November 7, 2013 የወያኔ ገዢ ጉጅሌ በባህርዩ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አጋጥሟት የማያውቅ ፍጹም ኢሰብዓዊና ነውረኛ ስብስብ እንደሆነ ለመረዳት ኢትዮጵያዊያንን ለማዋረድ የሚጠቀሟቸውን ተግባራትና ቃላትን ማጤን ይበቃል።
በሶማሌ ክልል የኦብነግን ታጣቂዎች ቅስም ለመስበር ልጃገረዶችንና እናቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ጭምር በቤተሰብ ፊት በደቦ የሚደፍሩ፤ ለዚህ ተግባር የሠለጠኑ የልዩ ጦር አባላት መኖራቸው በስፋት የሚታወቅና በተደጋጋሚም የተዘገበ ጉዳይ ነው። ወያኔ፣ የኦጋዴን ወገኖቻችን በዚህ ጥቃት ተሸማቀው ያነገቡትን መሣሪያ ጥለው ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዛሉ ብሎ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ዛሬ የሶማሌ ክልል ወንዱም ሴቱም፤ ወጣቱም አዛውንቱም በፀረ-ወያኔ አቋም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል። በኦጋዴን የወያኔ አስነዋሪ ጥቃት የፈጠረው ምሬት በውጭ አገራትም በሚደረጉ የፀረ ወያኔ ትግሎች የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ተሳትፎ እንዲጎለብት አድርጎታል። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በአፋር ክልልም ተመሳሳይ ጥቃት የዘወትር ትዕይንት እየሆነ መጥቷል። የአፋር የወል የግጦሽ መሬቶች ለሸኮራ አገዳ ልማት በሚል ሰበብ ሲነጠቁ የተቃወሙ የአገር ሽማግሌዎች ተደብድበዋል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተደፍረዋል። በአፋርም ውስጥ ለጾታዊ ጥቃት የሰለጠነ የወያኔ ልዩ ጦር ተሰማርቶ በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ አስነዋሪ ጥቃት አድርሷል። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በጋምቤላ ውስጥ ወያኔ ወገኖቻችን ከፈጀ በኋላ በሕይወት የተረፉትም ቅስማቸውን ለመስበር ጾታዊ ጥቃት በመሣሪያነት ተጠቅሟል፤ አሁንም እየተጠቀመ ነው። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
የወያኔ ዝቅጠት ዘግናኝ ነው። ወያኔ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ያላደረሰበት የአገራችን ክፍል የለም። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል … በሁሉም ቦታዎች ያልተነገሩ ጥቃቶች በዜጎታችን ላይ ደርሷል፤ እየደረሰም ነው።
በአንድ ወቅት በመሀል አገር፤ በሰሜን ሸዋ አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በእብሪተኛ ወያኔ የተገደለውን ባለቤትዋን ብልት ይዛ አስክሬኑን እንድትጎትት መደረጉን ከዓይን እማኞች አንደበት ሰምተናል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰበብ መስዋዕትነት እየተቀበሉ ያሉ ወገኖቻችን “ሽንታም አማራ” እየተባሉ ብልቶቻቸው ይቀጠቀጥ እንደነበር የሰማነው እና የምናውቀው ጉዳይ ነው። በወያኔ መዳፍ ውስጥ ውስጥ ገብተው በእስር ቤቶች በሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ዘግናኝ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መረጃዎች አሉ። በአዲስ አበባ በየቦታው ባሉት ስውር የማሰቃያ ቤቶችም ተመሳሳይ ተግባራት ዘወትር እንደሚፈፀሙ ይታወቃል።
ወያኔ ለጾታዊ ጥቃት ያሰለጠናቸው ሰዎችን በከተሞችም ውስጥ አሰማርቷል። በእነዚህ ጥቃቶች ግለሰቦች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ቢሆንም የተደፈርነው፣ የተዋረድነው ሁላችንም መሆናችን አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። የተደፈርነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነን። የተዋረደችው የምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ አገራችን እፍረት ባልፈጠረባቸው ነውረኛ የወያኔ ዋልጌዎች እንድትገዛ እንድትረገጥ በመፍቀዳችን ጥፋቱ የኛም ጭምር ነው። ይህን ነውረኛ ቡድን በሥልጣን ላይ እንዲቆይ በፈቀድንለት መጠን በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያችን ላይ የሚደርሰው በደል እየባሰ እንደሚመጣ በዓይኖቻችን እያየን በጆሮዎቻችን እየሰማን ነው።
ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ላይ የደረሰው ጥቃት የዚሁ አካል ነው። እኚህ ወገናችን የደረሰባቸውን ዘርዝሮ ለመናገር የሚከብድ መሆኑ ገልፀዋል። ማፈር የነበረባቸው ጥቃት አድራሾቹ መሆን ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ግን ይሉኝታ አልፈጠረባቸው። ምንም ይሁን ምን በወገናችን ላይ የደረሰው ጥቃት በእሳቸው ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን በሁላችንም ላይ የደረሰ መስሎ የሚሰማን መሆኑን ልንነግራቸው እንወዳለን። የተዋረደችው ኢትዮጵያ አገራችን ነች።
ይህ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔ ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ” ቀዳሚ ሥራችን ነው የሚለው ኢትዮጵያን ለማዳን ከዚህ የሚበልጥ አንገብጋቢና አጣዳፊ ሥራ ስለሌለ ነው። ወያኔን ለማስወገድ እንተባበር።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment