ze-habesha
ፖሊስ የደብረ ማርቆስ ተማሪዎችን እየደበደበ ነው፡፡ የትናንትናው ተቃውሞ በኢሳትና በሌሎች ሚዲያዎች መተላለፉን ተከትሎ ‹‹ማን ነው ከኢሳትና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር እየተደዋወለ መረጃ የሚሰጠው?›› እንዲሁም ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ካለ ተናገሩ›› በሚል ተማሪዎቹን አሳልፈው እንዲሰጡ ከፍተኛ ደብደባ እየፈጸመ መሆኑን ከቦታው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡ ፖሊስ አሁንም ተማሪዎችን እየፈለገ እያሰረ መሆኑም ተገልጾአል ይላል የዛሬ ዋና ዜና።
እነዚህ ልጆች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ታዳጊ ህጻናት ናቸው። ወዲያም አደረግነው ወዲህ ደህንነታቸው በዋናነት በቤተሰብና በማህበረሰቡ ሀላፊነት ላይ ነው ገና ያለው። ጥቃት እየፈፀመባቸው ያለው አካል ስራው ደህንነታቸውን መጠበቅ ይገባቸው ከነበሩት አንዱ “መንግስት” ተብዬው ነው። ይህ አካል ሁላችንንም እየቀጠቀጠ እየገዛ ያለና አሁንም ቤተሰብ ለምን ቢል ጥቃት ከመሰንዘር የማይመለስ መሆኑ ቢታወቅም። በአጠቃላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ ባላንጣ ቢሆንም። እነዚህ ልጆች ለብቻቸው መተው ግን በጭራሽ የለባቸውም።ቤተሰብም ማህበረሰቡም ዝም ብሎ ይህንን ህፃናት ልጆቹ ላይ የሚፈፀም ወንጀል መመልከት የለበትም። እጅጉኑ ዝም ልንለው ከሚገባው በላይ ያለፈም ነው።
ህፃናቱን ምን አድርጉ ነው የሚላቸው። 90%የሚሆኑት ለመምረጥ ገና እድሜያቸው አልደረሰም። ምረጡኝን ምን አመጣው። በጣም ከጥቂቶች በቀር አስራ ስምንት አመት ገና ያልሞላቸው አማካኝ እድሜያቸው አስራ ስድስት አመት አካባቢ የሆኑ ታዳጊ ህፃናት ናቸው። የትኛውንስ ርእዬት አለም ለማጥመቅም ሆነ ተከታዬ ሁኑ ለማለት ቤተሰቦቻቸውን አስፈቅዷል ወይ?። ተጠይቀንስ ፈቅደናል ወይ?። ይህም ሆኖ መታወቅ ያለበት ለአቅመ አዳም ለደረስነውም ማስገደድ ከባድ ወንጀል ነው። ህፃናትን አስገድዶ ተከታዬ ሁኑ፤ አስገድዶ ምረጡኝ ማለት አስገድዶ ከመድፈር በምንድን ነው የሚለየው?። ይህ አላንስ ብሎ መደብደብ፤ ማሰር፤ ትምህርታቸውን ማስተጓጎል፤ ማሸበርንስ ምን የሚሉት?፤ ማን አለብኝነትስ ነው?። እንዴትስ ነው ይህ ዝም ተብሎ የሚታየው?። ለልጆቹስ ይወጡት ተብሎ የሚተወው።
ልጅ እያለው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲለቀቁ እየጠበቅን ቾክ እንለምን ነበር። ልጅ ስለነበርኩም ይሆናል ተማሪዎቹ ጠብደል ጠብደል ያሉ፤ በስርአቱ የለበሱና ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚሄዱ ጎልማሶች ነበሩ። እኔ ሁለተኛ ደረጃ ስደርስ እንደጠበኩት አልነበረም። ገና ፔፕሲ፤ ሱዚና ሌባና ፖሊስ እረፍት ላይ ቅልጥ አድርገው የሚጫወቱ ነበሩ። አሁን ደግሞ ልጆቼ ናቸው። አውቃለው በእርግጠኛነት በጣም በለጋ እድሜ ያሉ ታዳጊ ህፃናት ናቸው። በዛ ላይ ገና አስረኛ ክፍል ያልደረሱ።
No comments:
Post a Comment