Saturday, March 1, 2014

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሰላኝ ከእውቀት እና እውነት ጋር የሚጋጭ ትንተና ለምን? ግርማ ሠይፉ ማሩ


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቅረቡ ወደ ሚዲያ የመጡት የኤርትራው ወዲ ኢሳያስ አፈወርቂ በሚዲያ ቀርበው አንድ አንድ ነገር በማለታቸው፤ ከማን እናንሳለን በሚል ነው የሚሉ ሰዎች ጋር መስማማት የለብንም፡፡ አጋጣሚ ነው ብለን ማለፍ ካልፈለግን አጋጣሚ ባይሆንም አጋጣሚውን ለእኛም እንድ አንድ “እውቀት” የሚጨምር ነገር ልናገኝበት የምንችል አጋጣሚ አድርጎ መውስድ ግድ ይለናል፡፡ እውቀት የሚለውን ነገር ግን ልብ ልንለው የሚገባ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ ተከትሎ ብዙ አስተያየት የተሰጠ ቢሆንም፣ የግል ዕይታዬን ማካፈል የተደጋገመ ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ አመንኩ፡፡ ምክንያቱም በመሬት ላይ ካለና ከምናየው እውነትና እውቀት ጋር የተጋጨ ስለመሰለኝ፡፡
የቡድን አመራርን በተመለከተ
የቡድን አመራር ነው ለሃያ ዓመት በፓርቲያችን ያለው ማለት አቶ መለስ እያሉም አመራር ላይ ነበርን ሊሉን ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ከህወሃት ክፍፍል በፊት (እነ ሰዬ፣ ገብሩ፣ ተወልድ፣ ወዘተ) በሚመክሩበት አጀንዳ እኛም ነበርን ሊሉን አይችሉም፡፡ በዚያን ጊዜ የቡድን አመራር በህወሃት ውስጥ እንደ ነበር እናውቃለን፣ ይህ በኢህዴግ ውስጥም ዘልቆ ገብቶ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንም አንድ አንድ የህወሃት ሰዎች በየክልሉ ተቀምጠው የህወሃት ውሳኔ ያስፈፅሙ ነበር፡፡ ከህወሃት ክፍፍል በኋላ ነገሮች እንደተቀየሩ እሙን ነው፡፡ ከህወሃት የቡድን አገዛዝነት ወደ አቶ መለስ ዜናው እጅ ስልጣን ተጠቃሎ ነው የገባው፡፡ ለዚህም ነው አቶ መለስ ዜናዊን “ጠቅላይ” የሚባሉት፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ቦታውን ከያዙት በኋላ በጠቅላይነት የሚያማቸው የለም፡፡ እንደ እኔ ዓይነቱ ወደ ቡድን አሰራር ገብተዋል የሚል ግምት የያዝን አለን፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደቀድሞ ቦታ ተመልስው ህወሃት ነው ከጀርባ ሆኖ ማርሽ የሚቀይረው ብለው ይጠራጠራሉ፡፡ እንዲህ ያለህ የተምታታ ግምት ስለአለ ነው በዘዴ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ነዎት?የሚል ሽንቋጭ ጥያቄ ያስነሳው፡፡
ኢህአዴግ በግልፅ እንደሚናገረው ተግባራዊ ነገር አድርጊያለሁ ብሎ የሚያምነው ከተሃድሶ በኋላ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከተሃድሶ በኋላ ደግሞ አቶ መለስ ጠቅላይ የነበሩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ኃይለማሪያምም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሹመት እንጂ ስልጣን አልነበራችሁም፡፡ ለምሳሌ አቶ ኃይለማሪያም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ጠቅላዩ የነበራቸው መረጃ በሙሉ ነበረኝ ምክንያቱም የቡድን አመራር ስለምንከትል ብለው አይዋሹኑም፡፡ ቢሉም በፍፁም አናምኖትም፡፡ በዚያ ደረጃ ተተኪ ልሆን እችላለሁ ብለው ዝግጅት እንዳልነበሮት የሚያሳብቀው እውነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት ቦታውን ሲይዙ ከሚሰጡት መግለጫ ለመረዳት የሚቻል ነበር፡፡ ለማነኛውም በቅጡ የኢህአዴግ የቡድን አመራር እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ወሳኝ ስብዕና ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቅ መሆኑን ተረድተው የቡድንም የግለሰብም ወሳኝነት ተመጣጥነው የሚሄዱበት መስመር የግድ እንደሚል ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአሜሪካው ፕሬዝደንት በግላቸው እንደፈለጋቸው አይወስኑም፡፡ ይህን ለመረዳት ቢንላደንን ለመያዝ የተደረገውን ዘመቻ እንዴት በቡድን እና እንዴት በግል ኃላፊነት ወስደው እንደወሰኑ የሚያሳየውን ፊልም ይመልከቱት፡፡
ቴሌ እና የሚታለብ ላም
ይህን በተመለከት ዶክትር ካሱ ኢላላ ብለውት እስከ ዛሬ ድረስ ካደረጉት ስህተት እንደ አንዱ የሚቆጠር የነበረ ነው፡፡ ኢህአዴግ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም የሚለውን በሚያጠናክር ሁኔታ ቃል በቃል ሲደግሙት በግሌ አዝኛለሁ፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ቴሌ “በመንግሰት እጅም” ሆኖ አትራፊ ነው፡፡ ቴሌ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነገሩን መረጃ መሰረት በመንግሰት እጅ ሆኖ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለልማት ያውላል ብለውናል፡፡ ያልገባቸው ነገር ግን ቴሌ በግል ይዞታ ቢሆንም ከዚህ ሶሰት እጥፍ የሚሆን ትርፍ ሊያተርፍ እንደሚችል ነው፡፡ ከዚህ ትርፍም መንግሰት ድርሻውን ያገኛል፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር ያለው ችግር የልማት ባለቤት ህዝብ ይሁን ወይስ መንግሰት የሚለው ነው፡፡ የግል ባለይዞታዎች ከቴሌ ትርፍ ካተረፉ የብር ኖት አይበሉም መልሰው አዋጭ ነው ብለው ባሉት መስመር ኢንቨስት ያደርጉታል፡፡ ምን አልባትም ከመንግሰት በተሻለ አዋጭ መስመር ነው ስራ ላይ የሚያውሉት፡፡ ለዚህ ጉልዕ ምሰሌ በመንግሰት እጅ የሚገኙ የነበሩትን የቢራ ፋብሪካዎች አሁን ለመንግሰት እየከፈሉ ያሉትን ታክስና በኢኮኖሚ ውስጥ እየፈጠሩ ያሉትን መነቃቃት ነው፡፡ እነዚህ ተቋሞች በመንግሰት እጅም እያሉ አትራፊ ነበሩ፤ አሁን ግን የበለጠ አትራፊ ናቸው፡፡
በዋነኝነት የቴሌ በመንግሰት እጅ መቆየት የሚፈለገው ለልማት ካለው ፋይዳ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ በስልጣን ለመቆየት ግን እንዲህ ያለን ህዝቦችን የሚያስተሳሰር ቴክኖሎጂ በግለሰብ እጅ አስገብቶ የነፃነት በር ሆኖ እንዲያገለግል አይፈለግም፡፡ ለሃምሳ ዓመት መግዛት የሚፈልግ ፓርቲ በዚህ ደረጃ ወርዶ ለማፈን ቢሞክር ባህሪው ነው ብሎ መውሰድ ነው፡፡ በልማት ስም በተለይ ለገጠሩ ህዝብ ለማስፋፋት ብለው ሰበብ ከሰጡ በኋላ ግን የቴሌ ገንዘብ ለባቡር መስመር ዝርጋታ እየዋለ ነው ብለው የገጠሩን ህዝብ ለመጠቀሚያ ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡ የቴሌው የህዝብ ግንኙነት በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሁን በተያዘው ማስፋፊያ 85 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ክፍል በኔትወርክ ይሸፈናል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ጠቅላላ ሀገሪቱን ለመሸፈን የቀረው ጥቂት ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን
ግርማ ሠይፉ ማሩ
ከመንግሰት በተሸለ ጥራት ለሚሰጡ የግል ድርጅት አስተላልፉ፣ መንግሰት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያና ቁጥጥር ላይ ለምን አይገባም
የሚለው መከራከሪያ አሁንም ለፊት ለፊት ጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ እንጂ ይህ ሊሆን የሚችለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ
መቃብር ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይዘገይ ይሆናል እንጂ ይህ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ማለትም አብዮታዊ ዲሞክራሲ
አስተሳሰብ ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡
እዚህ ጋ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር የግል ባለሀብቱን ስብሰባ እየጠሩ የግሉ ዘርፍ ምትክ የሌለው እንደሆነ እናምናለን፤ ከግል ዘርፉ ጋር ጠብ የለንም የሚል መንግሰት ጠቅላይ ሚኒስትር “መንግሰት ብቻ ነው ይህን ትርፍ ለልማት የሚያውለው” ማለት እንዴት ያለ ተቃርኖ እንደሆነ ነው፡፡ በግለሰቦች (ሲደመሩ ህዝብ የሚሆኑት) እምነት የሌለው መንግሰት፤ የህዝብ ወኪል የሚሆን አይደለም፡፡ በህዝብ ስም ግን ይነግዳል፡፡ መንግሰት ብቻ ነው የሚያለማው የሚለውን ከወሰድን የአሜሪካ መንግሰት ከመከላከያ እና ከተወሰኑ ፓርኮች በስተቀር የመንግሰት የሚባል ነገር የለውም፡፡ በአሜሪካ ልማት የለም በቻይና ነው ያለው እንደማይሉ ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡ ብዙ ሰው ቻይና ከአሜሪካ ቀጥሎ ግዙፉ ኢኮኖሚ እያሉ ሲሳሳቱ አሜሪካ ቻይናን 10 ዕጥፍ እንደምትበልጣት የምናውቅ አይመስላቸውም፡፡ ቻይና ከጃፓን በለጠች እንጂ አሜሪካ ጋር አልደረሰችም፡፡ ይህችን እንደ እግረ መንገድ ያዙልኝ፡፡ እርግጥ ነው የቻይና መንግሰት ሀብታም ነው፣ ህዝቡ ግን ድሃ፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍናው መንግሰት ብቻ ነው የሚያለማው የሚል እና የኛዎቹም ቅጂያቸው እንደዚያ ስለሆነ ነው፡፡ ሰትራቴጂው ገጠሩን እዚያው ገጠር ለማሰቀረት እቅድ ከሌለ በስተቀር የገጠሩ ህዝብ አሁን የሚፈልገው ስልክ እና መብራት ይዛችሁለት በጫካ ስር መኖር ሳይሆን ከተሜነት ነው፡፡ ወደ ስልኩ እና መሰረተ ልማቱ መምጣት ይኖርበታል፡፡
የታክስ ምጣኔ እና የታክስ መሰረት ማሰፋት
ግብር በማይከፈልበት የቦርድ ክፍያ እና ሌሎች ገቢዎች ለሚደጎም ባለስልጣን ብዙ ግልፅ ያልሆነ ግን ደሞዝተኛውን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ያለው ከፍተኛ ታክስ የሚከፈልበት የደሞዝ ጣሪያ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆኑ ነው፡፡ በጋዜጠኞች የቀረበውም ጥያቄ ይህን የሚመለከት እንጂ አጠቃላይ የታክስ ሪፎርም እየተባለ ለረዥም ጊዜ የተያዘ የተሰፋ ፕሮጀክት ምንደረሰ የሚል አይደለም፡፡ ደሞዝተኛውን ደሞዝ ጨመርንልህ ብሎ በግብር ከመቀማት በተግባር የታክስ ምጣኔውን ማስተካከል የዘገየ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን የስራ ተነሳሸነት እየገደለ ያለ በምድር ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ጨመረ ብሎ በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ የሚጨምር ፣ ይህንንም ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያደርግ መንግስት በቀጥታ ከደሞዝተኛ ላይ የደሞዝ መቀነስ እንደሆነ መረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ሲቪል ሰራተኞች የመነሻ ደሞዝ ከፍ ማድረግ (ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን መወሰን) እና የግብር ማሰከፈያውን የገቢ መጠን ከፍ ማድረግ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዜጎች የሚያገኙትን ገቢ እየተከታተለ የሚቀማቸውን አይፈልጉም፡፡ መንግሰትም ቢሆን፡፡ በታክሰና ግብር ስም እየቀሙ እኔ ለልማት አውለዋለሁ ማለት ከስድብ አይተናነሰም፤ ዜጎችም ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለልማት ለዚያውም ለዘላቂ ልማት ነው የሚያውልቱ፡፡ ከዜጎቹ እየቀማ ዜጎችን በማደኽየት የሚበለፅግ መንግሰት ልማታዊ ነኝ ሊል አይችልም፡፡
ሊስትሮም ሁን ብባል ወረዳም ሂድ ከተባልኩ አደርጋዋለሁ፤
ሊስትሮም ሁን ብባል ወረዳም ሂድ ከተባልኩ የምሄድ ወታደር ነኝ፡፡ ይህ አባባል በኢህአዴግ ሰፈር የግል ነፃነት ስለሌለ ምን ያህል እውቀት እንደሚባክን ነው የሚያሳየው፡፡ ልክ ነው በሚቀጥለው ዙር ወደ ክልል ቢባሉ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ አሁኑ በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ማዕረግ የሚያገለግሉት ቱባ ባለስልጣን ወደ ክልል ብሎም ወደ ዞን ሲላኩ እሺ ብለው መሄዳቸው የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ ከክልል ፕሬዝደንትነት ወደ ጠቅላይ ሚኒሰትረ አማካሪነት ተመሳሳይ የምደባ ዝውውር ነው፡፡ ይህ ግን በምንም ምክንያት ተገቢ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ቅዱስ መፅሐፍ ምሳሌ 4፡18 “የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው፤ ሙሉ ቀን እሲከሆን ድረሰም እየጨመረ ይበራል” ይላል፡፡ ምን ነው የኛ መሪዎች ቁልቁል ማየት ፈለጋችሁ፡፡ የሌሎች ሀገር መሪዎች ከመሪነት ሲለቁ ተከታይ ቦታቸው ሊሰትሮ መሆን ወይም የእርሱ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አማካሪነት ነው፡፡ ዛሬ ክሊንተን አንድ ሰዓት ንግግር አድርገው የሚያገኙት ገንዘብ ከወረዳ በጀት በስንት እጥፍ እንደሚልቅ ነጋሪ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይህን ብቃት አረጋግጫለሁ ያለ ሰው ወረዳ ለመሄድ አያስብም፡፡ በምደባ የተገኘ ስልጣን ግን በምደባ ሊነሳ ይሚችል ነው፡፡ በምደባ ከሚገኝ ስልጣን ያድነን፡፡ እኔ ግን ከዚህም በላይ የገባኝ፣ የጋራ አመራር አለ ብሎ ከግል ተጠያቂነት ለመሽሽ እንዳይሆን የሚል ፍርሃትም አለኝ፡፡ ሌላው ግን አብዛኛው ሹመኛ ነገ ወረዳ ልወረወር እቻላለሁ በሚል ስጋት ተግቶ በዘረፋ ይሰማራል፡፡ የብቃት ከግምት መውጣትና የምደባ ሹመት የሚያመጣው ጣጣ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለዛሬ ይብቃን ቸር ይግጠመን፡፡
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

2 comments:

  1. An excerpt from the book "The collusion on Eritrea"
    by Bocresion Haile (an Eritrean)

    - As part of the Italian colonial military, almost 4000 Eritrean Askaris were constantly kept in Libya, 800 in Somalia, 6606 Eritreans fought in Adwa against Ethiopia.
    ከፍ ሲል ቦክረጽዮን በመጽሐፉ እንደገለጸው በድምሩ 11406 ኤርትራውያን ባንዳዎች በቅኝ ገዣቸው ሠልጥነው ከጣሊያን ጦር ጋር ሊቢያን፣ ሶማሊያንና ኢትዮጵያን እንዲወጉ ዘምተዋል፡፡ አፄ ምኒልክ አደዋ ያዘመቱት ጦር ብዛት 60 ሺህ ቢሆን ይህንን ጦር ለመውጋት በጣሊያን ሠልጥነው ወደ አደዋ የዘመቱት ባንዳ ኤርትራውያን ደግሞ 6066 ሲሆኑ ይህም ከኢትዮጵያ ጦር 10.1% ያህል የሚሆን ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው አሁን ያዙን ልቀቁን የሚሉት የባንዳ ልጆች አባቶቻቸው ኢትዮጵያውያንን ለመውጋት ወደ አደዋ በመዝመታቸው አያፍሩም፡፡ ለምንስ በወራሪያችው ጣሊያን ላይ አላመጹም፣በጣም ያስደንቃል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም, ቦክረጽዮን በመቀጠልም እንዲህ ብሎናል -During the 1935 to 1936 war with Ethiopia, the Italians forced their Eritrean troops to bury dead Italians but not their own dead brothers. ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ እንዲሉ ዛሬ የባንደዎቹ ልጆችና የልጅ ልጆች በምኒልክ የሚያመካኙት እነርሱስ በጣሊያን አንገዛም ብለው ያመፁበት አጋጣሚ ነበርን፣ አለ የሚል ካለ እስቲ በማስረጃ የተደገፈ፣ ገጽ ጠቅሶ ይቅርብና እንወያይ፡፡ Wekipedia, the free Encyclopedia, Italian Eriteria ብሎ የጻፈውን እንመልከት፡፡

    The Italian-Eritrean community then grew from around 4,000 during World War I to nearly 100,000 at the beginning of World War II. …. By the early 1940s, Catholicism was the declared religion of around 28% of the colony's population.
    Source: Bandini, Franco. Gli italiani in Africa, storia delle guerre coloniali
    1882-1943, "Eritrea". Template:It-icon
    "Italian emigration to Eritrea". Template:It-icon
    ልብ በሉ እንግዲህ፣ ኤርትራውን ለጣሊዮኖች ምን ያህል ምቹ ተገዥ እንደነበሩና የጣሊያኖችም ቁጥር ከ4ሺ በአጭር ጊዜ 100ሺህ እንደደረሰ፡፡ የምኒልክ ጦር ወደ ኤርትራ ያልዘመተበት በቂ ምክንያት እንደነበረው በብዙ ምሁራን ተጽፎ ይገኛል፡፡ ተላላኪያቸው ወያኔና ተከታዮቹ ግን ዘወትር ምኒልክን እንደወቀሱ ነው፡፡ ባለቤት ካልጮኸ እኮ ጎረቤት አይደርስም፡፡ ለምን እነ ራስ መንገሻ ትግራይን አናስይዝም ብለው አምጸው ድረሱልን አሉ፡፡ አዲስ አበባስ እሩቅ ነው እንበል፣ ለምን ከ6606 ባንዳዎቻቸው መካከል መቶ ወይም አንድ ሺህ የለም እኔ በጣሊያን አልገዛም ብሎ ከትግራይ ወንድሞቹ ጋር አልተቀላቀለም፡፡ ይህ እንዳይደረገም ምኒልክ ከለከሉአቸው እንዴ፣ Shame on Bandits and their children, who are trying to steal antiquity. History will be more kinder to mperor Menelik than the Woyanes, who betray Ethiopia and the people.

    ReplyDelete