Wednesday, January 14, 2015

ከምርጫው በፊት ምርጫ ቦርድ የሚደክምለት አብዩት፤ – ከዳዊት ሰለሞን


አቦጊዳ  
በእርግጥ ምርጫ ቦርድን ለፕሮፌሰር መርጋ በቃና በመስጠት ኢህአዴግን ከጨዋታው ውጪ ማድረግ አይቻልም፡፡ የኢህአዴግ የስልጣን ደም ስር በዚህ ተቋም የተተበተበ በመሆኑ ምርጫ ቦርድን እንደ አንድ ራሱን የቻለ ነጻ ተቋም መቁጠር እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያኑ ቀርቶ ለምዕራባዊያኑም የሚዋጥ አይሆንም፡፡ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ለማሳየት ብዙ ርቀት መጓዝ አይጠበቅም፡፡
በአገሪቱ የተከናወኑ አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫዎች ለሁለቱ ተጋምዶ አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡በኢህአዴግ ኮሮጆ ገልባጭነት ለተደረጉ የምርጫ ማጭበርበሮች ምርጫ ቦርድ ህጋዊነትን እያጎናጸፈ የህዝብ ልጆች ደም በየዓምስት ዓመቱ እንደ ጎርፍ እየወረደ ኢህአዴግ የስልጣን ኮርቻውን እንደተፈናጠጠ አራት ኪሎ ይገኛል፡፡
ለስድስተኛ ጊዜ የሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ከሶስት ያነሱ የወራት ዕድሜዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡ምርጫ ቦርድ የህዝብ ታዛቢዎችን በማስመረጥ የመራጮች የምዝገባ ወረቀት መታደል መጀመሩን ቢገልጽም በገዢውና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ፉክክሩን ክፍት ሊያደርጉ በሚችሉ ጉዳዩች ዙሪያ የመነጋገር ምልክት አይታይም፡፡
ከሁሉ በከፋ መልኩ ምርጫ ቦርድ ድግሱ እንደደረሰለት ቅን ደጋሽ በአምስት ዓመት አንድ ግዜ የሚያገኘውን ዕድል በቻለው መጠን ክፍት፣ነጻና ሁሉን አሳታፊ ማድረግ ሲገባው ለገዢው ቡድን ያለው አጋርነት አቅሉን አስቶት ድግሱን ሊያደምቁ በሚችሉ ፓርቲዎች ላይ የማስፈራሪያ መግለጫዎችን በማስደመጥ ተወጥሯል፡፡
በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ከብዙ ማደናቀፊያዎች ጋር እየታገለ እዚህ የደረሰውን አንድነትን ምርጫ ቦርድ ሰንካላ ምክንያቶችን በማቅረብ በአጭር ግዜ ውስጥ ተደጋጋሚ ጠቅላላ ጉባኤዎችን እንዲያከናውን አስገድዶታል፡፡እውነቱን ለመናገር ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገዋል በማለት የእውቅና ሰርተፊኬት ከሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ምን ያህሉ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገዋል ?ኦዲት ተደርገዋል?ምን ያህሉ አድራሻ አላቸው ?የአባላት ቁጥራቸው ስንት ነው?ስንቶቹስ ፕሬዘዳንት(ሊቀመንበር)ምክትል ፕሬዘዳንት ጸሀፊና የህዝብ ግኑኝነት አላቸው?ለምሳሌ የአየለ ጫሚሶን ቅንጅትን እንውሰድ አቶ አየለ የፓርቲው ሊቀ መንበር፣ ዋና ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ ሲሆኑ የተረከበውን ህገ ወጥ አጠና ደብቆ በመሸጡ ከፖሊስነቱ የተቀነሰው አቶ ሳሳሁልህ የፓርቲው ምክትል ፕሬዘዳንት፣ የህዝብ ግኑኝነትና የሚዲያ ክፍል ሀላፊ ነው፡፡ ቅንጅት የሁለቱ ሰዎች ንብረት ቢሆንም ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤ፣የኦዲትና የስልጣን ክፍፍልን የሚመለከት ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም ከዚህ ይልቅ እነሳሳሁልህ ከምርጫ ቦርድ የተሳትፎም ይሁን የእውቅና ደብዳቤ በማግኘት ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡
ምርጫ ቦርድ በኪሳቸው ማህተማቸውን ይዘው ለሚዞሩ የፓርቲ አመራሮች ያልተደረጉ ጠቅላላ ጉባኤዎችን እንደተደረጉ በመውሰድ የእውቅና ሰርተፊኬት የአመራሮቹ መኖሪያ ቤት ድረስ በፖስተኛ እንደሚልክ ለሚያውቅ ሰው አሁን ደርሶ አንድነትን ሱሪ በአንገት ማለቱ አይደንቀውም፡፡
እነ መርጋ እነዚህን ፓርቲዎች የህልውናቸው ማረጋገጫ በመሆናቸው ይፈልጓቸዋል፡፡ፓርቲዎቹ በእነ መርጋ ድግስ እየተካፈሉ ኢህአዴግ ቢያንስ ምዕራባዊያንን የሚሞግትበትና የዋህንን የሚያስትበትን በር ይከፍቱለታልና ለመኖራቸው፣ለመዋለዳቸው ተግቶ ይሰራል፡፡በአንጻሩ ኢህአዴግ ፖሊሲ የሚቀርጽ፣ስትራቴጂ የሚነድፍ፣ፕሮግራም የሚያወጣ፣አባላቱን ለማብዛት በመላ አገሪቱ እግሩን ለመትከል የሚታትር እንደ አንድነት ያለ ፓርቲ ወደ ጨዋታው ሜዳ እንዲገባ አይፈቅድም፡፡ እናም መርጋ መጋረጃውን ገልጠው ለኢህአዴግ ዘራፍ ይሉለታል፡፡ኢህአዴግ ድምጹን አጥፍቶ ክርክሩ በምርጫ ቦርድና በፓርቲዎች መካከል እንደሆነ እስክናምን ድረስ መገኘውን ይሰውራል፡፡መርጋን ብትለቃቸው አንተን አያድርገኝ ካላቸው ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡
አብዩት የሚጠራው ማን ነው?ምርጫ ቦርድ ለምርጫ እየተዘጋጀ የሚገኝ ከመሰለን ተሞኝተናል፡፡ሰሞነኛው ድርጊቱ አብዩትን እያገለገለ ለመሆኑ አስረጂ ነው፡፡በመላ አገሪቱ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን አንድነትን ከምርጫው ለማገድ ከጫፍ ደርሷል፡፡ፓርቲው ህገ ወጥ ምርጫ አድርጓል ላሉ ሰዎች በሆቴል ውስጥ ምርጫ እንዲያከናውኑ ሁኔታዎችን በማመቻቸት መሪዎችን እንዲመርጡ አስደርጓል፡፡ይህም ምርጫ ቦርድ አንድነትን በበላይ ፈቃዱ ለሚመራው ካቢኔ ከመስጠት ይልቅ ትዕግስቱ አወሉን መረጥን ላለው ቡድን ለመስጠት መዘጋጀቱን ያሳያል፡፡በበላይ የሚመራውና የብሄራዊ ምክር ቤቱን እውቅና ያገኘው ቡድን ከአፈንጋጩ ቡድን ጋር እንዲጋጭ በምርጫ ቦርድ ብዙ ተለፍቶለት የነበረ ቢሆንም ትግሉን ከገዢው ቡድን ጋር ማድረጉ ሊሰራ ለነበረው ድራማ ግብዓት አሳጥቶታል፡፡
ምርጫ ቦርድን ወረቀት ላይ እንደቀረ ኪሳራ እንደሚቆጥረው የተናገረው የአንድነቱ ፕሬዘዳንት በላይ ፓርቲው የዘንድሮውን ምርጫ የሞት ሽረት ትግል አድርጎ መውሰዱን ይፋ አድርጓል፡፡ምርጫ ቦርድ ይህንን ሀይል በፈራው ኢህአዴግ በመታዘዙም አንድነት የሌለበትን ምርጫ ለማዘጋጀት የወሰነ ይመስላል፡፡
አንድነቶች ምርጫውን ታሳቢ በማድረግ ሲሰሩ በመቆየታቸው ወደ ምርጫ አትገቡም የሚለው ውሳኔ ብዙ ሊያሳዝናቸው ይችላል፡፡የምርጫ ፓርቲ መስርተው ለሚታገሉ ቡድኖች ምርጫ አትገቡም ሲባሉ የሚኖራቸው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፡፡ከምርጫ ቦርድ ያገኙትን ሰርተፊኬት በመመለስ ወደየቤታቸው መበታተን ወይም ህዝባዊ እምቢተኝነት በስርዓቱ ላይ እንዲፈጠር መስራት፡፡አንድነቶች የመጀመሪያውን አማራጭ ከዚህ ቀደም ጠረጴዛቸው ላይ በማቅረብ ውድቅ ያደረጉት በመሆኑ የሚተገብሩት ሁለተኛውን አማራጭ ይሆናል፡፡
ለህዝባዊ እምቢተኝነቱ ህዝብ ትልቁ መሳሪያ መሆኑ አይካድም፡፡አንድነት ይህንን ህዝብ ማግኘት እንደማያስቸግረው ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡በስርዓቱ የተከፉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር የትየሌለ ነው፡፡ስርዓቱ ያልነካው አንገቱን እንዲደፋ ያላደረገው የህብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ደደቢት በረሃ ድረስ ያመራችው አርቲስት ሳትቀር ለስርዓቱ ጉምቱዎች ‹‹እናንተስ በምርጫ ትወርዳላችሁን››በማለት ጠይቃቸዋለች፡፡አርቲስቷ ያነሳችው ጥያቄ የእርሷ ብቻ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ለውጥ ሊታይበት የሚችለው ሰላማዊ መንገድ ዝግ ሲሆን የሚከፈተው የአብዩት መንገድ በመሆኑ በመንገዱ ኢህአዴግን ለማሳለፍ ከአንድነት ጎን የህዝብ ጅረት ሊሰለፍ ይችላል፡፡
የአንድነት መታገድ የአንድነት ብቻ አይሆንም
ምርጫ ቦርድ በአቋሙ በመጽናት ይህንኑ ካደረገ በአንድነት ላይ የተወሰደው እርምጃ ህገ ወጥነት ተሰምቷቸው የተወሰኑ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ፡፡መድረክ ከአንድነት ጋር በመፋታቱ የአንድነትን ከምርጫ መታገድ ከቁብ ቆጥሮት እኔም ከምርጫው እወጣለሁ ይላል በማለት ለመናገር ባልደፍርም ሰማያዊ ና መኢአድ ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ፡፡ይህም ስርዓቱ ላይ የሚታይ ጫናና ህዝባዊ እምቢተኝነትን ከምርጫው በፊት ለመፍጠር ዕድል ይከፍታል፡፡አብዩቱ የሚፈጠረው ግን በምርጫ ቦርድ ወገንተኛ ውሳኔ እንጂ በፓርቲዎቹ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ፓርቲዎቹማ በምርጫው ለመሳተፍ ራሳቸውን እያዘጋጁ የነበሩ ናቸው፡፡10346525_435976806552557_6872474233828421189_n
10428627_759966307421639_3753389504227116176_n
64334_759966300754973_6395978200166176093_n

No comments:

Post a Comment