በጅጅጋ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ከነበሩ ቁጥራቸው በውል ከማይታወቅ እስረኞች መካከል 300 ያክሉ ከአራት ቀናት በፊት በጅጅጋ መንገድ ላይ መጣላቸው ታውቀ።
የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ያላከውን መረጃ በመንተራስ ኢሳት ባደረገው ማጣራት፣ ባለፈው ሃሙስ ለአርብ አጥቢያ አካላቸው በምግብ እጦት የከሳ፣ አይናቸው የታወረ፣ እግሮቻቸው ሽባ የሆኑ፣ የአእምሮ መታወክ የደረሰባቸውና አሰቃቂ የእስር ቤት ህይወት እንዳሳለፉ የሚናገሩ እስረኞች በጅጅጋ ጎዳናዎች ላይ ተጥለዋል።
ከተጣሉት መካከል ወላጅ አልባ የሆኑ ምናልባትም በእስር ቤት ውስጥ የተወለዱ ህጻናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ይገኙበታል።
አብዛኞቹ እስረኞች ከሰውነት ተራ የወጡና በበሽታ የተጠቁ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በእስር ቤት ውስጥ የቆዩ ናቸው። ኢሳት ለማረጋገጥ ባይችልም፣ የኦብነግ መረጃ እንደሚያሳየው ከተፈቱት እስረኞች መካከል 20ዎቹ በሶስት ቀናት ውስጥ በበሽታ ሞተዋል።
ከአንድ ወር በፊት ኢሳት ከጅጅጋ ከተማ 25 ኪሜትር ርቆ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በኮሌራ በሽታ ከ40 በላይ ሰዎች ሞተው በእስር ቤቱ አካባቢ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመቀበራቸው አስከሬናቸውን ጅቦች እያወጡ በመብላታቸውና እና አካባቢው በበሽታ በመበከሉ በድጋሜ እንዲቀበሩ መደረጉን ዘግቧል።
የክልሉ መንግስት አሁን የወሰደው እርምጃ በእስር ቤቶች ውስጥ የተነሳውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል እንደሆነ እየተነገረ ነው።
በሶማሌ ክልል የተካሄደውን የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን አስመልክቶ የክልሉን ገጽታ ያበላሻሉ የተባሉ ከ700 በላይ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችና መታወቂያ የሌላቸው ሰዎች እንዲታሰሩ መደረጉ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment