Thursday, August 7, 2014

የደመወዝ ጭማሪው የመንግሥት ሠራተኞችን ቅር አሰኝቷል ተባለ



በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ባለፈው ቅዳሜ መጠኑ ተገልጿል፡፡ ጭማሪው በመዘግየቱና እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆን የመንግሥት ሠራተኞች ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
በ2003 ዓ.ም. በተደረገው ጭማሪ 420 ብር የገባው የመንግሥት ሠራተኞች መነሻ ደመዝ 46.43 በመቶ ጭማሪ ተደርጎለት ከ582 ብር እስከ 700 ብር መስተካከሉ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ ተደርጓል፡፡ መካከለኛ ተከፋይ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች እስከ 36 በመቶ ጭማሪ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከፍተኛ ተከፋዮች ደግሞ በአማካይ 33 በመቶና ከዚያ በታች እንደሚያገኙ ይፋ ተደርጓል፡፡
የደመወዝ ጭማሪውን ይፋ ያደረጉት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ምሥራቅ መኰንን፣ መንግሥት በአጠቃላይ ለጭማሪው በዓመት 10.3 ቢሊዮን ብር ያወጣል ብለዋል፡፡
‹‹መንግሥት ይህንን 10.3 ቢሊዮን ብር ለደመወዝ ሲያወጣ ፕሮጀክቶችን አጥፎ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን፣ ‹‹ከደመወዝ ጭማሪው ውጪ በቀጣዩ ዓመት ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ይቀርባል፡፡ እንዲሁም የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አማራጭ እየተጠና ነው፤›› ብለዋል፡፡
የደመወዝ ጭማሪው በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ይደርሳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ወጥ የሆነና በመላ አገሪቱ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ሠራተኞች የደመወዝ ቀመርን የማዘጋጀቱና ወጥ የሆነ ደረጃ መፍጠሩ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በነሐሴ ወር ደመወዝ ላይ እንደሚካተት ዶ/ር ምሥራቅ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ‹‹ሠራተኛው ከኑሮ ውድነት ጋር የገባውን ግብግብ መንግሥት የተረዳው አይመስለንም፤›› በማለት ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹የዋጋ ጭማሪው መንግሥት ካደረ ገው የደመወዝ ጭማሪ ይበልጣል፤›› በማለትም በምሬት ይገልጻሉ፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚያቀርቡ ቢገልጹም፣ ሠራተኞች ይህ ይሆናል የሚል ተስፋ የላቸውም፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን መንግሥት የሚያወጣው 10.3 ቢሊዮን ብር በጣም ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ባለው የዋጋ ንረት ላይ ከዚህ በላይ ገንዘብ ወደ ገበያው ቢገባ የዋጋ ንረቱ ሊያገረሽ ይችላል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡
በመሆኑም ሁሉንም ኅብረተሰብ ያገናዘበ ጭማሪ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment