Friday, November 1, 2013

ሰላማዊ ትግል እና ባህሪያቱ – ስልጠና ክፍል ሶስት – አንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት

በአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት የተዘጋጀው የ5 ሳምንት ስልጠና የመጀመሪያው ክፍል (1) እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ረጅም የነፃነት ዘመን ሲኖራት በስልጣኔ ግን ብዙም እንዳልገፋችም። ስለዚህ ስልጠና ክፍል አንድ “ኢትዮጵያ ምን ስትሰራ ነበር?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ሁለት አብይ ክሎች ያሉት ሰፊ
ታሪካዊ መልሶች ሰጥቷል። በመቀጠል ክፍል አንድ (2) የሰላማዊ ትግልን እድገት አስመልክቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ዛሬ እስካለንበት ዘመን ያደረገውን ጉዞ እና እድገት መርምሯል። ክፍል ሁለት ደግሞ በሰላማዊ እና ትጥቅ ትግሎች መካከል ንፅፅራዊ ምርምሮች ማድረጉ ይታወሳል። በመቀጠል ሰላማዊ ትግል እና ትጥቅ ትግል የደጋገፋሉን? እና ሁለገብ የትግል ዘዴ ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። በመጨረሻ የመንግስት ሽግግር ባህላችን በተለያዩ ዘመኖች በተደረጉ የመንግስት ሽግግሮች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው በደል ተዘርዝሯል። ስልጠና ክፍል ሶስት ዋና እና ጠቃሚ እንዲሁም ወቅታዊ የሆኑ በርካታ የሰላማዊ ትግል ጽንሰ አሳቦችን ያቀርባል። ወቅታዊዎቹን ጉዳዮች ምሳሌ እየሰጠ ያብራራል። ስልጠና ክፍል ሶስት 6 ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነሱም፥ (1ኛ) ለሰላማዊ ትግል ፕላን መቀየስ (መተለም)፣ (2ኛ) የፖለቲካ ኃይል እና የፖለቲካ ኃይል ምንጮች፣ (3ኛ) የድጋፍ ምሶሶዎች እና ከፖለቲካ ኃይል ምንጮች ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ (4ኛ) ነፃ ሆኖ የተወለደ ህዝብ ተገዢነትን በመቀበል ነፃነቱን እንዲያስነጥቅ የሚያደርጉት ምክንያቶች እና ያስነጠቀውን ነፃነት ለማስመለስ ምን ማድረግ እንዳለበት፣ (5ኛ) የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች፣ እና (6ኛ) ሰላማዊ ትግል ለውጥ የሚያመጣባቸው ሶስቱ ተዳማሪ መንገዶች ናቸው። (1ኛ) ለሰላማዊ ትግል ፕላን መቀየስ (መተለም)፥ ቁም ነገር ሊሰራ የሚችል ሰላማዊ ትግል ለማኪያሄድ ለሰላማዊ ትግል ፕላን የሚቀይሱ (ስትራተጂስቶች) እና በድስፕሊን የታነጸ የሰላም ትግል ሰራዊት እንደሚያስፈልጉ፣ ለሰላም ትግል ፕላን ለመቀየስ መከናወን የሚገባቸው ተግባሮች የሚከተሉት 5 ክንውኖች፥ (1) አብይ ግብን በግልጽ ማስቀመጥ (ይህ አብይ ግብ መድረሻችንን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት – ለምሳሌ የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ የአንድነት ፓርቲ በግልጽ የተቀመጠ ግብ ነው።)፣ (2) አብይ ስትራተጂ ማስላት (አብይ ስትራተጂ የግባችንን ማስፈጸሚያ መንገድ በግልጽ ያስቀምጣል – የትግል ስልትን ጨምሮ። አብይ ስትራተጂ በሰፊ ጥናት ላይ የተመሰረተ እና በየጊዜው የማይለወጥ አውራ ጎዳና ነው።)፣ (3) አብይ ስትራተጂያችንን የምናስፈጽምባቸው ዘመቻዎች መተለም (የእነዚህ ዘመቻዎች ግቦች ህዝብን ማነቃቃት እና ከፍርሃት ማውጣት፣ አምባገነኖች በፖለቲካ ኃይል ምንጮች ያላቸውን ቁጥጥር ማዳከም እና የተቃዋሚዎችን ቁጥጥር ከፍ ማድረግ፣ ለምርጫ በሚደረግ ዝግጅት ህዝብ በብዛት ወጥቶ እንዲመርጥ እና የምርጫ ውጤት እንዲያስከብር ዘዴዎች ማስተማር ሊሆኑ ይችላሉ)፣ (4) ዘመቻዎችን የምናስፈጽምባቸው ታክቲኮች መንደፍ (ታክቲኮች ውስን ግብ ያላቸው ሁኔታዎች ሲቀየሩ ሊለዋወጡ የሚችሉ አጫጭር ፕላኖች ናቸው)፣ (5) ከ200 የማያንሱት የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ማወቅ እና መጠቀም መቻል (የሰላም ትግል መሳሪያዎች የታክቲኮች ማስፈጸሚያ ሲሆኑ ታክቲኮች እና የሰላም ትግል መሳሪያዎች ተጋግዘው በየደረጃው የሚደረጉ ዘመቻዎችን ተፈጻሚ ያደርጋሉ።) እንደሚያካትት ይዘረዘራል። ለሰላማዊ ትግል ፕላን የሚቀየስበት ምክንያት አምባገነኖች በፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ዝቅ ለማድረግ እና የሰላማዊ ትግልን ሰራዊት ቁጥጥር ከፍ ለማድረግ መሆኑን የሰላም ትግል ፕላነሮች ሁልጊዜም ሊዘነጉት እንደማይገባ በማስታወስ ወደ ሁለተኛው የመወያያ ርዕስ ሽግግር ያደረጋል። (2ኛ) የፖለቲካ ኃይል እና የፖለቲካ ምንጮች፥ የገዢው ወይንም የተቃዋሚ ፓርቲ የፖለቲካ ኃይል መጠን የሚወሰነው በፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ ባላቸው ቁጥጥር መጠን እንደሆነ፣ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ከህዝብ ጋር የሚኖሩ እና ባለቤታቸውም እራሱ እዝብ እንደሆነ፣ በፈቃደኛነት ወይንም በፍራቻ ወይንም በግዴለሽነት ህዝብ የፖለቲካ ኃይል ምንጮችን ለአምባገነኖች እንደሚለግስ፣ መለገስ ከቻለ ደግሞ መንፈግ እንደሚችል፣ ከአምባገነኖች ወስዶ ለተቃዋሚ ፓርቲ ሊለግስ የሚችለው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቢሮ ፖለቲካ ተላቀው በከተሞችን እና በገጠሮች ህዝብ ውስጥ በመግባት ቀጣይነት ያላቸው ህዝባዊ ስምሰባዎች እና ቅስቀሳዎች ሲያደርጉ ብቻ እንደሆነ ከፍ ባለ ድምጽ ተደጋግሞ ይዘረዘራል። በማስከተልም የሚከተሉት 6 የፖለቲካ ኃይል ምንጮች፥ (1) የስልጣን ባለቤትነት ወይንም ህጋዊ ገዥነት መብት (የመንግስት ወይንም የተቃዋሚ)፣ (2) ድጋፍ እና ትብብር የለገሰ ህዝብ ቁጥር (ለመንግስት ወይንም ለተቃዋሚ – በሰላማዊ ትግል የደጋፊ ህዝብ ቁጥር የፖለቲካ አቅምን ይወስናል።)፣ (3) ክህሎት እና እውቀት መለገስ (ለመንግስት ወይንም ለተቃዋሚ)፣ (4) በረእዩተ አለም ወይንም በጎሳ ተመሳሳይነት የሚገኝ የህዝብ ድጋፍ መጠን (ለመንግስት ወይንም ለተቃዋሚ)፣ (5) የአገር ሃብት ባለቢትነት (ለምሳሌ መንግስት የመሬት ባለቤት ከሆነ የአራሹን እና አርቢውውን ህዝብ ፖለቲካ ጸባይ ሊቆጣጠር ይችላል። የኢንዱስትሪ እና የገንዘብ ድርጅቶች ባለቤት ከሆነ ደግሞ የከተማውን ህዝብ የፖለቲካ ጸባይ ሊቆጣጠር ይችላል። ወ.ዘ.ተ.)፣ (6) የመቅጫ አቅሞች መጠን ለምሳሌ እስር ቤት የመወርወር፣ በቅጣት መልክ ንብረት የመንጠቅ፣ የትምህርት እድል ወይንም በስራ ቦታ እድገት የመከልከል፣ ነፃ ፕሬሶችን የመዝጋት እና የመሳሰሉት የመሳሰሉት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች እና ህዝብን የመንግስት ስልጣን ለማድረግ በሚደረግ ትግል ላይ ያላቸው ተጽእኖ ይተነተናል። አምባገነን መንግስት የእለት ተእለት ስራውን (ጭቆናውን ጨምሮ) ለማከናወን፣ የሰላም ትግል ሰራዊትም የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ግቡን ለማራመድ የድጋፍ ምሶሶዎች ያስፈልጉታል። የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በድጋፍ ምሶሶዎች ውስጥ ከህዝብ ወደ መንግስት ወይንም ወደ ተቃዋሚዎች ይፈሳሉ። (3ኛ) የድጋፍ ምሶሶዎች፥ አምባገነን ገዢዎችም ሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ኃይል ድጋፍ ምሶሶዎች ሊኖሩዋቸው እንደሚችል፣ አምባገነኖች በድጋፍ ምሶሶዎች ውስጥ የሚያገኙዋቸውን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በመጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲ ድጋፍ ምሶሶዎች እንዲባዙ እና እንዲጠናከሩ እንደማይፈቅዱ፣ ስለዚህ የሰላም ትግል ፕላነሮች በአምባገነኖች በተለይም በዋናዎቹ የድጋፍ ምሶሶዎቻቸው ላይ በማትኮር የአምባገነኖች የፖለቲካ ኃይል እንዲዳከም እና ብየተቃዋሚ የድጋፍ ምሶሶዎች እንዲያብቡ እና እንዲጠናከሩ ማድረግ እንዳለባቸው የተነተናል። በተጨማሪ የሚከተሉት 9 ያህል የድጋፍ ምሶሶዎች ተነስተው የሰላም ትግል ፕላነሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳቦች ይሰነዘራሉ። ዘጠኙ የድጋፍ ምሶሶዎች፥ (1) ፖሊስ – ህገ መንግስት ከማክበር ፈንታ አምባገነኖችን እንዲያከብር ይደረጋል። ዜጎች የፖሊሶችን ዝንባሌ ለመቀየር የመንግስትን መለወጥ ወይንም መቀየር መጠበቅ የለባቸውም። “ፖሊስ የህዝብ ነው፣ የኛ ነው” የሚሉት መፈክሮች ትምህርት ለጋሽም ናቸው። ፖሊሶች ውሎዋቸው ህብረተሰቡ ውስጥ ስለሆነ መቀራረብ ይቻላል። ሙያቸውን እንፈልገዋለን። የብዙዎቹን። (2) የጦር ኃይል – ለህገ መንግስት ተገዢ እንዲሆን ያስፈልጋል፥ (3) ሲቪል ሰርቫንት/ቢሮክራሲው (የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች) – በሰላማዊ ትግል የመንግስት ለውጥ ለማምጣት እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ የሚታገሉ ተቃዋሚዎች የመንግስት ሰራተኞችን ድጋፍ ማግኘትን አስፈላጊነት ሊዘነጉት አይገባም፣ (4) ሚዲያ – በሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዴሞክራሲ ለማጣት የሚመኝ በሙሉ ህዝብን መድረስ የሚያስችለው ሚዲያ ያስፈልገዋል። አምባገነኖች ይህን ስለሚያውቁ ነው የተቃዋሚ ጋዜጣዎች ሳይቀሩ የሚዘጉት፣ በሌላ በኩል የህዝብ ንብረት የሆኑትን ቴሌቪዥኖች፣ ሬዲዮኖች፣ ጋዜጣዎች እንዲሁም የፓርቲያቸው ጋዜጣዎች እና መጽሔቶች እናንተ ማን ናችሁ የሚላቸው የለም። የሰላም ትግል ፕላነሮች ይኽን ማስተዋል አለባቸው። (5) የንግድ ማህበረሰብ፣ (6) ወጣት – አምባገነኖች ወጣቱ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል የሰላም ትግል ፕላነሮች ሊያስታውሱ ይገባል፣ (7) ሰራተኞች – አምባገነኖች ሰራተኛውንም ይፈራልይ። በተቻላቸው መጠን በነፃ እንዲደራጅ አያደርጉም፣ (8) የሃይማኖት ተቋሞች – አምባገነኖች እነዚህን ተቁሞች ነፃ አይለቁም እና (9) መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች – በመንግስት ቁጥጥር ካልሆኑ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ለዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አጋር ስለሚሆኑ አምባገነኖች በነፃነት እንዲኖሩ አይፈልጉም። ምክንያት ፈጥረው እንቅስቃሴያቸውን ይገድባሉ ወይንም ይዘጋሉ። (4ኛ) ብዙ ህዝብ ለምን ለጥቂቶች ይገዛል የሚለው ጥንታዊ ጥያቄ፣ ነፃ ሆኖ የተወለደን ህዝብ ነፃነቱን ያስነጠቁት 6 ምክንያቶች ይብራራሉ። እነሱም፥ (1) ልማድ (ከላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተገዢነት ልማድ)፣ (2) ቅጣት መፍራት፣ (3) የግል-ጥቅም፣ (4) እሺ ብሎ መገዛትን የሞራል ግዴታ አድርጎ ማመን (መጽሀፍ ቅዱስ ንጉሱ የእግዚአብሔር እንደራሴ ሰለሆነ ተገዙለት ይላል)፣ (5) አንዳንድ ሰዎች ለተወሰኑ ገዢዎች የደም፣ የሳይኮሎጂ ወይንም ሌላ ቅርበት ያላቸው አድርገው በመውሰድ እነዚያ አምባገነን መሪዎች ነፃነታቸውን ቢገፉዋቸውም ሳይከፉ ይቀበላሉ፣ (6) በራስ መተማመን ማጣት ናቸው። አንዳንድ ሰዎች በ6ቱም ምክንያቶች የተነሳ ነፃነታቸውን ያስረክባሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ምክንያቶቻቸው ከቀድሞዎቹ ሊለዩ ይችላሉ። ስለዚህ የእያንዳንዱን ግለሰብ ምክንያት ማጥናት ተገቢ መሆኑን የሰላማዊ ትግል ፕላነሮች በቅድሚያ ሊገነዘቡ ይገባል። የተግባር ፕሮግራም ከመንደፋቸው በፊት። በስልጠና ክፍል አንድ ለውይይት የቀረበው የጋንዲ ገንቢ ፕሮግራም ትዝ ይላችኋል? ጋንዲ የተግባር ፕሮግራሙን የገነባው 200 ሚሊዮን ህዝብ ለምን ለ30 ሺ እንግሊዞች ሊገዛ ቻለ ? ለሚለው ጥያቄው ያገኛቸውን መልሶች መሰረት በማድረግ እንደነበር በስልጠና ክፍል አንድ ተወያይተናል። (5ኛ) የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች፣ ሶስቱ አብይ የሰላም ትግል ማራመጃ ክፍሎች (ግምጃ ቤቶች) (1) ተቃውሞ እና ማግባባት (Protest and Persuasion)፣ (2) ትብብር መንፈግ (non-cooperation) ፣ (3) ጣልቃ መግባት (intervention) የተባሉት እንደሆኑ፣ እያንዳንዱ ግምጃ ቤት ውስጥ የሚገኙት የሰላም ትግል መሳሪያዎች ድምር 200 ያህል እንደሚደርስ እና የኢትዮጵያን ባህል ከግንዛቤ በማስገባት በኢትዮጵያ ሊሰሩ ከሚችሉት ውስጥ ዋና ዋናዎቹን የትኞቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዚህ ክፍል እንመረምራለን። (1) ተቃውሞ እና ማግባባት (Protest and Persuasion) የተባለው አብይ ክፍል (ግምጃ ቤት) ከያዛቸው መሳሪያዎች ውስጥ ጥቂቱ (ሀ) በድረ ገጾች ወይንም በጋዜጣዎች በሚቀርቡ ጽሑፎች ወይንም ህዝብ በተሰበባቸው አደባባዮች በሚደረጉ ንግግሮች (በሚሰጡ መግለጫዎች) ተቃውሞን (ወይንም ድጋፍን) ማሳወቅ . . . ወ.ዘ.ተ. (ለ) መፈክሮች እና ባነሮች (Banners) መጠቀም፣ ጽሑፎች በማሰራጨት፣ በግድግዳዎች ላይ በመጻፍ፣ እንዲሁም ሲዲ፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን በመጠቀም መልዕክት ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ . . . ወ.ዘ.ተ. (ሐ) ድራማዎች እና ሙዚቃዎች በመጠቀም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጸሙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሞራላዊ ስህተቶችን መቃወም። ለምሳሌ “ዋሽቶ ለመኖር” የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ሙስናን ከሞራል አንጻር የሚቃወም ጥሩ የሰላም ትግል መሳሪያ ነው። (መ) በሰላም ትግል ላይ ለተገደሉ (ሰማዕታት) ክብር በመስጠት ገዳዮችን እና ድርጊቱን መቃወም፣ ለተገደሉ የፖለቲካ ሃዘን ባደባባይ ማድረግ፣ እሬሳን ተሸክሞ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እና የቀብር ስርዓት መፈጸም፣ “የሰማዕታት ቀን” መሰየም፣ በሰማዕታት መቃብሮች ላይ ሐውልት ማሰራት እና በሐውልታቸው ላይ ለምን እና የሞቱበትን ምክንያት መጻፍ . . . ወ.ዘ.ተ. በዚኽ አብይ ክፍል በትንሹ 54 ያህል የሚሆኑ የተለያዩ የሰላም ትግል መሳሪያ አይነቶች አሉ። ይሁን እንጂ በዚኽ አብይ ክፍል የሚገኙት የሰላም ትግል መሳሪያዎች ብቻቸውን የመንግስትን የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ለመቆጣጠር እና ለማዳከም አያስችሉም። በአብዛኛው ተምሰሌታዊ (symbolic) ናቸው። ፋይዳቸው ህዝብ ማነቃቃት ስለሆነ በፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ቀጥተኛ ሳይሆን ተዘዋዋሪ ነው። (2) ትብብር መንፈግ የመንግስትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በቆጣጠር እና በማድረቅ መንግስትን ለመቆጣጠርም ሆነ ከስልጣን ለማውረድ መድሃኒት የሆነ የሰላም ትግል መሳሪያ ነው። ለምሳሌ መንግስት የምርጫን ውጤት አልቀበልም ሲል ትብብር የመንፈግ ትግል የሚያስተላልፈው መልዕክት “እኛ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ (We the People of Ethiopia) የለገስንህን ትብብር ነፍገናል እና ከስልጣን ውረድ!” የሚል ነው። ትብብር መንፈግ የተባለው አብይ ክፍል ሶስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ማህበራዊ ትብብር መንፈግ የሚለውን ክፍል ወደጎን ትተን የቀሩት ሁለቱ ክፍሎች እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ይገለጻሉ፥ (ሀ) ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ፥ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው የንግድ ግንኙነት በማቋረጥ (የንግድ እገዳ ወይንም እቀባ) ከፖለቲካ ባላንጣ ጋር አለመገበያየት ነው። በውስጡ 26 ያህል የሰላም ትግል መሳሪያዎች አሉት። መገበያየት ማቋረጥ በአገር ውስጥ እንዲሁም በአገሮች መካከል ይፈጸማል። ሁለተኛው ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ ደግሞ ስራ ማቆም (Strikes) ሲሆን 22 ያህል የሰላም ትግል መሳሪያዎች አሉት። ምሳሌ፥ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የትራንስፖርቴሽን (የባቡር፣ ያቶቢስ፣ የታክሲ፣ የአየር መንገድ፣ ወ.ዘ.ተ.)፣ የማዕድን፣ የመንግስት መስሪያ ቤት፣ ወ.ዘ.ተ. ሰራተኞች ለየብቻቸው ወይንም በህብረት የሚያደርጉት የስራ ማቆም። ይኽ ሁለተኛው ትብብር መንፈግ በኃይል ወይንም በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የወጣን ወይንም የህዝብ ድምጽ አጭበርብሮ በስልጣን ለመቆየት የሚሞክር መንግስትን የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ይቆጣጠራል። ይኽ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ካለው የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ያደርቃል። ይኽ ከሆነ ደግሞ መንግስት ለወታደሩ፣ ለጦሩ፣ ለመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የሚከፍለው ደሞዝ ሊያጣ እና እንደቀድሞው መግዛት ሊያቅተው ይችላል። ለማንኛውም ዲሞክራሲን ለማምጣት በሚደረግ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ይኽ የትግል መሳሪያ ስራ ላይ ሲውል በዘር እና በሃይማኖት ክፍፍል እንዳይበከል (contaminate እንዳይደረግ) ጥንቃቄ መደረግ አለበት። (ለ) ፖለቲካዊ ትብብር መንፈግ፥ ይህ ክፍል 38 ያህል የሰላም ትግል መሳሪያዎች አሉት። ለናሙና ያህል አራት ምሳሌዎች እንመልከታለን። የመጀመሪያው የፖለቲካ ታማኝነትን መንፈግ (የመንግስትን የገዢነት ስልጣን መግፈፍ) (Rejection of authority) የሚለው ሲሆን ምሳሌ፣ ዜጎች በየድረ ገጹ፣ በየመጽሐፉ፣ በየመጽሔቱ እና በየጋዜጣው ላይ የሚፅፉት የፖለቲካ ትችት፣ ኩነና እና የትግል ቅስቀሳ። እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣኖች፣ ጀነራሎች እና በውጭ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች ስልጣናቸውን እየለቀቁ ሰላማዊ ትግሉን ሲቀላቀሉ፣ ሁለተኛው ዜጎች ለመንግስት የፖለቲካ ትብብር ሲነፍጉ (Citizens’ non-cooperation with government) – ምሳሌ፣ ዜጎች በምርጫ ወቅት ድምጻቸውን በስልጣን ላይ ለሚገኘው ፓርቲ በመንፈግ ለተቃዋሚ ፓርቲ ሲለግሱ፣ ዜጎች በነፃነት አደባባይ በሚሊዮኖች ሆነው በመውጣት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ ሲጠይቁ። ወ.ዘ.ተ. ሶስተኛው የመንግስት ሰራተኞች (ሲቪል ሰርቫንቱ/ቢሮክራሲው) ለመንግስት የፖለቲካ ትብብር ሲነፍጉ (Government personnel’s non-cooperation with government) – ምሳሌ፥ የአስተዳደር ስራ በተገቢ አለመስራት፣ የጸጥታ ክፍል ሙሉ ትብብር ሲነፍግ፣ ፖሊስ ፈልገህ እሠር የተባለውን ግለሰብ እያየ እንዳላየ ሲሆን፣ ፖሊስ ግደል ሲባል ከመግደል ወደ ሰማይ ሲተኩስ ወይንም እንቢ ሲል። ወ.ዘ.ተ. እና አራተኛው የአለም አቀፍ መንግስታት ለመንግስት የፖለቲካ ትብብር መንፈግ (International governmental action) – ምሳሌ፥ ተቃዋሚዎች ባደረጉት ከፍተኛ ዝግጅት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ምርጫውን በድብቅ መስረቅ እንዳይችል በማድረጋቸው አይን ባወጣ መንገድ የምርጫውን ውጤት አለቀበልም ሲል አለም አቀፍ ህብረተሰብ በስልጣን ላይ ለሚገኝ መንግስት ህጋዊ ዲፕሎማሲያዊ እውቅናን ሲነፍግ ወይንም ሲገፍ ወይንም ሲያቋርጥ። (3) ጣልቃ መግባት (intervention)፥ ድምራቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ መታገያ መሳሪያዎች አሉት። እነዚኽ የሰላም ትግል መሳሪያዎች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ለባለስልጣኖችም የሚደቅኑት ፈተና ቀጥተኛ በመሆኑ ፈጥኖ መልስ የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ከባለስልጣኖች የሚሰነዘረው ምላሽ ወከባ እና ቅጣት ሊሆንም ይችላል። ትብብር ከመንፈግ የሰላም ትግል መሳሪያዎች ይልቅ ጣልቃ መግባት የሰላም ትግል መሳሪያዎች አምባገነኖችን ይበልጥ ሊያስቆጣ እና ፈጣን ቅጣት ሊያስከትልም እንደሚችል የሰላም ትግል መሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል። አራት ምሳሌዎች እንመልከት፥ አንደኛው ሳይኮሎጂያዊ ጣልቃ ገብነት (Psychological intervention) የተባለው ሲሆን – ምሳሌ የረሃብ አድማ በማድረግ ዜናውን በአለም አሰራጭቶ የመንግስት ባለስልጣኖችን ማስጨነቅ፣ ሁለተኛው አካላዊ ጣልቃ ገብነት (Physical intervention) የሚለው ሲሆን ምሳሌ፥ የግብጽ ካይሮን የነጻነት አደባባይ (ታህሪርን) መውረር እና የድንኳኖች ከተማ መስርቶ ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ በአደባባዩ መኖር (Sit-ins)፣ የ1997 ምርጫን ተከትሎ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ወደ እስር ቤት በሚወሥደው የፖሊስ መኪና መንገድ ላይ የኮተቤ ተማሪዎች እና ያካባቢው ዜጎች መንገድ መዝጋታቸው (ከፖሊስ አዛዦች መሐይምነት የተነሳ ወንጀል ተደርጎ የተገደሉ ቢኖሩም ትግሉ ሰላማዊ ትግል ነበር) እና የመሳሰሉት የሰላም ትግል መሳሪያዎች፣ ሶስተኛው ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት (Economic intervention) ሲሆን ምሳሌ ደግሞ የባለስልጣኖች ገንዘብ እና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ (የሊቢያው መሪ የጋዳፊ ሃብት በአሜሪካ፣ የግብጹ ሙባረክ ሃብት በስዊዝ ባንክ፣ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ንብረት በተባበሩት መንግስታት እንዳይንቀሳቀስ እንደተደረገው)፣ የንግድ ደንበኛን በመቀየር የፖለቲካ ባላንጣን ኢኮኖሚ ማዳከም፣ አራተኛው ደግሞ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት (Political intervention) የሚባለው ሲሆን ምሳሌ፣ የመንግስት አሰተዳደር በስራ እንዲወጠር እና የእለት ከእለት ስራውን መስራት እንዳይችል ማድረግ፣ የሰላዮችን ስም ይፋ ማድረግ፣ የሰላዮች ስም ይፋ ሲደረግ ስህተት እንዳይፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የጋዳፊ መንግስት ትሪፖሊን ጨምድዶ ይዞ ሳለ ተቃዋሚው በቤንጋዚ ከተማ የመሰረተው ትይዩ መንግስት (Parallel government) ጥሩ ምሳሌ ነው። የእለቱ የመጨረሻው የስልጠና ነጥብ የሰላም ትግል ለውጥ ማምጫ በሆኑት ሶስቱ ተዳማሪ መንገዶች ላይ ይሆናል። የሰላም ትግል ፕላነሮች እነዚህን ሶስት መንገዶች የመጠቀም ብቃታቸውን ከፍ ለማድረግ ከፍ ብለው በተዘረዘሩት የሰላማዊ ትግል ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ንቁ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። (6ኛ) የሰላም ትግል ለውጥ ማምጫ መንገዶች፥ የሰላም ትግላችን ግብ ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ እንደሆነ፣ ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት ለማድረግ በህዝብ እና በአምባገነን መንግስት መካከል የሚገኘው የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ግንኙነት ወደ ህዝብ እንዲያደላ ያልተቋረጠ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ሽግሽግ መደረግ እንዳለበት፣ ይህ ደግሞ የሰላማዊ ትግል መስፋፋትን እና አቅም መገንባት የግድ እንደሚጠይቅ እና (1) መቀየር/የመለወጥ (Peaceful conversion)፣ (2) መቻቻል (accommodation) እና (3) ሰላማዊ አስገዳጅነት እና ሰላማዊ መፈረካከስ/መበታተን (Peaceful coercion and disintegration) የተባሉት ሶስት መንገዶች ከሰላማዊ ትግል አቅም ግንባታ አንስቶ እስከ መንግስት ሽግግር ፍጻሜ የሚያደርስ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ሽግሽግ ወደ ህዝብ እንዲያደላ ሊያደርጉ የሚችሉ መንገዶች መሆናቸው እንደሚከተለው ባጭር ባጭሩ ይዘረዘራል። (1) መቀየር/መለወጥ፥ በአምባገነኖች የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ የሚያደርሰው ቀጥተኛ ጥቃት ባይኖርም የሰላማዊ ትግል ፕላነሮች ፕላን ቀይሰን በአግባብ ከተጠቀምንበት መቀየር/መለወጥ የተባለው የለውጥ ማምጫ መንገድ የመንግስት ባለስልጣኖችን ብቻ ሳይሆን ህዝብንም በመቀየር/በመለወጥ ለዲሞክራሲ ትግል መስፋፋት እና ለሰላማዊ ትግል አቅም ግንባታ ጥቅም በመስጠት በአምባገነኖች የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ ተዘዋዋሪ (ቀጥተኛ ያልሆነ) ጥቃት እንደሚያደርስ፣ ለምሳሌ፥ ተቃዋሚዎች ከቢሮ ፖለቲካቸው ተላቀው በአገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወሩ ቀጣይነት ያላቸው ሰላማዊ ሰልፎች፣ ተቃውሞዎች፣ የአደባባይ እና የአዳራሽ ህዝባዊ ውይይቶች ቢያደርጉ እና እነዚህ የሰላማዊ ትግል ዜናዎች ቢሰራጩ የህዝብን ዝንባሌ ሊቀይሩ፣ ከፍራቻ ነፃ ሊያወጡ እና ትግሉን እንዲቀላቀል ሊያነሳሱ ይችላሉ። ይብራራል። (2) መቻቻል፥ አንዳንድ ጊዜ አምባገነናዊ መንግስቶች በዜጎች ዘንድ ላገር አሳቢ መስሎ ለመታየት፣ በውጭ መንግስታት ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ወይንም የገጠማቸውን የለውጥ ጥያቄ ውጥረት ለማርገብ ሲሉ የዲሞክራሲ ኃይሎችን ጥያቄዎች ይቀበላሉ። ይኽን የሚያደርጉት መብት አክባሪ እና ትሁት በመሆናቸው ሳይሆን ለተቃዋሚዎች የለውጥ ጥያቄ የመቻቻል መፍትሄ ብንሰጥ ስልጣናችን አይነጠቅም፣ አቅማችንም አይዳከምም ነገር ግን ከጭቅጭቅ እንድናለን ከሚል እምነት ተነስተው ነው። ይሁን እንጂ አንድ አምባገነን መንግስት መቻቻልን እንደመፍትሄ ከወሰደ በስልጣን ላይ የነበረው ፍጹም የሆነ ቁጥጥር ተቀንሷል ማለት ነው። በህዝብ እና በአምባገነኖች መካከል በነበረው የኃይል ሚዛን ግንኙነት ላይ የተወሰነ ሽግሽግ ተደርጓል ማለት ነው። በዚህ ክፍል ትልቁ ትኩረታችን ምርጫ ላይ ነው። ምርጫም መቻቻል ነው። የኢትዮጵያ ህገ-መንግስትም በየአምስት አመቶች ምርጫ እንደሚደረግ እና የመንግስት ስልጣን ከተሸነፈ ፓርቲ ወደ አሸናፊ ፓርቲ ሰላማዊ ሽግግር እንደሚደረግ ይደነግጋል። ህገ-መንግስቱ ይሄን ቢደነግግም አምባገነኖች ነጻ ምርጫ ፈቅደው፣ ውጤቱ የማይወዱት ቢሆንም በደስታ ተቀብለው ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ይለቃሉ ብለን ማመን የለብንም። ሳይገደዱ በፈቃደኛነት ስልጣን ማስረከብ የአምባገነኖች ጸባይ አይደለም። አምባገነኖች ዲሞክራቶች አይደሉም። አምባገነኖች ስልጣን ላይ የወጡት በግድያ እና በሽብር እንደሆነ እና በስልጣን ለመቆየትም መንግስታዊ ሽብር እንደሚፈጽሙ እያወቅን ምርጫ ስለተባለ ብቻ ባህሪያቸውን መዘንጋት የለብንም። አምባገነኖች ምርጫን የሚፈልጉት ህጋዊነት ለማግኘት ብቻ ነው። ምርጫን የሚያደርጉት ደግሞ መራጩን በማስፈራራት የምርጫውን ውጤት እንሰርቃለን ከሚል ሙሉ እምነት በመነሳት ነው። መረጩን እንደሚያዋክቡ፣ የምርጫ ሳጥኖችን በሃሰት ድምጾች እንደሚሞሉ እና ምርጫውን ውጤት እነሱን እንዲደግፍ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ቀደም ብለን መገመት እና መስረቅ የሚያስችሉ ቀዳዳዎችን በሙሉ መድፈን አለብን። እርግጥ ዝግጅት ያስፈልጋል። የሰላም ትግል ፕላነሮች ይህን የአምባገነኖች ምኞት ወደ ሃዘን መቀየር አለባቸው። “አሳ ፈላጊው አምባገነን መንግስት ዘንዶ አወጣ” መሆን አለበት የአምባገነኖች ምርጫ ምኞት። ሰርቢያዎች እንዳደረጉት። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2000 ዓመተ ምህረት በሰርቢያ እና በ2002 ዓመተ ምህረት በዝንባቡዌ የተደረጉት ምርጫዎች በንፅፅር ማየት ይጠቅማል። ሁለቱም ምርጫዎች በስልጣን ላይ በነበሩት አምባገነኖች ተሰርቀው ነበር። ይሁን እንጂ በሰርቢያ የህዝብን ድምጽ ማስከበር ተቻለ። በዝንባቡዌ ግን የህዝብ ድምጽ ማስከበር ሳይቻል ቀርቷል። ስለዚኽ የሁለቱ ምርጫዎች የመጨረሻ ውጤት ሊለያይ ችለዋል። ታሪኩ እንደሚከተለው ነበር፥ በሰርቢያ ተቃዋሚው በመላ አገሪቱ የምርጫ ታዛቢዎች አሰልጥኖ አሰማራ። ህዝቡ ንቅል ብሎ ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ የሚያነሳሳ እና የሚቀሰቅስ የሰላማዊ የምርጫ ሰራዊት አሰልጥኖ በመላ አገሪቱ አዘመተ። መንግስት ድምጽ ቢሰርቅስ ብሎ ቀደም ብሎ በማሰብ ተቃዋሚው ድምጽ ለማስከበር ፕላን ለ (Plan አዘጋጀ። አንድ መንግስት የህዝብ ድምጽ አላከብርም ካለ ህዝቡም በበኩሉ ለመንግስት የለገሰውን ህጋዊነት የመንፈግ መብት እንዳለው የሰላም ትግል ሰራዊት ህዝብን ቀደም ብሎ አስገነዘበ። የምርጫ ድምጽ ማስከበር ወንጀል መፈጸም ሳይሆን መብት ማስከበር እንደሆነ ህዝብን አስተማረ። ስለዚኽ “ፕላን ለ” (Plan ድምጽ ለማስከበር የሚፈጸም የፖለቲካ እምቢታ፣ ትብብር የመንፈግ እና የጣልቃ መግባት ሰላማዊ ትግል ዝግጅት ነው። በየምርጫ ጣቢያው የተመደቡ የተቃዋሚ ታዛቢዎች በድምጽ ቆጠራው ላይ በንቃት በመሳተፍ ቆጠራው እንዳለቀ በዚያው ምሽት ውጤት በየምርጫ ጣቢያው ይፋ እንዲሆን አስደረጉ። በየምርጫ ጣቢያው መራጩ ህዝብም ድምጹን እግዚአብሔር እንዲጠብቅለት ጥሎ ወደ ቤቱ አልሄደም ነበር። በየምርጫ ጣቢያው ደጃፍ በስነስርዓት ተሰልፎ ይጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ በሞሊሶቪች ይመራ የነበረው አምባገናንዊ መንግስት የምርጫው ውጤት እንደፈለገው ሳይሆን መቅረቱን ሲገነዘብ አይኑን በጨው አጥቦ አሸንፌያለሁ ቢልም አድማጭ ሳያገኝ ቀረ። በምርጫው እለት ምሽት በየምርጫ ጣቢያው የምርጫ ውጤት ይፋ ተደርጎ ስለነበር እና ህዝቡ ውጤቱን በዚያው ምሽት እና ለሊት እዲያውቅ ተድርጎ ስለነበር በምላሹ ህዝቡ “ድምጽ ይከበር” አለ። ተቃዋሚው ቀደም ብሎ ያዘጋጀውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሰላማዊ የምርጫ ሰራዊት አንቀሳቀሰ። ይኽ ሰላማዊ ሰልፈኛ “ድምጽ ይከበር” በማለት ፓርላማውን ያዘ። ወታደሩ እና የፖሊስ ኃይል በምርጫ ፖለቲካ እንዳይገባ ተቃዋሚው ቀደም ብሎ ብዙ ህጋዊ ስራ በመሰራቱ እና በተጨማሪ ድምጽ ለማስከበር በዋና ከተማዋ ቤልግሬድ እና በሌሎች ከተሞች አደባባይ የወጣው ህዝብ የሞልሶቪችን የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ስላደረቀው የጦር እና የፖሊስ ኃይል ጣልቃ ከመግባት ተቆጠቡ። በዚህ አይነት ነበር በ2000 ዓመተ ምህርተ የመንግስት ስልጣን 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ አካተተው አሸናፊ ህብረት (ግንባር) የተሸጋገረው። በሰርቢያ ነፃ መርጫ የተደረገው መቼ እንደነበር ታውቃላችሁን? በሰርቢያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ ምርጫ የተደረገው በሰላማዊ ሽግግር ስልጣን የተረከበው የተቃዋሚዎች ህብረት 3 ወይንም 4 አመቶች በህብረት ሰርቢያን ከገዛ በኋላ በ2003 ወይንም በ2004 ዓመተ ምህረት ምርጫ ሲጠራ ነበር። በኢትዮጵያም በህውሃት/ኢህአዴግ ስር ነፃ ምርጫ ሊኖር ይችላል የሚል እምነት ሊኖረን ፍጹም አይገባም። እርም እናውጣ። ነፃ ባለሆነ ምርጫ ተሳትፈን አሸናፊ ሆነን ለመውጣት ነው መዘጋጀት ያለብን። የሚያስፈልገው ዝግጅት ሁሉ ቀደም ብሎ መደረግ አለበት። በየምክንያቱ እያኮረፍን እና ምክንያት እየፈጠረን በምርጫ አንሳተፍም የምንል ከሆነ ምኑን በአምባገነን አገሮች ውስጥ የሚታገል የምርጫ ፓርቲ ሆነን። ህውሃት/ኢህአዴግ ከምርጫው የሚፈልገው የምርጫውን ሃቀኛ መሆን ሳይሆን አሸነፈ መባልን ነው። ድምጽ ሰርቆም ሆነ ተቃዋሚው አኩርፎ ከምርጫ እራሱን ቢያገል ለህውሃት/ኢህአዴግ ልዩነት የለውም። እንዲያውም የተቃዋሚው አለመሳተፍ ህጋዊነትን ለማግኘት ስራውን ያቃልለታል። እስቲ በ2002 የዝንባቡዌን ሁኔታ እንመልከት። በዝንባቡዌ ተቃዋሚው ፓርቲ ደጋፊዎቹ በብዛት ወጥተው እንዲመርጡ በማድረግ እና በተቻለ መጠን ምርጫው ጥቂት የነፃ እና የፍትሃዊ ባህሪዎች እንዲይዝ አለም አቀፍ ህብረተሰብ በሙጋቤ አምባገነን መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳርፍ በማድረግ ረገድ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ምርጫውን ከሙጋቤ መንግስት ስርቆት የሚያድን “ፕላን ለ” (Plan ግን ቸል ብሎ ነበር። የሙጋቤ መንግስት በምርጫ ሽንፈት ቢደርስበት ስልጣን እንደማይለቅ የሚጠቁሙ ምልክቶች ቀደም ብለውም ይታዩ ነበር። በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች እና ፓርቲ ሰራተኞች ላይ ወከባዎች፣ ድብደባዎች፣ ግድያ፣ ማሳደድ እና እስር ቤት የማጎር ተግባራት ይፈጸሙ ነበር። በምርጫው ቀን ሳይቀር አለም አቀፍ ታዛቢዮች እየተመለከቱ ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ዜጎች ይደበደቡ ነበር። ፖሊስ፣ ደህንነት፣ የጦር ኃይል፣ ካድሬ፣ ሚሊሺያ፣ እና በገንዘብ የተገዙ ቦዘኔዎች ሳይቀሩ በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ አረመኔያዊ ተግባሮች ሲፈጽሙ ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲ የመረጡ ብዙ ዜጎች ለህይወታቸው በመፍራት መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደዱ። ምርጫ ለመታዘብ ከአውሮፓ ተጋብዘው ከመጡት ውስጥ ምርጫው ሳያልቅ አገር ለቀው እንዲወጡ የተደረጉም ነበሩ። ባጭሩ ምርጫው እንደሚሰረቅ የሚናገሩ ብዙ ምልክቶች ነበሩ። ሆኖም ግን ተቃዋሚው ፓርቲ እንደ ሰርቢያዎች ፕላን ለ (Plan አልነበረውም። የዝምባቡዌው ሙጋቤ እንደ ሰርቢያው ሞሊሶቪች አይኑን በጨው አጥቦ በምርጫው አሸናፊ መሆኑን አወጀ። የሞሊሶቪች አዋጅ ተቀባይ እንዳጣ አይተናል። የሙጋቤ አዋጅ ግን ተቀባይ አላጣም። ምክንያቱም ተቃዋሚው ፓርቲ ምርጫውን ከሙጋቤ ስርቆት ማዳን ባለመቻሉ። ተቃዋሚው ምርጫውን ከመሰረቅ ማዳን ስላልቻለ የሙጋቤን በጎ ፈቃደኛነት የሚጠይቁ “ምርጫው ነፃ አይደለም፣ ድምጽ ይጣራ፣ ሌላ ምርጫ ይደረግ” የሚሉ ፋይዳ ቢስ ጩኸቶች ከማሰማት ባሻገር ተቃዋሚው ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር። እርግጥ የምዕራቡ አለም በዝንባቡዌ ላይ ጥቅም ስለነበረው እና ይህን ጠቅም ዪሚያስጠብቅለት የሻንግራይ ተቃዋሚ ፓርት ብቻ በመሆኑ በሙጋቤ ላይ ያልተቋረጣ ጫና እና ሽምግልና በማድረግ የህብረት መንግስት እንዲመሰረት አድርጓል። በኢትዮጵያ ግን ህውሃት/ኢህአዴግ እንደሙጋቤ በምዕራቡ የተጠላ ስላልሆነና የምዕራቡን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ቋሚ ደንበኛቸው በመሆኑ ምዕራቡ የዝንባቡዌን ተቃዋሚ የደገፈውን ያህል የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ሊደግፍ ይችላል ብሎ መገመት ተላላነት ነው። የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ነፃ በልሆነ ምርጫ ተሳትፈው አሸናፊ ሆነው መውጣት ብቻ ነው ያላቸው አስተማማኝ አማራጭ። እንደ ሰርቢያ “ፕላን ለ” (Plan ያስፈልገዋል በኢትዮጵያ የሚደረግ ምርጫ። የግድ! በምርጫ አለመሳተፍ የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት እናደርገዋለን የሚለውን ግባችንን ህውሃት/ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ባለቤትነቱ እንዲቀጥል እናደርጋለን በሚል አዲስ ግብ እንደመለወጥ ያህል ነው። (3) ሰላማዊ ማስገደድ እና ሰላማዊ መፈረካከስ/መበታተን፥ አምባገነን መንግስትን ማስገደድ የሚችል ሰላማዊ ትግል ከተገነባ የአምባገነናዊ መንግስት አቅም እጅግ ዝቅ ብሏል ማለት ነው። በአንጻሩ የዲሞክራሲ ኃይሎች የፖለቲካ ኃይል ከፍ ብሏል ማለት ነው። ጉልህ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ግንኙነት ሽግሽግ ተደርጓል ማለት ነው። የሆነው ሆኖ የገዢውን ቡድን ህልውና ላይ ስጋት የሚያሳድሩ አስገዳጅ ጥያቄዎች ከመቅረባቸው በፊት ግን ተቃዋሚው ጥንቃቄ የተሞላበት ፕላን መቀየስ እና ሰፊ የአቅም ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል። ተፈጻሚ ሊሆኑ የማይችሉ አስገዳጅ ጥያቄዎች ማቅረብ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያሳጣል። የፕላን አለመጠናቀቅ ወይንም የትግል አቅም ማነስ ካለ አስገዳጅ ጥያቄዎችን ከማቅረብ መቆጠብ ወይንም አኪያሄድን ማስተካከል ይመረጣል። በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን መንግስት የቀረበለትን አስገዳጅ የለውጥ ጥያቄ ፈቃደኛ ሳይሆን ተገዶ ከተቀበለ ማስገደድ ተሳካ ሊባል ይችላል። የሰርቢያን እና የዝምባቡዌን ሁኔታዎች ደግመን እንመልከት። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 አመተ ምህረት በሰርቢያ በተደረገው ምርጫ ተቃዋሚው ድል አድራጊነቱን ያወጀው በስልጣን ላይ የነበረው የሞሊሶቪች መንግስት ምርጫው መደገም እንዳለበት በመደፋንት ላይ ሳለ ነበር። ምርጫው ሊሰረቅ እንደሚችል በቅድሚያ በመገመት ተቃዋሚው ስልጣን በሰላማዊ ትግል ለመረከብ ዝርዝር ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ከፍ ብሎ አንብበናል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር “የህዝብ ድምጽ አስከባሪ ሰላማዊ ሰራዊት” ወደ ፓርላማ ሲያመራ የስርቢያ ፖሊስ እና የጦር ኃይል በምርጫ ፖለቲካ ጣልቃ አንገባም በማለታቸው የሞሊሶቪች መንግስት ሁለት ቁልፍ የድጋፍ ምሶሶዎች (Pillars of support) አጣ። በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኛ (ቢሮክራሲ) እና ሌሎች ሰራተኞች ስራ በማቆማቸው ተጨማሪ የመንግስት የፖለቲካ ኃይል ምንጭ አደረቁ። ስለዚህ ሞሊሲቪች ሽንፈትን በሰላማዊ ትግል ተገዶ ተቀበለ። በ2002 አመተ ምህረት በዝንባቡዌ እንደደረሰው በቂ ዝግጅት እና አቅም ሳይኖር ለማስፈራራት ያህል የሚጠሩ አጣቃላይ ስራ የማቆም አድማዎች እና የመሳሰሉት ሰላማዊ አስገዳጅ እርምጃዎች የሰላም ትግሉን ይጎዳሉ። በዝንባቡዌ ሁለት አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማዎች በተቃዋሚው ፓርቲ ተጠርተው ነበር። ሁለቱም አልተሳኩም። እንደዚህ አይነት ስህተት የሰላማዊን ትግል አቅም ያባክናል። ንቁ የህዝብ ድጋፍ ይቀንሳል። ስለዚህ የመንግስትን የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ለማድረቅ የሚጠራ አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ (ሰላማዊ ትግል) ከመጠራቱ በፊት በቂ ዝግጅት መደረግ እና ትግሉ በቀጣይነት ሊጓዝ የሚያስችለው አቅም መገንባቱ በቅድሚያ መረጋገጥ ነበረበት። የማይሳካ ትብብር የመንፈግ ትግል ጥሪ መደረግ የለበትም።

No comments:

Post a Comment