ሃኪም ብዙ ባይናገርም እኔ ግን እድሉን ካገኘሁ እናገራለሁ” ያሉት ተሰብሳቢው፤ “የሚኒስትርነት ሹመት የሚሰጠው የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ቢሆን ኖሮ አብዛኞቹ ሚኒስትሮቻችን ፈተናውን ይወድቁ ነበር” ሲሉ የኢህአዴግ ሚኒስትሮችን ሸነቆጡ፡፡ ሽንቆጣውን ተከትሎ በአዳራሹ ውስጥ ከዳር እስከዳር የተስተጋባው ሳቅ ግን ግራ አጋባኝ፡፡ (የራሳቸው የሚኒስትሮቹ ሳይሆን አይቀርም!) ሃኪሙ ሳቁ ገታ እስኪል ጠበቁና፤“ይሄ ሳቅ የተናገርኩት ነገር እውነት መሆኑን ያረጋግጥልኛል” አሉ፡፡
አሁንም ያው ሳቅ ተስተጋባ፡፡ ይኼኔ ጆሮዬን ተጠራጠርኩት። “የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር ችላችሁ አትዘምሩትም ማለት ያስቃል እንዴ?” ስል ጠየቅሁ – ሚኒስትሮቹን ሳይሆን ራሴን፡፡ ትንሽ ቆይቼ ግን “ግዴለም– ይሳቁ!” አልኩኝ፡፡ (ባለሥልጣናት ሲስቁ አይቼ አላውቅማ!) አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ “ልማታዊ መንግስት” ሳቅ ላይ ያለው አቋም እንዴት ነው? እኔ የምለው ግን— ከሚኒስትሮቻችንና ከሌሎች የመንግሥት ሹመኞች መካከል ምን ያህሉ ብሄራዊ መዝሙራችንን በትክክል ጀምረው ይጨርሱታል? (ዶክተሩ ጉድ አፈሉ እኮ!) አይዟችሁ — መዝሙሯ የሹመት መስፈርት እንድትሆን “ሎቢ” የማድረግ ወይም “ፒቲሽን” የማሰባሰብ እቅድ የለኝም፡፡ አንዲት ከፓርላማ የማትጠፋ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኛ (ይቅርታ “ነፃ ፕሬስ” የለም፤ “የግል ፕሬስ” እንጂ ተብሏል ለካ!) ምን አለችኝ መሰላችሁ? “አብዛኞቹ የፓርላማ አባላትም መዝሙሩን የሚችሉት አይመስለኝም” ስትል ጥርጣሬዋን ሹክ አለችኝ፡፡
“እንዴት አወቅሽ?” አልኳት በጥርጣሬ እያየኋት። “ መዝሙር ሲዘመር አፋቸውን እየው እስቲ–አይነቃነቅም እኮ!” (“የኢትዮጵያን መዝሙር ሳያውቁ ኢትዮጵያን መምራት???”) በነገራችሁ ላይ — ከብሔራዊ መዝሙራችን ጋር በተገናኘ ሰሞኑን አንዲት ድንቅ የሆነች ኦሪጂናል የቢዝነስ አይዲያ ብልጭ ብላልኛለች፡፡ ምን መሰላችሁ? የሚኒስትሮቻችን ሞባይል ላይ ብሔራዊ መዝሙር መጫን ነው፡፡ ከዚያማ በቃ በፈለጉ ሰዓት ከሞባይላቸው ላይ እየከፈቱ Rehearse ያደርጋሉ – ይለማመዳሉ፡፡ ዝም ብሎ ቱባ ቱባ ሹማምንትን “ብሔራዊ መዝሙር አይችሉም” እያሉ ከማማት— እንዲህ እንደኔ ከእነ መፍትሄው ማቅረብ ብልህነትም ቅንነትም ይመሥለኛል፡፡ እንግዲህ—የብሔራዊ መዝሙራችንን ነገር በዚሁ እንግታና ወደ ሌላ ትኩስ የፖለቲካ አጀንዳ ደግሞ እንለፍ፡፡ እኔ የምላችሁ… ኢህአዴግ እንዴት “አውራ ፓርቲ” ሊሆን እንደቻለ በቅርቡ የተሰጠውን “ሳይንሳዊ” (ይቅርታ አብዮታዊ ማለቴ ነው!) ትንታኔ ሰምታችሁልኛል? የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አባ ዱላ፤ ስለኢህአዴግ “አውራ ፓርቲነት” ሲተነትኑ ፤ “የህዝቡና የፓርቲው ትክክለኛ መስተጋብር ውጤት ነው” ብለዋል፡፡
ይሄንን ብቻ አይደለም አፈጉባኤው ያሉት “ኢህአዴግ እያሸነፈ የሚቀጥልበትና ተቃዋሚ በተቃዋሚነት የሚቀጥልበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉም የገዢውንና የተቃዋሚውን ጎራ የወደፊት እጣፈንታ በ“ግምታዊ ጥናት” ላይ ተመስርተው ተንብየዋል፡፡ አይገርማችሁም? እኔ እኮ ኢህአዴግ ድንገት ተነስቶ “አውራ ፓርቲ” ነኝ ያለ ነበር የመሰለኝ፡፡ ለካስ በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው (በአብዮታዊ ጥናት ላይ ማለቴ ነው!) ባለፈው ዓመት ትዝ ይላችኋል አይደል —አቦይ ስብሃትን ጨምሮ በርካቶች “ፓርላማ አስደናቂ መነቃቃት አሳይቷል” ሲሉ፤ አፈጉባኤውን ጨምሮ በርካታ የምክር ቤቱ “ኢህአዴጎች” ሽምጥጥ አድርገው እንደካዱ? (ኢህአዴግ አንዳንዴ አድናቆትና ነቀፋ አይለይም ልበል?) በነገራችን ላይ — የኢህአዴግ “ወዶ-ገብ” የሆኑት በፓርላማ የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ሳይቀሩ “ዘንድሮ ፓርላማ ጥርስ አውጥቷል” በሚለው ሃሳብ እንደማይስማሙ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ (ድሮም ጥርስ አለው ለማለት እኮ ነው!) የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? ሰሞኑን አፈጉባኤ አባ ዱላ ከምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ፓርላማው ጥርስ ብቻ ሳይሆን መንጋጋ ለማብቀል እየሞከረ እንደሆነ የሚጠቁሙ ፍንጮች አሳይተዋል፡፡ እንዴት አትሉኝም? በአፈ-ጉባኤው የተነቃቁ ንግግሮች በኩል ነው! እናማ ወዳጆቼ—ዘንድሮ ፓርላማው እሳት የላሰ ባይሆን ምን አለ በሉኝ! እንዴ — የተከበሩ አባ ዱላ እኮ ቀጥ በቀጥ ባይሆንም “እንደድሮው መፋዘዝ የለም” ብለዋል (አድናቂያቸው ነኝ!) ምናልባት እሳቸው ባሳቡት መንገድ ከሄደላቸው እኮ “Best African Parliament” የሚል አዋርድ ልናፍስ ሁሉ እንችላለን፡፡
እኔን ትንሽ ያልተመቸኝ ምን መሰላችሁ? ይሄ በኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ የሰፈነው ተቃዋሚዎችን የመፍራት አባዜ (phobia) ነው፡፡ እኔ እኮ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም በቅርቡ ፓርላማ ውስጥ በሰጡት ማብራርያ “መንግስት አይፈራም፤ ባህሉም አይደለም–”ሲሉ ኢህአዴግንም ማለታቸው መስሎኝ ነበር፡፡ መሳሳቴ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል —- ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ወይ ይፈራቸዋል አሊያም ይጠላቸዋል፡፡ (ሁለቱም ደግሞ አክሳሪ ናቸው!) በቅርቡ አፈ-ጉባኤ አባ ዱላ፤ በአውራው ፓርቲ አባላት ከጥግ እስከ ጥግ ስለሞላው ም/ቤት ጥንካሬ ሲናገሩ፤ “ከየትኛውም ተቃዋሚ የበለጠ የኢህአዴግን (መንግሥትን) ጉድለቶች ነቅሶ የማውጣት ብቃት አለው” ብለዋል (ይሁንላቸው ባይመስልም!) አክለውም፤ እንደ ተቃዋሚ ግን ለማጋለጥ አይደለም የሚሰራው፤ ለማሻሻል እንጂ ብለዋል፡፡ (ወይ ማጋለጥ!) እኔ ደግሞ ምን እላለሁ መሰላችሁ — መልካም ሥራ በቅጡ መደነቅና መመስገን እንዳለበት ሁሉ መጥፎ ሥራ ደግሞ በደንብ መጋለጥ አለበት ባይ ነኝ፡፡ አሁን ለምሳሌ ሙሰኞችን ከማጋለጥ ውጭ ሌላ ምን አማራጭ አለ? (ምክርና ተግሳፅ ለ“ስኳር” አይሰራም!) እናም አውራ ፓርቲያችንን የምመክረው– የተባለውን ሁሉ አጨብጭበው ከሚቀበሉ “አባላት” ይልቅ ለጊዜው ቢኮሰኩስም ያለአንዳች ምህረት ስህተትንና ጉድለትን የሚያጋልጡ ተቃዋሚዎች ይሻላሉ፡፡
(“ጠንካራ ተቃውሞ እኮ ጥርት ያለ መስተዋት ማለት ነው”ጥቅስ የራሴ!) እናም ኢህአዴግ “ነፍሴ” ተቃዋሚን እንደ ጦር መፍራቱን እንዲተው “ሜዲቴሽን” ነገር እንዲጀምር እመክረዋለሁ፡፡ ከጀመርኩት ላይቀር ኢህአዴግ ተቃዋሚን በተመለከተ ያለውን አቋም ለማሳየት ያህል አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ፓርቲያቸው “አውራ ፓርቲ” የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ የተናገሩትን እነሆ (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!) “ኢህአዴግ ድርብ ኃላፊነት የተሸከመውና አውራ ፓርቲ የሆነው ተቃዋሚዎች መወጣት ያለባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው ነው” በሌላ አነጋገር— ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ የሆነው ወዶና መርጦ ሳይሆን ተገዶ ነው፤በተቃዋሚ ድክመት! (ችጋር በቅቤ ያስበላል አሉ!) በነገራችሁ ላይ — አሁንም ኢህአዴግ “ጠንካራ ተቃዋሚ ስጠኝ!” የሚለውን ፀሎቱን አጠናክሮ እንደቀጠለ ከውስጥ ምንጮች መረጃ ደርሶኛል፡፡
Source-www.addisadmass.com

No comments:

Post a Comment